
ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2012 ዓ/ም (አብመድ) የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በፓርኮቹ ልማት፣ ኦፕሬሽን ጥናት፣ የግንባታ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የመሬት ግዥና ርክክብ ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው ፓርኮች ሲገነቡ ለእርሻ የሚውል መሬትን አለመሻማት፣ የአየር ንብረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለማሳደር፣ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ግብዓትና የሰው ኃይል በቅርብ ማግኘት የሚያስችል መሆን በመስፈርትነት ተቀምጠዋል፡፡
ፓርኮች ሲገነቡ የካሳ እና ባለቤትነት ጉዳይ በሌሎች እንደሚሠራ የገለጸው ኮርፖሬሽኑ ‹‹የ3 ሺህ 348 ሄክታር መሬት የባለቤትነት ካርታና ደብተር ተቀብያሁ›› ብሏል።
በዚህ ወቅት በኮርፖሬሽኑ ስር ከሚገኙ 12 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሰባቱ ሥራ ላይ ሲሆኑ እነዚህም ለ50 ሺህ ቀጥተኛና ለ55 ሺህ ዜጎች ተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን -ከአዲስ አበባ