ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ!

164

የካቲት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ጦርነት ከውስጥም ከውጭም ያልተሰነዘረባትን ዘመን ማንሳት ከቻልን ምንአልባትም አንድ ለእናቱ የንጉሥ ገብረ መስቀል ዘመነ ንግሥና ብቻ ነው፡፡

በተደጋጋሚ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያዊያን መሪዎቻቸው ይኽንን ዓለም እስከወዲያኛው ሲሰናበቱ እንኳን በወጉ እና በማዕረጉ የሸኙበት ጊዜ ከገላውዲዎስ በኋላ እምብዛም አልተስተዋለም፡፡ ኢትዮጵያን ጠላት ከሩቅ ቢጠፋ ከቅርብ፤ ከውስጥ ቢከስም ከጎረቤት አያጣትም፡፡ ቸር አሳድረኝ ብላ ቸር አውለኝ እስከምትል ጠላቶቿ እንደ አሸን ፈልተው ያድራሉ፡፡ ደግነቱ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ እና ጠላቶቿ አሰላለፋቸው ዳዊት እና ጎሊያድን ስለሚመስል በአንድ ጠጠር የሚወድቁት ይበዛሉ፡፡

ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ! ይህ ክስተት ከታላቁ የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ ውጤት ከኾነው የዓድዋ ድል በኋላ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተ ሌላ አኩሪ ገድል ነው፡፡ ዳግም ኢትዮጵያዊያን ድንበራቸው እንዳይቆረስ ክብራቸው እንዳይቀንስ ሲሉ እስከ ሕይዎት መስዋእትነት የደረሰ ዋጋ ከፍለውበታል- የካራማራው ጦርነት፡፡

ግልጽ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከመታወጁ ቀድሞ ታላቋን ሶማሌ ላንድ የመመሥረት የቆየ ጽኑ ፍላጎት የነበራቸው እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሶማሊያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በፕሬዚዳንትነት የመሩት መራሄ መንግሥት ዚያድ ባሬ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል የድል ብስራት ጮራ የወጣችላቸው ይመስላል፡፡ በአንጻሩ ለረጅም ዘመናት ሥር የሰደደውን ዘውዳዊ ሥርዓት አሳልፈው በማኅበረ ሱታፊ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም ሀገሪቱን ለመምራት ደፋ ቀና የሚሉት አፍቃሪ ሶሻሊስቱ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አጣብቂኝ ውስጥ የወደቁ ይመስላል፡፡

ጋዜጦች ስለጉዳዩ ሲያትቱ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ባልጠበቁት አቅጣጫ የመውደቃቸው መርዶ መጣ ይላሉ፡፡ ራዲዮኖች ከቅኝ ግዛት ዘመን ሴራ ጀምሮ የተጋቱትን ትርክት ደጋግመው ይወቅራሉ፡፡ አካባቢውን ለዘመናት በጥብቅ ስትሻው የኖረችው እንግሊዝ ተከፋይ ዞቤዎቿን በኦጋዴን ሰማይ ስር ታንዣብብ ይዛለች፡፡ የውስጥ ገንጣይ አስገንጣዮች ከሀገራቸው ክብር ይልቅ የስልጣን ጥም አናውዟቸው እራታቸውን በዳረጎት ለመቀየር በግልጽ እና በህቡዕ ከላይ ታች ይማስናሉ፡፡

በአጭሩ ከንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን መናጋት ማግስት፣ ከተማሪዎች ንቅናቄ ሳልስት እና ከተራማጅ ኃይሎች መንኮታኮት በኋላ ሥልጣን በመዳፋቸው ሥር የወደቀላቸው ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ገና ወንበራቸውን በወጉ ሳያደላድሉ እድል ቀድማ ፊቷን ያዞረችባቸው መስላለች፡፡ ይህ ኹሉ ሲኾን ግን ፕሬዚዳንት ዲያድ ባሬ ገና ግልጽ ጦርነት አላወጁም ነበር፡፡

የፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ጦር በባንዳ ስብስቦች እየታገዘ በምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትሮችን እና በደቡብ በኩል 300 ኪሎ ሜትሮችን ድንበር ጥሶ ገብቷል፡፡

ከሙስታሂል እስከ ጎዴ፣ ከገላዳን እስከ ዋርዴር፣ ከወልወል እስከ ቀብሪድሃር የኢትዮጵያ ግዛቶች በወራሪው ኃይል ቁጥጥር ስር ገብተዋል፡፡ በወቅቱ የቀረችው ቁልፍ ቦታ ብትኖር አንድ ደጋሃቡር ብቻ ናት፡፡ የጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም መንግሥት ገና በጥዋቱ ያበቃለት እና ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለወራሪ እጅ የሰጠችበት ጊዜ እየተቃረበ ለመምጣቱ በርካቶች ጥርጣሬ አልነበራቸውም ነበር፡፡ ያውም ደግሞ ጣሊያንን የሚያክል ጦር መቆሚያ እና መቀመጫ ያሳጡት ኢትዮጵያዊያን እምብዛም የጦርነት ድል ታሪክ በሌላት ሀገር መደፈር የእግር እሳት የኾነባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡

የፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምን መንግሥት መውደቅ ለሚጠባበቁ የህቡዕ እና የግልፅ ጠላቶቻቸው የድል ብስራት ዜና መስማት ናፍቋቸዋል፡፡ በወርኃ ሐምሌ 1969 ዓ.ም ጦርነቱ በግልፅ ሲታወጅ ደግሞ ቀድሞ የተዘጋጀው ወራሪ ኃይል ጅግጅጋ፣ ሐረር እና ድሬድዋ ድረስ ዘልቆ ገባ፡፡ የውጭ ድጋፍ የነበረው የፕሬዝዳንት ባሬ ጦር ክንድ እየበረታ መጣ፡፡ በምዕራባዊ የሶማሌ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ሲፈተን የነበረው የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል እና የኦጋዴን አካባቢ ነዋሪ በቀላሉ ለጥቃት ተዳረገ፡፡ ያም ኾኖ ግን ለፕሬዝዳንት ባሬ ጦር ነገሮች አልጋ ባልጋ አልኾኑም፤ ያላሰበው መከላከል እና ጥቃቶች ያጋጥሙት ነበር፡፡

የፕሬዝዳንት ባሬ ጦር አልሞት ባይ ተጋዳይ ኾኗል፤ የኢትዮጵያ የውስጥ ተገንጣዮች ህቡዕ ድጋፍ ደግሞ ጉልበት ኾኖታል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ የረጅም ዘመን መሪ የኾኑት የኩባው ፊደል ካስትሮ 16 ሺህ ወታደሮቻቸውን ልከው የጓድ መንግሥቱን ጦር እንዲቀላቀሉ አድርገዋል፡፡ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምም ወደ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ለመግባት ቋፍ ላይ የቆሙ ይመስላሉ፡፡

የካቲት 26/1970 ዓ.ም በምሥራቁ ኢትዮጵያ ሞቃታማ ቦታዎች ባንዱ “ካራማራ” የእሳት አሩር የሚተፉ እና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ድምፆች ከምድር ከሰማይ ተደባለቁ፡፡ በፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም የሚታዘዘው የኢትዮጵያ ጦር “አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” በሚል ዓላማ ወደፊት ገሰገሰ፡፡ የሞት ሽረት ትግል በካራማራ ሰማይ ሥር ኾነ፡፡

በምሥራቁ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ከ6 ሺህ 100 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ከ12 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳረጉ፡፡ እንደዚያም ኾኖ ግን ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት ራዕዩ ጫፍ የደረሰ የመሰለው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ በመጨረሻም “በዚች ዓለም ላይ ምንም ቋሚ የኾነ ነገር የለም” ለማለት ተገደደ፡፡

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል የወጣች የመሰለችው የባሬ ፀሐይ መልሳ በምሥራቅ በኩል በሶማሊያ ሰማይ ስር ስትጠልቅ ተመለከተ፡፡ ታላቅ ለመኾን ያቀደላትን ሶማሊያም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ላላባራ ጦርነት አጋፍጧት አለፈ፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ እልህ አስጨራሽ የድል ጦርነት 84 ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ወር በሰሜን ኢትዮጵያ በዓድዋ ተራሮች በእምዬ ምኒልክ ዘመነ ንግሥና ራሷን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነፃ አድርጋለች፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያው የዓለም ጥቁር ሕዝብ የነጻነት አርነት ከኾነው የዓድዋ ድል ተመልሳችሁ ወደ ምሥራቅ ስትዞሩ ደግሞ የዛሬ 44 ዓመታት የካቲት 26/1970 ዓ.ም የዚያድ ባሬን ወረራ በመመከት ኢትዮጵያዊያን ዳግም በካራማራ ገድል ኾነ፡፡

መሪ እና ኗሪ አላፊዎች ይኾናል እንጂ በትናንቱም ኾነ በሚመጣው መካከል ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚከፈለው ዋጋ ኹሌም አንድ ነው “ከግል ሕይወት በላይ ነጻነት!” ምሥጋና እና ክብር ትናንት በጋራ ወድቀው ዛሬ በነጻነት ላኖሩን ኹሉ ይሁን!

በታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleከአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ለአመራርና ሠራተኞች ሲሰጥ የነበረን የገንዘብ ብድር በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ፤
Next article“ሕገ ወጥ ግብይትንና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር እየናረ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመግታት የመንግሥት አስፈፃሚዎች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ.ር)