የዓድዋ ፈርጦች በመላው ዓለም ያሉ ጥቁሮችን ያኮራ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡

228

ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዓድዋ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍ ብሎ የሚታይ እና በወርቅ ቀለም ተከትቦ ትውልድ በቅብብሎሽ የሚያከብሩት ብሔራዊ በዓል ነው፡፡ የዓድዋ ድል በዓል በድል እንዲጠናቀቅ ገፊ ምክንያቶች አሉት፡፡ በዛሬው ዘገባችን ታዲያ የኢትዮጵያን አርበኞች እና የቁርጥ ቀን ልጆችን በማነሳሳት ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

የባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ገረመው እስከዚያ (ዶ.ር ) እንደነገሩን በዓድዋ ጦርነት መላው ዓለምን ያስደመመ ድልን እንድንጎናፀፍ የአዝማሪዎች ሚና ከፍተኛ ነበር ይላሉ፡፡ ሊቀ-መኳሶች አበርክቷቸው ከፍ ያለ ቢኾንም በተለያዩ የታሪክ መጽሐፍቶችም ሆነ በዘገባዎች እነዚህ ታላላቅ ኢትዮጵያዉያን ሲዘከሩ አይስተዋልም ብለዋል ዶክተር ገረመው፡፡

ሊቀ-መኳሶች ኢትዮጵያውያን አርበኞችን ከማወደስ እና ከማነሳሳት አልፈው የንጉሥን ሃሳብ እስከመሞገት የደረሰ አቅምም ነበራቸው። የታሪክ መምህሩ እንደሚሉት ትግልን በአሻፈረኝ ስሜት በማነሳሳት፣ ጦርነቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ከፍተኛ ኢትዮጵያዊ ስሜት የተሞላባቸዉ ግጥሞችን ከማሲንቆ ጋር በማዋዛት፤ ዘማቾችን በማበረታታት የእቴጌ ጣይቱ የግል አዝማሪ የነበረችዉ ጣዲቄ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡

ስለዚች አዝማሪት ሰፋ ባለ መልኩ ፈረንሳዊው ጎብኝ ሃኪም ሜየር እንደፃፈም መምህሩ አስረድተዋል፡፡ ይህች ጀግና ኢትዮጵያዊት ጣሊያኖች ከኢትዮጵያዊያን ጋር የሰላም እናዉርድ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት እንዲህ ስትል መቀኘቷንም ነግረውናል፡፡ ‹‹አዉድማው ይለቅለቅ በሮቹም አይራቁ፣
ቀድሞም ያልሆነ ነው፣ ዉትፍትፍ ነው እርቁ››

ፊታውራሪ አባ ጎራው የዓድዋ ድል ታሪክ በተነሳ ቁጥር በጀግንነታቸው የሚወደሱ የዓድዋ ፈርጥ ነበሩ። አዝማሪዎችም በተደጋጋሚ ተቀኝተውላቸዋል።
‹‹የንጉስ ፊታውራሪ የጎራው ገበየሁ፣ አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፣
ለምሳም አልበቁት ቁርስ አደረጋቸው››
በአንባ አላጌ ውጊያ ወቅት ከተሰዉ ጀግኖች መካከል ፊታውራሪ አባ ውርጂ አንዱ ነበሩ። አርበኛው ከጀኔራል ማጆር ቶዞሊን ጋር ተያይዘው ወደ ገደል በመወርወር መስዋእት በሆኑ ጊዜ አንድ አዝማሪ እንዲህ ሲል ተቀኘ።

‹‹ጀኔራሉን ማጆር ቶዚሊ፣ ማን ይነካዋል ያለ ፈጣሪ፣
ገደል ሰደደው አንድ ፊታውራሪ›› በሁለተኛዉ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የተለያዩ የሀገር ፍቅር ስሜትን የሚያግለበልቡ ቅኔያት፣ ግጥሞችና የቅስቀሳ ንግግሮች ተካሂደዋል፤ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን ኢትዮጵያ በጣሊያኖች ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት፣ጣሊያኖች ይፈፅሟቸው የነበሩ ድርጊቶችን በመታዘብ፣
‹‹አውራ ጎዳና ላይ ዳቦ እየገመጡ፣
እቤተስኪያን ገብቶ ትምባሆ እየጠጡ…›› ሲሉ አዝማሪዎች ተሳልቀውባቸዋል፡፡

የአዝማሪዎች ሚና በአድዋና በማይጨው ጦርነት ተወሰኖ የቀረ የጀብድ ታሪክ ብቻ አልነበረም፡፡ የሴት መኳንንቷ ጣዲቄ አበርክቶ ለ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችም ከፍተኛ መነሳሳትን መፍጠሩን የቅርብ ጊዜውን ክስተት በማንሳት የታሪክ መምህሩ አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድን (ዶክተር) የክተት መክት የህልውና ዘመቻ ጥሪ በመቀበል ቁጥራቸው በርከት ያሉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ግንባር ድረስ በመዝመት፣ ሕዝቡን በማነሳሳት፣ ከዘርፉ የሚገኙ ገቢዎችን በጦርነቱ ለወደሙ አካባቢዎች ለመልሶ ማቋቋም እና ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በማዋል፣ በተለያዩ ሚዲያዎች ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችና ጥበባዊ ይዘት ያላቸዉን መልዕክቶችን በማስተላለፍ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ዶክተር ገረመው አብራርተዋል።

የጥበብ ሰዎች በተለያዩ የባሕል መዝናኛ ስፍራዎች ስለሀገራዊ አንድነት፣ ስለሰላም፣ ስለጦርነት እንዲሁም ስለሀገር መሪዎች ተቀኝተዋል፡፡

‟የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስተሳስሩ፣ የሀገር አንድነትን የሚያጠናክሩ እንዲሁም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን መሥራት ቢችሉ እኛም የዘመናችንን ዓድዋ የሆነውን ድህነት እና መለያየት ማሸነፍ እንደምንችል መገንዘብ ያስፈልጋል“ ብለዋል።

ዘጋቢ፡- የምስራች ኀይሉ (በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምሕርት ክፍል ተማሪ)

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Amhara Media Corporation – YouTube
youtube.com

Previous article❝የዓድዋ የነጻነት ተጋድሎና ድል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አርማ ነው!!❞ የአማራ ክልል መንግሥት
Next article“እንኳን ለ126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን” ደመቀ መኮንን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር