በክልሉ በመስኖ ልማት ተስፋ ሰጪ የበጋ ምርት መመልከታቸውን ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ተናገሩ።

137

የካቲት 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ በመስኖ የለማን የስንዴ ሰብል ተመልክተዋል።

ከርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በተጨማሪ የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በመስኖ ልማት በኩታ ገጠም ምርት መማረታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል። መልካም የሚባል ጅማሮ እያዩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና የግብርና ባለሙያዎች ከፍተኛ እገዛ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል። እያመረቱት ያለው ስንዴ በጥራትና በምርታማነት የተሻለ መኾኑንም አንስተዋል። የዘር አቅርቦት መዘግየት እንዲቀረፍም ጠይቀዋል። ሰብላቸውን ወደ ገበያ እንዳያደርሱ የመንገድ ችግር እንቅፋት እንደኾነባቸውም ተናግረዋል።

ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከኾነ አሁን እያመረቱት ካለው ምርት የተሻለ ማምረት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎችን በማሰማራት በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የአርሶአደሩን ሕይወት ለመቀየር በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑም ተመላክቷል። በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ኅብረተሰቡን እንዲያግዙ እየተደረገ መኾኑም ተነስቷል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶ.ር) ቁርጠኝነት ካለ የአርሶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት መቀየር ይቻላል ብለዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ባከናወነው ሥራ አርሶ አደሮቹን ራሱንም ተጠቃሚ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በወልቃይት ጠገዴ፣ በጃዊ እና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የክልሉን ለም መሬቶች በማልማት ክልሉን መቀየር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰቡን ሊለውጥ የሚያስችል ሥራ መሥራት አለባቸውም ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በክልሉ ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅና የግብርና ሥራውን በቁርጠኝነት መሥራት የክልሉ ኹለት ታላላቅ ግንባሮች መኾናቸውን ገልጸዋል። በተከናወነው ሥራም በግብርናው ዘርፍ ብዙ ለውጦች መታየታቸውንም ተናግረዋል። ባዩት የመስኖ ልማት መደመማቸውንም ገልጸዋል። “ያየሁት ኹሉ ተስፋ የሚሰጥና ተሰፋን የሚያለመልም ነው” ብለዋል።

የአርሶ አደሮች ትጋት የእድገት ጉዟችን ቅርብ እንደኾነ የሚያሳይ ነውም ብለዋል። አርሶ አደሮቹ በርካታ ችግሮች አሉባቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ካደረግን ከፍተኛ ለውጥ ይመጣልም ብለዋል። መንግሥት አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን እንዲጠቀም ያደርገልም ነው ያሉት።

የተጀመሩ የመስኖ ግድቦች ሲጠናቀቁ አሁን እየተመረተ ከሚገኘው ምርት በብዙ እጥፍ ከፍ ማድረግ እንደሚቻልም ገልፀዋል። አርሶ አደሩ በአካባቢው በሚገኙ መስኖዎችን በመጠቀም ራሱን እንዲቀይርም አሳስበዋል። አርሶ አደሮቹ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ነው የተናገሩት።

ዩኒቨርሲቲዎች እያደረጉት ላለው ጥረትም አመስግነዋል። ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የኹሉም ተቋማትን ርብብር እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን አርሶ አደሩ በብዙ ነገር እየተለወጠ መኾኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የኩታ ገጠም ልማት በበጋ ወቅትም ተግባራዊ እየተደረገ አርሶ አደሩን እየጠቀመ መኾኑን መመልከታቸውን ነው የተናገሩት። አርሶ አደሮቹ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች መፍታት ከተቻለ የተጀመረውን ውጤት ማሳደግ እንደሚቻል መመልከታቸውንም ተናግረዋል። የሚነሱ ጥያቄዎችንና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ግብርና ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleከ100 ሺህ በላይ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እየተሠራ ነው።
Next articleበውጭ ሀገራት በተለያዬ ምክንያት ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየተሠራ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።