“የዓድዋ ጀግኖች ነፃነትን ከነ ክብሩ በደማቅ የጻፉ፤ ከሀገር በላይ ምንም አለመኖሩን በግብር ያረጋገጡ ናቸው” የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን

139

ደባርቅ: የካቲት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ 126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡

በዓሉ “ዓድዋ ለኢትዮጵያዊያን ሕብረት፤ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ጮራ”በሚል መሪ መልእክት ነው የተከበረው፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለዓለም ፈንታሁን፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ፈንታሁን አየለ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፣ የደባርቅ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ቀደምት አባት አርበኞችና የከተማው ማኅበረሰብ በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ያለዓለም ፈንታሁን “የዘንድሮው ዓድዋ ድል በዓል ሀገራችንን ከመበተን በታደጉ ተጋድሎዎችና የዘመናችን ታላቅ ክዋኔ በተሰኘው የህዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጨት የታጀበ በዓል መኾኑ ልዩ ያደርገዋል” ነው ያሉት፡፡

ዋና አስተዳዳሪው “የዓድዋ ጀግኖች በሞታቸው ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ፣ ነፃነትን ከነ ክብሩ አድምቀው የጻፉ፣ ሞትን በነፃነት ድል የነሱ፤ ከሀገር በላይ ምንም አለመኖሩን በግብር ያረጋገጡ ጀግኖች ናቸው” ብለዋል፡፡

የዞኑ የባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ አሥራት ክብረት በበኩላቸው የዓድዋ ድል በኢትዮጵያዊያን የመሪነት ጥበብ፣ በአርበኞቻችን ጀግንነት የተገኘ ለጥቁር ሕዝቦች ተስፋን የፈነጠቀ፣ ለምዕራባዊያን ድንጋጤ የፈጠረ ደማቅ ድል መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ስለ ዓድዋ ጦርነትና ድል ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ፈንታሁን አየለ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) አሸባሪው የትግራይ ቡድን የፈፀመውን ወረራ ለመቀልበስ በተደረገው ተጋድሎ ብዙ ገድል የፈፀሙት ጀግኖች አርበኝነትን በታሪክ አንብበው፣ ሰምተውና ከአባቶቻቸው ወርሰው ነው ብለዋል፡፡

ነፃ ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ አርበኛ ያስፈልገናል ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አርበኛን ለመፍጠር የዓድዋ ድል በዓልን በየዓመቱ በድምቀት ማክበር፣ ጀግኖች አርበኞችን በተገቢው መንገድ መዘከርና ታሪካቸውን ለትውልድ መንገር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የደባርቅ ወረዳ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር አርበኛ በላይ ድልነሳ “የዓድዋ ድል አባቶቻችን ለነፃነታቸው ደማቸውን ያፈሰሱበት፣ አጥንታቸውን የከሰከሱበት፤ አፍሪካዊያን የነፃነት ጮራ ያዩበት የተከበረ በዓል ነው” ብለዋል፡፡

“ዓድዋን ድል ለትውልድ ለማስተላለፍ አባቶች ለትውልድ ታሪክን በተገቢው መግለጽ፤ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ኢትዮጵያን ከነክብሯ ለትውልድ ለማስተላለፍ የአባቶቹን ጋሻ ማንሳት አለበት” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በበዓሉ አርበኞችን የሚዘክሩና ታሪክን የሚነግሩ ክዋኔዎች ከቀረቡ በኋላ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን በጀግንነት ተፋልመው መስዋእትነት ለከፈሉ ሰማእታት የኅሊና ፀሎት በማድረግ ተጠናቅቋል፡፡

ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ -ከደባርቅ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleሀገረ ምኒልክ የአፍሪካዋ ጃፓን ወይስ አፍሪካዊቷ ኤልዶራዶ?
Next articleትውልዱ በዓድዋ የታየውን የአንድነት እና የመተባበር መንፈስ በመላበስ የተጋረጠበትን የኅልውና አደጋ የመሻገር ታሪካዊ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አሳሰበ፡፡