ብሔራዊ ምክክር ለብሔራዊ መግባባት

203

የካቲት 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ለረጅም ጊዜ ለግጭት እና ለመከፋፈል መሠረታዊ ምክንያት በኾኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያገባናል የሚሉ አካላት በሰለጠነ መንገድ የሚያደርጉት ውይይት እንደኾነ ምሁራን ያነሳሉ፡፡ በዚህም በዓለም ከአርባ በላይ ሀገራት የተሳኩ እና ያልተሳኩ ብሔራዊ ምክክር መድረኮች አካሂደዋል፡፡

ኢትዮጵያም ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ራሱን የቻለ ኮሚሽን አቋቁማ እየሠራች ነው፡፡

ውጤታማ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ምን ዓይነት መንገድ መከተል ያስፈልጋል?

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምሕር መኮንን አለኸኝ (ዶ.ር) እንዳሉት በኢትዮጵያ የብሔራዊ መግባባት ጥያቄው ካለፉት መንግሥታት ጀምሮ ሲነሳ የቆየ ነው፡፡ አለመግባባቶችን ለመፍታት ብሔራዊ እርቅ ማውረድ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደኾነ ያነሱት ዶክተር መኮንን ይኽንን ለማድረግ ደግሞ በሀገሪቱ ለልዩነት፣ ለግጭት ወይንም ለአለመግባባት ምክንያት የኾኑ መሠረታዊ የጋራ ሀገራዊ ጥያቄዎችን በጥንቃቄ መለየት ይገባል ብለዋል፡፡

ችግሮችን በመለየት ለምክክር የሚያመቻቹ አካላትን ደግሞ ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ ነፃ እና ገለልተኛ ከኾኑ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና በእኩልነት ሊወስኑ ከሚችሉ አካላት ማቋቋም ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል፡፡ የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ከመነሻው እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ተገቢውን ክትትል፣ ቁጥጥር እና ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ምክክሩ ምን ፋይዳዎች አሉት?

•ብሔራዊ ምክክር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡

•ከግጭት እና ከጦርነት አዙሪት በመውጣት ለልማት ትኩረት ለመስጠት፣ ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ ኹሉም ዜጋ በእኩልነት የሚኖርባት ሀገር ለመገንባት ያስችላል፡፡

• ሀገሪቱ ከድህነት እንድትላቀቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ መሰረታዊ የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታት እድል ይሰጣል፡፡

•ተቋማዊ ተቀባይነትን ያሻሽላል፡፡

•በተለይም ደግሞ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ሀገራዊ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡

• ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የተሳካ የፖለቲካ ሽግግር ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ዶክተር መኮንን ጠቅሰዋል፡፡

የብሔራዊ ምክክሩ መልካም እድሎች ምንድን ናቸው?

በኢትዮጵያ በሚካሔደው ብሔራዊ ምክክር በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት ዐዋጅ መውጣቱ፣ ኮሚሽነሮች መመረጣቸው፣ ብሔራዊ ምክክሩን አስመልክቶ በመንግሥት ሥልጠና መሰጠቱ እንደመልካም እድል ተነስተዋል፡፡

ከምሁራን እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሐሳብ ግብዓቶችን መሰብሰባቸው፣ በአብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ተቋማት፣ የውጭ አካላት ድጋፍን ማግኘቱ ሌላው እንደ መልካም እድል ሊታይ እንደሚገባ ነው ዶክተር መኮንን ያነሱት፡፡ ባለፉት መንግሥታት ሲገፋ የቆየ በመኾኑ በዚህ ወቅት ተቀባይነት ማግኘቱም መልካም አጋጣሚ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ ምክክሩ ተግዳሮቶችስ?
የተወሰኑ የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች አኹንም በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ሥር መኾናቸው የብሔራዊ ምክክር መድረኩን ሂደት ሊፈታተን እንደሚችል አንስተዋል፡፡

ጫፍ የረገጡ አመለካከቶች አኹንም መኖራቸው ለምክክር መድረኩ ሂደት ሌላኛው ችግር ሊኾን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው የተዛባ ትርክቶች አለመስተካከላቸው ለምክክሩ ትልቅ ችግር ሊኾን እንደሚችል ምሁሩ አንስተዋል፡፡

ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሔዎችስ?
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ልማት ትምሕርት መምሕር ዶክተር አልዩ ውዱ እንደሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው፡፡

•ለአንዱ ብሔር ቁልፍ የኾኑ ጉዳዮች ለሌላው ብሔር ቁልፍ ጉዳይ ባይኾኑ እንዴት መግባባት ላይ መድረስ ይቻላል የሚለው ጉዳይ መታሰብ አለበት፡፡

•ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ መሠረታዊ የኾኑ የግጭት ምክንያቶችን መለየት፤

• የምክክሩ አባላት ከብሔር ብሔረሰቦች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሲቪል ተቋማት፣ ከዲያስፖራው፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም አካላት በተቻለ መጠን አካታችነትን በተላበሰ መንገድ የተመረጡ ሊኾኑ ይገባል፤

• የተመረጡ አባላትም ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ እና ከግል ፍላጎት ነፃ ሊኾኑ ይገባል፤

•ኮሚሽኑ የትግበራ ዕቅድ በማዘጋጀት ከጅምሩ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በሚዲያ ሸፋን መስጠት እና በተለያዩ አማራጮች በየጊዜው ለሕዝብ ግልጽ ሊያደር ይገባል፡፡

•በብሔራዊ ደረጃ ውይይት ከመደረጉ በፊት ከመንደር ጀምሮ ሕዝብን ባሳተፈ መንገድ ውይይቶች ሊደረጉ ይገባልም፤

• ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን ሕጎች፣ አጠቃላይ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ተዓማኒነት ማረጋገጥም ትኩረት መሠጠት አለበት፤

•በዋና ዋና ችግሮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ ባለፉት ዓመታት የተፈጸሙ ወንጀሎች በሀገሪቱ ዳግም እንዳይደገሙ ዋና የወንጀል ተዋናዮችን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል፤

•ካሳ በመክፈል፣ ይቅርታ መጠየቅ፣ እርቀ ሰላም ማውረድ ይከናወናል፤

•በየአካባቢው ባሉ አደረጃጀቶች ማኅበረሰቡ በባሕላዊ መንገድ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች ፊት ለፊት በመነጋገር መፍትሔ መስጠት ይገባልም፡፡

የአብዛኛዎቹ ሀገራት ውድቀት ምክንያቱ በሂደቱ ላይ የሚነሱ የግልጸኝነት ጥያቄ እንደኾነ ያነሱት ዶክተር አልዩ የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት መፍታት ይገባዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“እርር ቅጥል ቢሉም የእርሱ ጠላቶቹ፣ ምኒልክ ጀግና ነው እስከ ዘመዶቹ”
Next article“አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ በተካሔደው ትግል የአማራ ሕዝብ ስንቅ እና ትጥቅ ለጸጥታ ኀይሉ በማቅረብ እና በቀጥታ በመፋለም የማይተካ ሚና አበርክቷል”