
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከ26 ዓመታት በፊት 1988 ዓ.ም የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት ሕጋዊ ሰውነትን አግኝቶ ሲቋቋም መነሻ ካፒታሉ ከ26 ሚሊየን ብር አይበልጥም ነበር፤ የቀድሞው ጥረት ኮርፖሬት የአሁኑ ንጋት የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት።
የአማራ ክልል ሃብት እና ንብረት የኾነው ንጋት የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት ከ13 ቢሊየን ብር በላይ ጠቅላላ ሃብት አለው። በማኑፋክቸሪንግ፣ አገልግሎት፣ ግብርናና አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ኮንስትራክሽን እና ማማከር የሚሠራባቸው ዘርፎች ናቸው።
ንጋት በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው 15 እና ከአጋር አካላቱ ጋር የሚጋራቸው 4 በድምሩ 19 ኩባንያዎች እና 6 ፕሮጀክቶች አሉት። በባለቤትነት ከያዛቸው ኩባንያዎች እና ፕሮጀክቶች የሚያገኘው የትርፍ ክፍፍልም ለተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ማስፋፊያ፣ ለማኅበራዊ ልማት እና ለተቋሙ ሥራ ማስኬጃ ይውላል ያሉት የኮርፖሬቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምላኩ አስረስ (ዶ.ር) ናቸው።
ንጋት ላለፉት 26 ዓመታት ጥረት በሚል ስያሜ መዝለቁን ያወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዘመኑን በዋጀ እና የአማራ ሕዝብን እሴት፣ ማንነት እና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ራሱን እያደራጀ ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ሃብት እና ንብረት ከመኾኑ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ተጠሪነቱ ለክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት ኾኗል ያሉት ዶክተር አምላኩ በተከታታይ የመዋቅር፣ የአሠራር እና የስያሜ ለውጥ ሲያካሂድ ቆይቷል ብለዋል።
የድርጅቱ መቋቋም ዋና ዓላማ በክልሉ ሥር የሰደደውን ድህነት ለማስወገድ በሚረገው ጥረት የራሱን ድርሻ መወጣት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቆይታው በርካታ የልማት እና የበጎ አድራጎት ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
በቅርቡ በአሸባሪው ቡድን የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት እና ለጎርጎራ ፕሮጀክት ከ214 ሚሊየን ብር በላይ ሰጥቷል ተብሏል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የስያሜ እና የምልክት ለውጥም ድርጅቱ በተጠናከረ መንገድ ወደ ሕዝብ እንዲቀርብና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ግዙፍ የሕዝብ ተቋም ኾኖ ሳለ ወደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ማስጠጋት እና ከሕዝብ መነጠል ተገቢ አይደለም ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ እና የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል፥ ይህ አካሄድ የሚጎዳው የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይኾን የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን ዜጎች ጭምር ነው ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ክልሉ የተከፈተበትን ወረራ እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት ተከትሎ የንግድ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ተጎድቶ ነበር ያሉት አቶ መላኩ ጥረት ሰባት ቢሊየን ብር የንግድ እንቅስቃሴ በማድረግ ተኪ አልነበረውም ብለዋል።
ተቋሙ በሥራ እድል ፈጠራ፣ ገቢ ማመንጨት፣ የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ እና መሰል አበርክቶዎች የክልሉ ሕዝብ ሃብትነቱን አሳይቷል ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው። ችግሮች እና ውስንነቶች ቢኖሩ አሠራርን ግልጽ በማድረግ ለሕዝብ በቂ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በመርኃ ግብሩ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ እና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ እና የቦርድ አባል ዳግማዊት ሞገስ፣ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/