
ባሕር ዳር: የካቲት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 126ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ❝የዓድዋ የነጻነት ተጋድሎና ድል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አርማ ነው❞ ሲል ገልጿል።
የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋደሎ ምልክትና ውጤት ነው፡፡
ለጦርነቱ መነሻ የኾነው በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው የውጫሌ ውል ስምምነት አንቀፅ አስራ ሰባት የጣልያንኛውና የአማርኛው ትርጉም የተለየ ሐሳብ መያዙ ነው፡፡ የአማርኛው ትርጉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ልዕልና የሚያከብር ሲኾን የጣልያንኛው ትርጉም ግን የሀገራችንን ሉዓላዊነት መዳፈር ብቻ ሳይኾን ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ይነካል፡፡
ይህን የተገነዘበው የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን ጥቅም በማይነካና ሉዓላዊነቷን በሚያከብር መልኩ እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ውጤት ሳይመጣ ስለቀረ ወደ ጦርነት መግባት የግድ ኾነ፡፡
በጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ አርበኞች በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ፋሽስታዊ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ወራሪ በአንድ ቀን ጦርነት የካቲት 23/1888 ዓ.ም ድል አድርገውታል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በጦርነት፣ በወታደራዊ መረጃ፣ በደፕሎማሲና በፖለቲካል ጥበብ የሰለጠነውን እስከ አፍንጫው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የፋሽስት ወራሪ ሠራዊት ዕቅድ በማምከን ዓድዋ ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጅታለች፡፡
የዓድዋ ድል በአፍሪካ የጦርነት ታሪክ ውስጥ የተከበረና የተደነቀ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ብስራት ነው፡፡ በዓድዋ ጦር አምባ ታሪክ ለሀገራቸው ነፃነትና ክብር ህይወታቸውን ለመስጠት ያልሳሱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአፍሪካ ምድር የነፃነትን ምስጢር በክቡር ደማቸው በዓድዋ ተራሮች ላይ ጽፈው አልፈዋል፡፡
በፈሰሰው ክቡር የኢትዮጵያውያን ጀግኖች ደም ሰንደቅ ዓላማችን በአፍሪካ እና በመላው ዓለም ደምቆና ከፍ ብሎ እንደተውለበለበ ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ተጋድሎና ቆራጥነት በዓለም የነፃነት ምድር የጥቁር ሕዝቦች አይበገሬነት ተምሳሌት ኾናለች፡፡
የዓድዋ ድል የአባቶቻችንን ጀግንነትና ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከሩበት ድል ሲኾን ሀገራችንን ከአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ በመታደግ በዓለም አቀፍ መድረክ ታዋቂነትን እንድታገኝ ምክንያት ኾኗል፡፡
ድሉ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መመስረትንና በቅኝ ግዛት ለወደቁ አፍሪካውያን ነጻ መውጣት ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በጥቅሉ የዓድዋ የነጻነት ተጋድሎ ለኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የኩራትና የክብር ምንጭ የኾነ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈ፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ወኔ በመኾን መነቃቃት የፈጠረና በአባቶቻችን ደም የደመቀ ታላቅ አንፀባራቂ ድል ነው፡፡
በመኾኑም የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል የካቲት 23/2014 ዓ.ም ለአንድ መቶ ሃያ ስድሰተኛ ጊዜ በድምቀት ስናከብር በዓለማችን ታሪክ ውስጥ የፈጠረውን አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍና የአባቶቻችንን አደራ አንግበን ሉዓላዊነታችንን እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጽናት ላይ ማተኮር ይኖርብናል፡፡
በተለይ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እያደረሱብን ያለውን ጫናና ጣልቃ ገብነት በመቋቋምና አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በክልላችን በከፈተው ጦርነት የደረሰውን ጉዳት በመልሶ ግንባታው እንቅስቃሴ ከመንግሥታችን ጎን በመቆም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውሰጥ በንቃት መሰለፍ ይጠበቅብናል፡፡
ሀገራችን በሰላም በልማትና በዴሞከራሲ ሥርዓት ግንባታ የጀመረችውን ጉዞም በማስቀጠል የዓድዋን ድል እጥፍ ድርብ ልናደርገው ይገባል፡፡
የዓድዋን ድል ስናከብር የተሸረሸረውን ኢትዮጵያዊ አንድነትና እሴት መልሶ በጽኑ መሰረት ላይ ለመትከል ቃል እየገባን መኾን አለበት።
እንኳን ለ 126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
የካቲት 22/2014 ዓ.ም.
ባሕር ዳር – ኢትዮጵያ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/