
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 126ኛው የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በባሕርዳር እና አካባቢው የአብን ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሰብሳቢ በቃሉ ታረቀኝ (ዶ.ር ) እንዳሉት ዓድዋ ፍትሕ የተረጋገጠበት፣ ራስን የመኾን ብቃት ያሳየ ድል ነው። ዓድዋ ሀገርን አጽንቷል፤ ጥቁር በቅኝ ገዥዎች ያደረበትን ፍርሃት፣ የበታችነት እና የዝቅተኝነት ስሜት ያስወገደ እንደኾነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በየጊዜው የተቃጣባቸውን ጥቃት በአንድነት በመፋለም የሀገራቸውን ነፃነት ቢያስከብሩም አኹንም የውስጥ ባንዳዎች ሀገሪቱን ለመበተን እየሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል። በተለይም ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን መሳደድ ለማስቀረት በመርህ ላይ የተመሠረተ ትግል ያስፈልጋል ብለዋል።
በሀገር የባለቤትነት ጉዳይ ላይ መመካከር ያስፈልጋልም ነው ያሉት ዶክተር በቃሉ። በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ሀገር በቀል መፍትሔ፣ ጥበብ የተሞላ የአመራር ዘዴ እና አካታች ሥርዓተ መንግሥት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። የአኹኑ ትውልድም የራሱን ዓድዋ የሚሠራበት ጊዜ አኹን መኾኑን ነው የገለጹት።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባል ጽጌ ገነት(ዶ.ር) ‟አባቶቻችን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የመጣውን ወራሪ ኀይል ድል ያደረጉበት ምስጢር መሪና ተመሪው በመደማመጡ እና ሕዝባዊ አንድነት በመኖሩ ነው” ብለዋል። በቅኝ የተገዙ ሀገራት የነፃነት ቀናቸውን ሲያከብሩ ኢትዮጵያ ግን የድል ቀን ማክበር እንድትችል አስችሏታል ነው ያሉት።
ይኹን እንጂ አሁንም በዓድዋ ድል የተሸማቀቁት ቅኝ ገዥዎች በእጅ አዙር መንገድ በውስጥ ባደራጁት ተላላኪዎቻቸው በኩል ኢትዮጵያን ለማዳከም ከተቻለም ለማፍረስ እየሠሩ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የአኹኑ ትውልድም የዓድዋን የአንድነት እና የመተባበር መንፈስ በመላበስ ልክ እንደ አባቶቹ የተጋረጠበትን የኅልውና አደጋ የመሻገር ታሪካዊ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል። ከእርስ በርስ መናቆር በመውጣት የመደማመጥ ባሕል ማዳበር ይገባዋልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/