
የካቲት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባለ ርስት ኾነው ሳለ እንግዳ፣ ባለሀብት ኾነው ሳለ የበይ ተመልካች ኾነው የቆዩት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አማራዎች ከበጌምድር ተነጥለው በማይመስላቸው ማንነት ውስጥ ለዓመታት ቆይተዋል። እነዚህ የስሜን በጌምድር አማራዎች ለማንነታቸውና ለነፃነታቸው ሲሉ ለዓመታት ተጋድሎ አድርገዋል። በተጋድሏቸውም ነፃነታቸውን እና ማንነታቸውን አስመልሰዋል።
በተፈጥሮ ላገኙት የአማራ ማንነት እና የፀና ኢትዮጵያዊነት ሲሉ አያሌ መከራዎችን ተቀብለዋል። በተጋድሏቸውም ማንነታቸውን ዳግም ተጎናፅፈዋል። የመሠረተ ልማት ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱላቸውም ጠይቀዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ወጣቶች ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በባሕር ዳር መክረዋል።
ወጣቶቹ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ሲናፍቁትና ሲናፍቃቸው ከኖረው ሕዝብ ጋር ተገናኝተዋል። በተጓዙባቸው አካባቢዎች ኹሉ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። አንድነታቸውንም ለማፅናትም ከሕዝባቸው ጋር ቃል ተጋብተዋል። ወጣቶቹ በተዘዋወሩባቸው አካባቢዎች ኹሉ አስደናቂ ፍቅር እንደተሰጣቸው ነው የተናገሩት።
ወልቃይት ጠገዴ ወደነበረው ማንነቱና የግዛት አስተዳደሩ ተመልሷል ብለዋል ወጣቶቹ፡፡
በማንፈልገው ማንነት እና ሥርዓት ኖረናል ያሉት የወልቃይት ጠገዴ ወጣቶች ወልቃይት ጠገዴ ነፃ እንዲወጣ መላው የአማራ ሕዝብ ተጋድሎ ስላደረገ ለታገለልን ሕዝብ ምስጋና ለማቅረብ ተጉዘናል ነው ያሉት። ትግሉ እስኪቋጭ ድረስ ሕዝቡ በጋራ እንዲቆም ለማሳሰብና ጦርነቱ ስላለበቃ የአማራ ወጣቶች እና ሌላው ኢትዮጵያዊ ጠንክሮ እንዲታጠቅ ለማሳሰብ መጓዛቸውንም አስታውቀዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በአሸባሪው ሕወሓት የኃይል አገዛዝ ዘመን ግፍ ሲፈጸምበት ቢኖርም ዛሬ ላይ ነጻነቱን አረጋግጦ ከወገኑ ጋር ደስታውን እየተጋራ ነው ብለዋል፡፡ እናቶች በየመንገዱ በእልልታ እንደተቀበሏቸውም ገልፀዋል።
አሸባሪው ሕወሓት ሕዝብ አሳዶና ገድሎ በአማራ ለም መሬት ላይ ትግራይን መገንባት ዓላማ ይዞ ወልቃይት ጠገዴን በኃይል ወስዶት እንደነበር ነው የተናገሩት። የትግራይ አሸባሪ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፅም እንደኖረም ተመላክቷል። በኃይል የተወሰደው ማንነት ለነጻነት በተደረገ መራር ተጋድሎ መመለሱንም ወጣቶቹ ገልፀዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የቀደመ ማንነቱን ቢጎናፀፍም በመሠረተ ልማት እጦት ችግር ውስጥ መኾኑንም ተናግረዋል። የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥት ተባብረው የመሠረተ ልማቶችን ችግር እንዲፈታም ጠይቀዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በማንነቱ ሲደርስበት የነበረውን ግፍ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀውም ተናግረዋል። የወልቃይት ጉዳይ የአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይኾን የመላው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እንደኾነም ገልጸዋል።
እኛ የጠየቅነው እውነት፣ ማንነት ነው፣ ማንነት ደግሞ ኾነን የተወለድነው ነው፣ ሰው የሰጠን አይደለም፣ መላው ኢትዮጵያውያን እውነታዎችንን ተረድተው ከጎናችን እንዲቆሙ እንጠይቃለንም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/