“እኛስ አባት አለን ምኒልክ የሚባል እንኳን ተቆጥቶ ዝም ሲል ያባባል”

266

የካቲት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቁሮች አባታችን የሚሉት፣ ስሙን ከፍ አድርገው የሚያነሱት፣ በዚያ ዘመን በዙፋን በዚህ ዘመን በልባቸው ያነገሱት፣ በውስጣቸው ያተሙት፣ የጥቁርን የመከራ ካባ ያወለቀ፣ የነጭን ክንድ በክንዱ ያደቀቀ ኃያል ንጉሥ፡፡ መንበሩ በኢትዮጵያ ኾኖ ሳለ በግርማው በሮምም የነገሠ፣ በዝናው ዓለምን ያዳረሰ፣ የነጭን የክፋት ግንብ ያፈረሰ፡፡ የሮም አደባባዮች የሚፈሩት፣ የሮማ ነገሥታት፣ መኳንንትና መሳፍንት የሚያከብሩት፣ የሚርዱለት፣ ከወገባቸው ጎንበስ ከአንገታቸው ቀለስ ብለው ጉልበት ስመው የሚሰግዱለት፣ በማርያም የሚምል፣ ቃሉን የማያብል፡፡
ኃያላንን ነው የሚሉት የፈሩት፣ ከእኛ በላይ ማን ይከበራል የሚሉት ያከበሩት፣ ሕዝቦች ምኒልክ፣ ምኒልክ እያሉ የጠሩት፣ የሚጠሩት፡፡ አባታችን እያሉ የሚያነሱት፣ በሕይወታቸው የማይረሱት፣ አባት ኾኖ ሳለ እንደ እናት እምዬ የተባለ፣ ስሙ ከመቃብር በላይ የዋለ ኃይል፡፡
ያቺ የጥቁሮች ምድር አፍሪካ የነጭ ወታደር ዘምቶባት፣ በደልና መከራ በዝቶባት፣ የጨለማ በርኖስ ተደፍቶባት፣ ብርሃን ርቋት፣ ጨለማ አጥለቅልቋት፣ የመውጫ መንገድ ጠፍቶባት ነበር፡፡ የነጭ ነገሥታት የብስ እያቋረጡ፣ ባሕር እየሰነጠቁ ወደ ጥቁሯ ምድር ወታደሮቻቸውን ያዘምታሉ፡፡ በጥቁሯ ምድርም አያሌ በደሎችን ይፈጽማሉ፡፡ ባለ እርስቶቹ እንግዶች፣ እንግዶቹ ባለ እርስቶች ኾነው ይኖራሉ፡፡ ጥቁሮች በራሳቸው ድግስ ያባረራሉ፣ ነጮች በአፍሪካውያን ድግስ ደጋሽና ባለአባት ይኾናሉ፡፡ ግፍና መከራ የበዛባቸው ጥቁሮች በጨለማ ውስጥ ብርሃን እያበራ፣ ወደ ነጻነት የሚመራ መሪ ይሰጣቸው ዘንድ ፈጣያቸውን እየተማጸኑት ነው፡፡
አፍሪካ ድንግዝግዝ ባለ ጨለማ ውስጥ ስትኖር ታዲያ በምሥራቅ ንፍቅ በኩል ብርሃን ይታይ ነበር፡፡ በዚያች ተስፋና በረከት በተሰጣት፣ ፈጣሪ አስቀድሞ በመረጣትና በሚጠብቃት ቃል ኪዳን በበዛላት ምድር ብርሃን ነበር፡፡ እኒያ የውጭ ወራሪዎች ታዲያ በምሥራቅ ንፍቅ ከፍ ብላ የምታበረውን ፀሐይ ያጠፉ ዘንድ ወደዱ፡፡ በምሥራቅ ንፍቅ የምታበራው ፀሐይ ከጠፋች፣ በጨለማ ከተታካች አፍሪካ ሙሉ ለሙሉ በጨለማ ካባ ትጠቀለላለች፡፡ ተስፋም ታጣለች፡፡ ለአፍሪካ ምድር ተስፋዋ የምሥራቋ ፀሐይ ብቻ ነበረች፡፡
ቀኝ ገዢዎች የተስፋዋን ጀንበር ሊያጠፉ ወደ ምሥራቅ ንፍቅ ገሰገሱ፡፡ ያቺ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ የምታስቀድም፣ ክንደ ብርቱ የኾነች ምድር እንደሌሎቹ አልነበረችም፡፡ በእርሷ ቀዬ ውስጥ ጠላት አይኖርበትም፣ ደፍሮ አይረግጣትም፡፡
የምሥራቋ ጀንበር ጨለማ በበዛበት ምድር ከፍ ብላ እያበራች ነው፡፡ እርሷ የበራችው በጽናት፣ በጠበቀ አንድነት፣ በጸና ሃይማኖት ነውና የሚያጠፋት፣ ከከፍታዋ የሚያወርዳት አይገኝም፡፡
የሮም ነገሥታት፣ መኳንንትና መሣፍንት በአፍሪካ ምድር በብቸኝነት እያበራች ያለችውን ጀንበር ሊያጠፉ ወደ ቅድስቷ ምድር ኢትዮጵያ ሠራዊቶቻቸውን ላኩ፡፡ የሮም ጎዳናዎች በእልልታ ተመሉ፣ ኢትዮጵያን እንዲይዙ የተመረጡት የጦር አበጋዞች በኩራት ተንጎማለሉ፡፡ ልዑላን ነገሥታት፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ ወይዛዝርቱና ጎበዛዝቱ ሠራዊታቸው ኢትዮጵያን አስገብሮ እንደሚመጡ ሙሉ ለሙሉ ተማምነዋል፡፡ ሠራዊቱም ኢትዮጵያን አስገብሮ እንደሚመለስ ቃል ገብቶ ተነሳ፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ኃያሉ ንጉሥ ምኒልክ ነግሦ ነበር፡፡ የኢጣልያን መዘጋጀትና ጉዞ መጀመር የሰማው ምኒልክ ከእቴጌዋ ከጣይቱ፣ ከጦር ባለሟሎቹ፣ ከመኳንንቶቹና መሳፍንቶቹ ጋር መከረ፡፡ በሚገባም ተዘጋጀ፡፡ በሠንደቁና በሀገሩ ለማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብም በማርያም ምሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ ንጉሥ የሚያከብረው፣ ድንበር የሚያስከብረው የኢትዮጵያ ሕዝብም የንጉሡን ቃል በአሻገር ኾኖ ሰማ፡፡ ስንቅና ትጥቁን አዘጋጅቶ፣ ላግኝህ ወደ ተባለበት ሥፍራ ገሰገሰ፡፡
የተቆጣው ምኒልክ ሀገሩን ሊያስከብር፣ ጠላትን ሊያንበረክክ በአባ ዳኛው ላይ ተቀምጦ ፊቱን ወደ ዓድዋ አዞረ፡፡ ጎዳናዎች ኹሉ ተጨናነቁ፡፡ በየደረሰበት ኹሉ ምኒልክ፣ ምኒልክ እየተባለ ተጠራ፡፡ ጠላት የኢትዮጵያን ምድር ረግጧል፡፡ ወረራም ፈጽሟል፡፡ የማትደፈረውን ሀገር ደፍሯል፡፡ የዓለም መንግሥታት የኢጣልያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ላይ የሚያገኘውን ድል ለመስማት ጓጉተዋል፡፡ እምዬ ምኒልክ የጦር በአጋዞቹን አስቀድሞ ገሰገሰ፡፡ በአምባላጌ ላይ ሠፍሮ የነበረው የጠላት ሠራዊት ምድምጥማጡ ጠፋ፡፡ ጠላት ያልጠበቀው ነገር ገጠመው፡፡ የተረፈው ወደ መቀሌ ሸሸ፡፡ ጀግኖቹ እግር በእግር ተከታትለው ደረሱበት፡፡
በእቴጌ ጣይቱ የጦር ስልት፣ በጀግኖቹ ብስለት መቀሌ ላይ የሠፈረውን ጠላት ድባቅ መቱት፡፡ ያቺ ቀን ቀረበች፡፡ ወደ ዓድዋም ገሰገሱ፡፡ ቀኗ ደረሰች፡፡ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ፍርሃት ያልፈጠረባቸው፣ እልህ የሚተናነቃቸው፣ ጽናትና አንድነት የተቸራቸው ጀግኖች የኢጣልያንን ሠራዊት ወጥተው አሰቃዩት፡፡ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ጠላት በጎራዴ እየቀነጠሱ መሬት ላይ አነጠፉት፡፡ እንደ ቅጠል አረገፉት፣ እንደ ዱቄት በታተኑት፡፡ ድል ለባለ ድሎቹ ለኢትዮጵያውያን ኾነ፡፡
በጨለማ ማቅ ውስጥ የነበረችው አፍሪካ ብርሃን ወጣለት፡፡ በምሥራቅ ንፍቅ ስታባራ የነበረችው ጀንበር በመላ አፍሪካ አዳረሰች፡፡ ከፍ ብላም በራች፡፡ ዓለም ደነገጠች፡፡ ሮም በጨለማ ተዋጠች፡፡ በሮም አደባባይ ሲያቅራሩ የነበሩት ኹሉ አንገታቸውን ደፉ፣ በዓለም ፊት አፈሩ፡፡ አፍሪካ ደግሞ ብርሃን አየች፡፡ የዓድዋን ተራራ ፈጣሪ ከፍ አድርጎ ፈጠረ፡፡ ከዓድዋ ተራራ ላይ ደግሞ ሌላ የታሪክ ተራራ ኢትዮጵያውያን ፈጠሩ፡፡ ምኒልክ የመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት በዓድዋ ተራራ ላይ በድል ፎከረ፡፡ የኢጣልያ ሠራዊት ደግሞ እንዳልነበር ኾኖ ቀረ፡፡
አጤ ምኒልክ በየካቲት 23 ድል አድርጎ ድሉን ባጣጠመ በአንድ ወሩ በመጋቢት 23 ቀን ለሙሴ ሽፋኔ የጻፈውን ደብዳቤ ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረውታል፡፡ “በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ኾኑ፡፡ እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ኹሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኋቸው ብየ ደስ አይለኝም” ምኒልክ በድል የማይኩራራ፣ ጠላት የማይፈራ፣ ከብልሃት ብልሃት፣ ከጀግንት ጀግንነት የተቸረው ንጉሥ ነው፡፡ በግፍ ዘምተውበት ድባቅ መትቶ መልሷቸው ስለ አማሟታቸው የሚያዝን ቅን ልብ ያለው ጀግና ነው፡፡
ቤርኪሌይን ዋቢ አድርገው ጳውሎስ ኞኞ ሲጽፉ “በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋ ያለ ጦርነት የለም፡፡ በአፍሪካ በኩል ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡ አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸውን በኦሪት ዘ ፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶርና ኦዲዮን በሚባሉ አማላክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትና ሃይማኖትን የተቀበሉ ናቸው፡፡ አሁን የኹሉንም ፍላጎት ዓድዋ ዘጋው” ብለዋል፡፡
ዓድዋ የነጭን ኢፍትሐዊ አካሄድን የደመሰሰ፣ የነጭን የበላይነት የገረሰሰ፣ እኩልነትን በዓለም ያዳረሰ ኃያል ድል ነው፡፡ ታላቁ ንጉሥ አባ ዳኘው ምኒልክ ዛሬ በፈረሱ ኾኖ ወደ ዓድዋ ይመለከታል፡፡ ምኒልክ ዛሬም ከዓድዋ ተራራ ላይ ዓይኑን አያነሳም፡፡ ዓድዋ ሲታይ አንድነት፣ ዓድዋ ሲታይ አሸናፊነት፣ ዓድዋ ሲታይ ኢትዮጵያዊነት፣ ዓድዋ ሲታይ ኃያልነት አብሮ ይነሳልና ምኒልክ ዓይኑን ከዓድዋ ላይ አያነሳም፡፡ ትውልድ ኹሉ ዓድዋን ያስብ፣ በዘመኑ ዓድዋዎችን ይሥራ፡፡ ያን ጊዜ ይከበራል፣ ያን ጊዜ ያስከብራል፣ ያን ጊዜ ይፈራል፡፡
“እኛስ አባት አለን ምኒልክ የሚባል
እንኳን ተቆጥቶ ዝም ሲል ያባባል” የሚያኮራ አባት አለን፡፡ ታሪክ ሠርቶ በክብር ያኖረን፣ በኩራት ያስቀመጠን፣ ተከብሮ ያስከበረን፡፡ እንኳን ሲቆጣ ዝም ሲል የሚያባባ፣ የሚያስደነግጥ የሚያርድ ኃያል፣ ደግ አባት፣ እንደ እናት እምዬ የሚባል አባት አለን፡፡ ሀገርን ከነክብሯ ያወረሰ፣ የክብርን ካባ ለልጆቹ ያወረሰ የምንኮራበት የምንመካበት አባት አለን፡፡ እምዬ ስንል እንጠራዋለን፡፡ ምኒልክ ስንል እናከብረዋለን፡፡ ንጉሥ ኾይ ስንል እጅ እንነሳዋለን፡፡ አባ ዳኛው እያለን ድሉን እናስባለን፡፡ ስሙን እንጠራለን፣ ታሪኩን እንዘክራለን፣ የሠራውን እናከብራለን፡፡ እንኳን ለኩራትና ለአሸናፊነት ቀን አደረሳችሁ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ቀጣናዊ የሚኒስትሮች ፎረም የመምራት ኀላፊነትን ተቀበለች።
Next articleየብላቴ ልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑና በሥራ አፈጻጸማቸው ብልጫ ላሳዩ የሠራዊት አባላት የማዕረግ ማልበስ መርኃ ግብር አካሄደ።