
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድነታችን አርማ የሆነው የዓድዋ ድል የልዩነት ምንጭ እንዲሆን ሲሠራበት ነበር፡፡ ይህ አዝማሚያ አሁንም እየተስተዋለ ስለመሆኑ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምሕሩ ዶክተር ጥጋብ በዜ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ በነጻነት መኖር ለአፍሪካውያን የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል መነሳሳትን ሲፈጥር ለቅኝ ግዛት አቀንቃኝ ሀገራት ግን ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት የዓድዋን ድል ትሩፋቶች የማንኳሰስ እንቅስቃሴ በስፋት ታይቷል፡፡
ኢትዮጵያ በወታደራዊ ትግሉም ይሁን በዲፕሎማሲው ዘርፍ እንዳሸነፈች በትክክል እየታወቀ እውነታውን ለመቀበል ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ የዓድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት መጠናቀቁ በጣልያን ድክመት እንጂ በኢትዮጵያውያን ጥንካሬ የተገኘ እንዳልሆነ ለማስረጽ ጥረት አድርገዋል፡፡ ፋሽስት ጣልያን ዳግም ለመውረር ጥረት እስካደረገበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ የተረጋጋች እንዳትሆን አሻጥር ሲሠራ ነበር።
በኢትዮጵያውያን መካከል መከፋፈል እንዲኖርም አቅማቸውን አሟጥጠው ሲሠሩ ቆይተዋለ። የጣልያን ተረክ ውላጅ የሆነው ወያኔ ለዘውጋዊነት ሥርዓት ሕገ-መንግሥታዊ ሽፋን ሰጥቶ ሀገሪቱ በዘር ፖለቲካ እንድትታመስ አድርጓል። በዚህም ብዙ ምስቅልቅል እንዲኖር ማድረጉን ነው ዶክተር ጥጋብ የተናገሩት፡፡ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ለታሪካዊው ዓድዋ ድል የተሰጠው ትርጉም እና ትኩረት በእጅጉ አስተዛዛቢ ሆኖ አልፏል፡፡ እነዚያ አካላት ለታሪክ የነበራቸው አረዳድ መንሻፈፍ እና የታሪክ ሽሚያ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ትውፊቶች የሚያንኳስሱ ሆነው አልፈዋል።
የኢትዮጵያውያን የአንድነት አርማ የሆነው ዓድዋ ድል የልዩነት ምንጭ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ትውልዱ ሀገርን እንዲገነባ ከማስተማር ይልቅ እርስ በእርስ እንዲነታረክ ተሠርቷል፡፡ ይህ አዝማሚያ አሁንም እየታየ መሆኑን የታሪክ መምሕሩ አብራርተዋል፡፡
ሆን ተብሎ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት፣ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ታግዞ የተጣመመ ታሪክ በትውልዱ ውስጥ እንዲሰርጽ ተደርጓል፡፡ የታሪክ መምሕሩ እንዳሉት ይህም ወጣቱ በታሪኩ እንዳይኮራ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ ወጣቱ ይህንን ድንቅ ታሪክ በትክክል እንዳይገነዘበው አድርጎታል፡፡
ይሁን እንጂ በዓድዋ ጦርነት የታየው ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ጀግንነት፣ አልደፈር ባይነት እና የሥነ-ልቦና ልዕልና በተለያዩ አጋጣሚዎች ይስተዋላል፡፡ እኛ ባለንበት ዘመንም የዚህ እኩይ ተግባር ባለቤት የኾነውን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት ሕዝቡ በአንድነት ተሰልፏል፡፡ ይህም የማይበጠስና በደንብ የተሰናሰለ ማንነት የመኖሩ ማሳያ ነው ይላሉ ዶክተር ጥጋብ፡፡
እንደዚህ አይነት እሴቶችን ይበልጥ ማጉላት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ወጣቱ በታሪኩ እንዲኮራ፣ ታሪክ ለሀገር ግንባታ እንዲውል በአግባቡ ማስተማር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ተዋንያን ሰከን ብለው ሕዝብና ሀገርን ያማከለ ተግባር መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ልዩነት ላይ ከማተኮር ይልቅ ለአንድነት፣ ከመነታረክ ይልቅ ለመነጋገርና ለጋራ ሀገር ልዕልና ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለታሪካቸውና ለማንነታቸው ዋጋ መስጠት እንደሚገባቸው የጠቀሱት ዶክተር ጥጋብ ሕዝቡ ወደ ቀልቡ መመለስ እንዳለበት አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/