ሀገረ ምኒልክ የአፍሪካዋ ጃፓን ወይስ አፍሪካዊቷ ኤልዶራዶ?

199

ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ሀገረ መንግሥት ያጸናች ምድረ ቀደምት መሆኗን በርካታ የታሪክ ሰነዶች ያመላክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በመልካ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በተፈጥሮ ሃብት እና በባሕል የበርካቶችን ቀልብን ቀድማ የሳበች ጥንታዊት ሀገር ብትሆንም የዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ትውውቋ ግን ዘግየት ብሎ ይመዘዛል፡፡

በበርካታ የታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ የሚቆጠረው አጼ ቴዎድሮስ ወደ ስልጣን ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው ይላሉ፡፡ በሀገሪቱ የሥነ መንግሥት ታሪክ ለአንድ ምዕተ ዓመት የተጠጋው የዘመነ መሳፍንት ቆይታ ሀገሪቱን ማዕከላዊ መንግሥት አሳጥቷት በጎጥ እና በእርስት ተሸንሽና እና ተዳክማ ቆይታ ነበር፡፡ በዘመነ መሳፍንት ስርዓት ውስጥ ተፈጥሮ የዘመነ መሳፍንት ማርከሻ እና መደምደሚያ የሆነው ቋረኛው ካሳ ኀይሉ ወደ ስልጣን ሲመጡ የሀገሪቱ ዘመናዊ አሥተዳደርም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መቆጠር ይጀምራል፡፡

ሀገሪቱን በየጊዜው ለመሯት ነገሥታት ሁልጊዜም ቢሆን ፈተና የነበሩት የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገቦች ነበሩ፡፡ እነዚሁ የውጭ ኀይሎች የአፄ ቴዎድሮስን የዘመናዊነት እሳቤ አምክነው ለሕልፈታቸው ምክንያት ቢሆኑም ከእርሳቸው ቀጥሎ ለሚመጡት ነገሥታት የጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እርሾ ትተውላቸው አልፈዋል፡፡ ከዋግ ሹሙ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ የሦስት ዓመታት አጭር የመሪነት ቆይታ እና ከአፄ ዮሐንስ የ17 ዓመታት መሪነት በኋላ የመጡት የሸዋው ምኒልክ ዓለም ስለጥቁሮች ያለውን የተንሸዋረረ እይታ በኅይል የቀየሩ ዘመናዊ እና ተራማጅ መሪ ያደርጋቸዋል፡፡

የ1888ቱን የዓድዋ ጦርነት ድል አድራጊነት የ19ኛው ክፍለ ዘመን መደምደሚያ እንጂ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መክፈቻ አይደለም ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡

በሌላ መልኩ የዓድዋ ድልን ተከትሎ በመላው ዓለም የተቀጣጠለውን የጥቁሮች አቢዮት ያስተዋሉ፣ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን የመረመሩ እና ዓለም በተለይም አሜሪካውያን ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመስረት መሻትን የተመለከቱት ደግሞ የዓድዋ ድል የ20ኛው ክፍለ ዘመን መክፈቻ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡

ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች በአንድ ነገር ይስማማሉ፤ እርሱም የዓድዋ ድል የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መደምደሚያ ስለመሆኑ፡፡ ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን ቅጥ ያጣ ጥላቻ እና መታበይ አክስሞ ጥቁሮችም በጦርነት እንደሚያሸንፉ ለአዲሱ ክፍለ ዘመን የትውልድ ተረኞች ፍንጭ የሰጠ ክስተት ነው -የዓድዋ ድል፡፡

በመላው ዓለም በግፍ፣ በባርነት እና በስቃይ ለሚማቅቁ ጥቁሮች የትግል አርነት ነው -የዓድዋ ድል፡፡ ተፈጥሮ ሃብታቸውን እንጂ ማንነታቸው ለተረሳው እና ለተዘነጋው አፍሪካዊያን የማንቂያ ደወል ነው -የዓድዋ ድል፡፡ ዓለም ለአፍሪካዊያን ያለውን የተሳሳተ ግምት እና እይታ ደግሞ እና ደጋግሞ እንዲማርበት ያደረገ ክስተት ነው -የዓድዋ ድል፡፡ እናም በምኒልክ መሪነት እና በምኒልክ ሀገረ መንግሥት ተራሮች ነጮች ክፉኛ የተቀጠቀጡበት የዓድዋ ድል የ19ኛው ክፍለ ዘመን መደምደሚያ ክስተት ነበር መባሉ ስህተት የለውም፡፡

ድል አድራጊው ንጉሠ ነገሥቱ ግን በዓድዋ ተራሮች ባገኙት ድል የሚዘናጉ እና የሚታበዩ ቆሞ አልነበሩም፡፡ የዓድዋ ድል የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መደምደሚያ ቢሆንም ምኒልክ ግን ፈጥነው ወደ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እሳቤ እና እይታ አሸጋገሩት፡፡ የማይኮሩት እና የማይፈሩት ንጉሥ ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ የሄዱበት መንገድ ምዕራባዊያኑን ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ሀገረ ምኒልክ የአፍሪካዋ ጃፓን ወይስ አፍሪካዊቷ ኤልዶራዶ? ብለው እንዲጠይቁ አስገደዳቸው፡፡

ወትሮውንም ጦርነትን ፈጽመው ያልፈለጉት አጼ ምኒልክ ተገድደው የገቡበትን ጦርነት በድል አድራጊነት ካጠናቀቁ በኋላ ፊታቸውን ያዞሩት ድንበራቸውን ከማይነካ፣ ከሕዝባቸው ጋር ትከሻ ከማይለካካ እና በውስጥ አሥተዳደራቸው ገብቶ ከማያቦካ ሀገር ጋር በትብብር መሥራትን ነበር፡፡

ቴክኖሎጂን ለሀገራቸው የሚናፍቁት እና ስልጣኔን ለሕዝባቸው የሚሹት አጼ ምኒልክ በዓድዋ ተራሮች ግርጌ በሚመሩት ሕዝብ ተጋድሎ እና በበሳል መሪነታቸው ያገኙትን ድል ለስልጣኔ መንገድ እና ለዲፕሎማሲ ግንኙነት እድል ተጠቀሙበት፡፡ ከባቡር እስከ ስልክ፣ ከዘመናዊ ጦር እስከ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት፣ ከትምህርት ቤት እስከ ሆስፒታል፣ ከወፍጮ እስከ ፖስታ ዘመናዊነትን አነፍንፈው የሚያላምዱት አጼ ምኒልክ በበርካታዎቹ ምዕራባዊያን ዘንድ “ሀገረ ምኒልክ የአፍሪካዋ ጃፓን?” ልትሆን ትችላለች ሲሉ ለመጠየቅ ተገድደዋል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍን በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊቀይር እንዴት ይቻለዋል?” ሲሉ የሚሳለቁት ነጮች ለኢትዮጵያ ስልጣኔ የማይዋሃዳት እስከማስመሰል ለመናገር ዳድቷቸው ነበር፡፡ ምኒልክ ግን ይህንን የተንሸዋረረ እይታቸውን ቀየሩት፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆነን በአጤ ምኒልክ ካልኮራን ታዲያ በማን ልንኮራ እንችላለን! አጤ ምኒልክ በተለይም ከ1903 ዓ.ም ጀምሮ ከአሜሪካ ጋር የጀመሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በበርካቶች ዘንድ አዲስ እይታን ፈጠረ፡፡

የወቅቱን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ልዩ መልዕክተኛ እና ቆንሲል ስኪነር በተለየ ክብር ተቀብለው የንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስምምነት የተፈራረሙት አጼ ምኒልክ ሀገራቸው በምዕራባዊያን ዘንድ በልዩ ትኩረት እንድትመረመር እድል ፈጠሩ፡፡

ይህንን የአሜሪካን እና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያስተዋሉት ምዕራባዊያን ጋዜጠኞች ኢትዮጵያን በ1480 ዓ.ም ካከተመው የኤልዶራዶ ሥርዓት ጋር ያገናኙታል፡፡ ኤልዶራዶ የስፓኒሽ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ወርቃማ” ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኤልዶራዶ ወይስ ኢትዮጵያ ራሷ የጠፋችው ኤልዶራዶ ነች ብለውም ለመመርመር ይሞክራሉ፡፡ ኤልዶራዶ በ15ኛው ክፍለ ዘመን ማለቂያ ቀደም ብሎ በደቡብ አሜሪካ ይኖር የነበረ የሙስካ ንጉሥ መጠሪያ ነበር፡፡ ቆይቶ ደግሞ ኤልዶራዶ ከንጉሡ አልፎ የግዛቱ እና የከተማዋ መጠሪያ ሆነ፡፡ አሳሹ ክርስቶፎር ኮሎምበስ በ1592 ዓ.ም ማዕከላዊውን አሜሪካ ካገኘ በኋላ በርካታ አሳሾች ወደ ቦታው ዘልቀው ገብተው ነበር፡፡

በወቅቱ የሚሰሙት እና ትኩረታቸውን የሚስብ አንድ አፈ ታሪክ ነበር፡፡ ይህ ታሪክ የሚያወሳውም ስለጠፋችው እና ስለተሰወረችው የወርቅ ከተማ ኤልዶራዶ ነበር፡፡ እናም ምዕራባዊያኑ ጋዜጠኞች አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጠፋችው ኤልዶራዶ ጋር አገናኝተው ነበር ለመመርመር የፈለጉት፡፡ መነሻቸው ደግሞ ዓድዋ፣ ቀደምትነቷ፣ የተፈጥሮ ሃብቷ፣ ጽናቷ እና አይበገሬነቷ ከወቅቱ ተፈላጊነቷ ጋር ተዳምሮ ነበር፡፡

ለምዕራባዊያኑ የቅኝ ግዛት እንቅፋት የሆነችውን ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ያጸኗት በሳል መሪ እምየ ምኒልክ ነበሩ፡፡ ከጦርነት ወጥቶ በዲፕሎማሲ መንገድ ለአፍሪካ ምሳሌ የሆነችውን ሀገር የመሯት እና ያስተዋወቋት ጥቁሩ ንጉሥ ምኒልክ ነበሩ፡፡ ሀገረ ምኒልክ ዛሬ ከአንገታቸው ቀና ብለው ለሚሄዱ ጥቁሮች ባለውለታ ናት፡፡ ግፉአን አርነት የወጡት በምኒልክ እና በዓድዋ ነውና ዘላለም ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡ ጥቁሩ ንጉሥ የነጮች ራስ ምታት ነውና ዛሬም ድረስ በትውልዱ ልብ ውስጥ መሪ ነው፡፡ ምንጭ፡- ታላቁ ጥቁር በንጉሴ አየለ

በታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Amhara Media Corporation – YouTube
youtube.com

Previous article“የዓድዋ ድል የተገኘው በእምዬ ምኒልክ ብልሀትና ጥበብ፣ በእቴጌ ጣይቱ ድፍረትና በሁሉም ኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶክተር)
Next article“የዓድዋ ጀግኖች ነፃነትን ከነ ክብሩ በደማቅ የጻፉ፤ ከሀገር በላይ ምንም አለመኖሩን በግብር ያረጋገጡ ናቸው” የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን