ማኅበራዊ ሜዲያን ለበጎ ዓላማ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና የሚያገኙበት የጣና ሽልማት አሸናፊዎች ነገ ይታወቃሉ፡፡

155

ማኅበራዊ ሜዲያን ለበጎ ዓላማ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና የሚያገኙበት የጣና ሽልማት አሸናፊዎች ነገ ይታወቃሉ፡፡

ሽልማቱ በባሕር ዳር የሚካሄድ መሆኑን የጣና ሽልማት አዘጋጅና የዘመራ ማስታወቂያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ አያሌው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

የሽልማት ሥነ-ስርዓቱ ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በ21 ዘርፎች የተወከሉ እጩዎች ዕውቅናና ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዕጩዎቹ ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን ተጠቅመው ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች እንዲጎለብቱ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

ተሸላሚዎቹ ከጥላቻ ይልቅ ማኅበራዊ አንድነት እንዲጠነክር የሠሩ፣ የሀገራቸውን መልካም ገጽታ ያስተዋወቁና በመሰል አወንታዊ ተግባራት የተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንደሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

እንደ አቶ ደምስ ገለፃ ዕጩዎቹ 30 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ የሚያገኙት ከሕዝብ በተሰጠ ጥቆማና አስተያዬት ነው፤ 70 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከተለያዩ ዘርፎች የተወጣጡ ምሁራን በሚሠጡት ውጤት መሠረት ነው፡፡ ዕጩዎቹ ማኅበራዊ ሜድያን ሲጠቀሙ የሚለቋቸው ፎቶ፣ ተንቀሳቃሽ ምስልና ይዘት እንደሚወዳደሩ ተመላክቷል፡፡

ሽልማቱ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ማኅበራዊ ሜድያን ተጠቅመው ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸውን መረጃዎች የሚያደርሱ ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም አዘጋጆቹ አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ በሚካሄደው የጣና ሽልማት የዕጩዎችን ቁጥር እንዲጨምርና ለዝግጅቱ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የበጀት ችግሮችን ለመቅረፍ አጋር ድርጅቶች ሊኖሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleየአሜሪካ ኤምባሲ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የደስታ መግለጫ አወጣ፡፡
Next articleየአማራ ክልል መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኖቤል አሸናፊ መሆን የተሰማውን ደስታ ገለጸ፡፡