ብሔራዊ ምክክር እና የሀገራት ልምድ

226

ባሕር ዳር: የካቲት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ ከአርባ በላይ ሀገራት የተሳካና ያልተሳካ ምክክር እና ብሔራዊ እርቅ አካሂደዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ሴራሊዮን፣ ጋና፣ ሞሮኮ፣ ላይቤሪያ፣ ቡሩንዲ፣ ቶጎ፣ ዝምባብዌ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ሌሎችም ሀገራት በአፍሪካ ብሔራዊ ምክክር፣ ፍትሕ እና እርቀ ሰላም ማካሔዳቸውን ምሁራን ያነሳሉ፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ልማት ትምሕርት መምሕር አልዩ ውዱ (ዶ.ር) እንዳሉት ብሔራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ለረጅም ጊዜ ለግጭት እና ለመከፋፈል መሠረታዊ ምክንያት በኾኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያገባናል የሚሉ አካላት በሰለጠነ መንገድ የሚያደርጉት ውይይት ነው፡፡
ብሔራዊ ምክክር በዋናነት አካታች በኾነ መንገድ የተመረጡ ተዋናዮች እንደ ታሪክ፣ የመንግሥት ምስረታ፣ የፌዴራሊዝም፣ የማንነት፣ የሰንደቅ ዓላማ እና በሌሎች መሠረታዊ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መግባባት ላይ የሚደረስበት እና የውሳኔ ሐሳብ የሚያስቀምጡበት መንገድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ብሔራዊ ምክክር ውይይት እንጅ የመጨረሻ ግብ አለመኾኑን ነው ዶክተር አልዩ ያነሱት፡፡ በብሔራዊ ምክክሩ ለግጭት ምክንያት በኾኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ፤ በምክክሩ የተላለፉ ውሳኔዎች በፍትሕ እና እርቀ ሰላም መንገድ ተግባራዊ ይደረጋሉ፤ በፍትሕ እና እርቀ ሰላም ሂደት ከውይይት ባለፈ ወንጀል የፈጸሙ እና ወንጀል የተፈጸመባቸው ወገኖች በጋራ ተቀምጠው የጥፋቱን ደረጃ ይወስናሉ፤ ውጤቱ ደግሞ ፍትሕ፣ ይቅርታ፣ እርቅ እና ምሕረት ሊኾን ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሩዋንዳ የተከሰተውን የዘር ጭፍጨፋ አንዱ ማሳያ እንደኾነ ዶክተር አልዩ አንስተዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምሕር መኮንን አለኸኝ (ዶ.ር) እንዳሉት አንድ ሀገር ከገባችበት የእርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭት ወይንም አለመግባባት ወጥታ የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት በመጀመሪያ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋታል፡፡
ዶክተር መኮንን በዚህም በዓለም ከአርባ በላይ ሀገራት የተሳካ እና ያልተሳካ ብሔራዊ ምክክር፣ ፍትሕ እና እርቀ ሰላም ማካሔዳቸውን ነግረውናል፡፡ ‹‹የተሳካ ብሔራዊ ዕርቅ አካሂደዋል›› ከሚባሉት ሀገራት መካከል ኬንያን ለአብነት አንስተዋል።
በ2007 እና 2008 (እ.አ.አ) በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ያነሱት ዶክተር መኮንን ገዥው ፓርቲ እና ተፎካካሪዎች በመነጋገር ‹‹የተሳካ›› እርቅ ማካሔዳቸውን አንስተዋል።
ለዚሕ ደግሞ ምክክሩ ግልጽ ዓላማዎችን ይዞ በመነሳቱ፣ የገዥው እና የተቃዋሚ መሪዎች ያላግባባቸውን አራት መሰረታዊ አጀንዳዎች በመለየት ግልጽ ውይይት አድርገው ችግሮቻቸውን መፍታት መቻላቸው ለስኬታማነቱ በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
ምሁሩ እንዳሉት ብሔራዊ ምክክር አካሂደው ካልተሳካላቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ደቡብ ሱዳን አንዷ ናት፡፡ በምክክር ሂደት ላይ የሀገሪቱ መሪዎች የራሳቸውን ፍላጎት ማንጸባረቃቸው እርቀ ሰላሙ እንዳይሳካ ማድረጉን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ዶክተር መኮንን ግጭቶች ሳይቆሙ ወደ ብሔራዊ ምክክር መሔዳቸው ላለመሳካቱ ሌላኛው ምክንያት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
እንደ ዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መኖር ብሔራዊ ምክክሩ በሚፈለገው መንገድ እንዳይሄድም አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ ከተጀመረበት እስከ መጨረሻው ድረስ ጠንካራ ክትትል፣ ቁጥጥር እና የትግበራ ሥራ አለመሠራቱም ለምክክሩ አለመሳካት ዶክተር መኮንን እንደምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ችግሩ እስከ አሁን እንዲቀጥል ኾኗል ብለዋል፡፡
ዶክተር አልዩ በበኩላቸው በሩዋንዳ የተደረገው ምክክር ሳይኾን ፍትሕ እና እረቀ ሰላም እንደነበር ነው ለአብነት ያነሱት፡፡ በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ የተሳተፉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን ሁሉንም ለፍርድ ለማቅረብ ባለመቻሉ እንደ ወንጀሉ ክብደት ፍርድ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ከ12 ሺህ በላይ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጉዳዮች መታየታቸውን ዶክተር አልዩ ገልጸዋል፡፡
መለስተኛ ወንጀል የፈጸሙ በብሔራዊ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንደተሰጣቸው አንስተዋል፡፡ ዋና ዋና ወንጀለኞችን ደግሞ በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርጎ ተቀጥተዋል፡፡
በሩንዳ በተካሔደው የፍትሕ እና እርቀ ሰላም ሥራ ሁቱዎች እና ቱትሲዎች ሀገራቸውን በጋራ በማልማት ውጤታማ መኾናቸውን ነው ምሁሩ የጠቀሱት፡፡ ምሁሩ በተወሰነ መንገድ ካሳኩ ሀገራት መካከል ብለው ከጠቀሷቸው ቱኒዚያ ሌላኛዋ ሀገር ናት፡፡ በዚህም አዲስ ሕገ መንግሥት በመቅረጽ ምርጫን የሚመራ ተቋም አቋቁመዋል፤ ምርጫም አካሂደዋል፡፡
በሱዳን በአልበሽር ወቅት የብሔራዊ ውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ እንደነበር ያነሱት ዶክተር አልዩ በውይይቱ ሂደት የአልበሽር አሥተዳደር ከፍተኛ እጅ ስለነበረበት ማኅበረሰቡ በኮሚሽኑ እምነት በማጣቱ ሳይሳካ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ በየመንም የሀገሪቱ የአገዛዝ መዋቅር ፌዴራሊዝም መኾን አለበት የለበትም በሚል ጉዳይ አለመሳካቱን አንስተዋል፡፡
ምሁሩ ብሔራዊ ምክክር መካሄድ ያለበት ለይስሙላ ሳይኾን ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ፣ ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ፣ መልካም አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ፣ ለሰላም ትልቅ ዋጋ በመስጠት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያም ሊካሔድ ስለታሰበው የብሔራዊ ምክክር እና ፋይዳው በቀጣይ የምንዳስሰው ይሆናል፡፡ ሀሳባችሁን በአስተያየት መስጫው ላይ ብታጋሩን የሚለው የአክብሮት ግብዣችን ነው፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየመከላከያ ኅብረት ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ በሥራቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አመራርና አባላቱ የእውቅናና የምሥጋና ዝግጅት በማካሄድ ላይ ይገኛል።
Next articleኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ቀጣናዊ የሚኒስትሮች ፎረም የመምራት ኀላፊነትን ተቀበለች።