“90 ደቂቃ በሐይቅ ቢተር” ንጉሠ ነገሥት አፄ ኀይለሥላሴ

221

ባሕር ዳር: የካቲት 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለግማሽ ምዕተ ዓመታት በተጠጋው የንግሥና ዘመናቸው በርካታ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አበርክቶ እንደነበራቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በየጊዜው ከሚገጥሟቸው ችግሮች በፍጥነት ማገገም የሚችሉ፣ ጽኑ እና አገናዛቢ መሪም ነበሩ ይባላል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚገባ በመረዳት ለሀገር ውስጥ ፖለቲካው እርሾ የሚያደርጉ፤ የዓለም የፖለቲካ ጨዋታ በተወሳሰበ ቁጥር ልቀው መጫዎት የሚችሉ መሪ ነበሩ የሚሉአቸው በርካቶች ናቸው፡፡
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ውዥንብር ወቅት ሥልጣን በእጃቸው ያስገቡ፤ የዓለም መንግሥታት ማኅበርን እስከ መቀላቀል የደረሱ፤ በየሀገራቱ በሚያደርጉት ጉብኝት ሀገራቸውን እና መንግሥታዊ ሥርዓታቸውን በሚገባ ያስተዋወቁ በሳል እና ዘመናቸውን በሚገባ የዋጁ መሪ ይሏቸዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከቀደምቶቻቸው በተለየ ግብጽ እና ኢየሩሳሌምን በመጎብኘት የመካከለኛው ምሥራቅን ፖለቲካ የዘወሩ እና አዲስ ክስተቶችን የፈጠሩ ናቸው፡፡ በ1928 ዓ.ም በወቅቱ ተነባቢ በሆነው ታይም መጽሔት የፊት ገጽ ላይ “የዓመቱ ሰው” በመባል የቀረቡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ፡፡ ድል አድራጊ ንጉሥ እና ነፃ አውጪ መሪ ተደርገው የሚወሰዱ መሪም ናቸው፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሥልጣን መምጣት አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ተፈጥሮ በቸረቻው ብስለት፣ አርቆ አሳቢነት እና አስተዋይነት አለቀላቸው ሲባሉ ያልወደቁ ጠንካራ የተምሳሌት መሪ ናቸው፡፡
ከሥልጣን ማማ እንደወጡም ሁሌም የሚከተላቸው ያ የሕይዎት ውጣ ውረድ እና የጥንካሬ ምክንያታቸው የሆነ ፈተና ከራሳቸው አልፎ በሀገራቸው ላይም መጣ፡፡
ጣሊያን ከአራት አስርት ዓመታት ዝግጅት በኋላ ለዳግም ወረራ ወደ ሀገራቸው መጣች፡፡ እንደ ቀደሙት አባቶቻቸው እርሳቸውም ጣሊያንን አሜን ብለው ሳይቀበሉ ከግንባር ዘመቻ እስከ ግዞት ድረስ ክፉና በጎውን አይተዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ በይፋ ሀገራቸውን ከወረረችው ጣሊያን ይልቅ ጥላዋ በአፍሪካ ቀንድ የሚያንዣብበው እንግሊዝ የጎን ውጋታቸው ነበረች፡፡ ጣሊያን በድጋሚ ኢትዮጵያን ስትወር እና ለሞሶሎኒ ሲያስማሙአት ፍንጥር ጠጪዎቹ እንግሊዛውያን እንደነበሩ ንጉሠ ነገሥቱ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከወቅቱ የእንግሊዝ መሪ ቸርችል ይልቅ ቀዳማዊ አፄ ኀይለሥላሴ በአዕምሮ ልቀው ቀን እየጠበቁ በዝምታ ለሚፈልጉት መንገድ አመቻች እና ተባባሪ ያደርጓቸው ነበር፡፡
ንጉሡ በንግሥና ዘመናቸው ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ዘመናዊነትን እንደተላበሰች ቢያውቁም ፖለቲካዊ ሥሪቷ ግን ቆሞ ቀር እንደነበር ይሰማቸዋል፡፡ ፖለቲካቸውን እና የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓቱን ለማሻሻል ቆርጠው የተነሱት ንጉሠ ነገሥቱ ከዚህ ጎን ለጎን የእንግሊዝ ልዩ ትኩረት የነበረውን የጣና ሐይቅን እና የዓባይ ወንዝን አልምተው መጠቀም የሚያስችል መሻታቸው ጥልቅና ልባዊ ነበር፡፡
አፄ ኀይለሥላሴ ዓባይ እና ጣናን ለማልማት ካላቸው ትልቅ መሻት የተነሳ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተጀምሮ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ታሪካዊ የተባለለትን የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማደስ ጥረት ጀመሩ፡፡ ተሳክቶላቸውም በ1921 ዓ.ም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ፈር ያስያዘ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ይህም አንድ ወቅት በወርሃ የካቲት ለፈጸሟት ታሪካዊ ውይይት ፈር አስያዘላቸው፡፡
በ1919 ዓ.ም ዶክተር ማርቲን በሚል መጠሪያ የሚታወቁትን ሐኪም ወርቅነህ እሸቴን አንድ የግል ተቋም በዓባይ ወንዝ ላይ ጥናት እንዲያካሂድላቸው ለማስፈረም ቢልኩም አልሳካ ያላቸው ንጉሠ ነገሥቱ የችግሩ ምንጭ ምን እንደነበር ገብቷቸዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ያልተሳካላቸውን መልዕክተኛ ሐኪም ወርቅነህን ካልተሳካልህ ተመለስ ከማለት ይልቅ ለሌላ ተልዕኮ አዘጋጇቸው፡፡ መልዕክተኛው ወደ ኒው ዮርክ ሀርለም አቅንተው በዚያ ለሚኖሩ ጥቁር አሜሪካውያን ነጻዋ ሀገር ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ማሕጸን እንደሆነች ግንዛቤ ፍጠር አሉት፡፡ ይህም ለረጅም ጊዜ ዕቅዳቸው መደላድል እያዘጋጁ ነበር፡፡
የንጉሡ የሩቅ እሳቤ ጉዟቸውም በ1928 ዓ.ም ለተዋወቁት እና የረጅም ዘመን የሕግ አማካሪያቸው የነበሩትን አሜሪካዊ የሕግ ፕሮፌሰር ጆን ስፔንሰርን እንዲተዋወቁ ዕድል ፈጥሮላቸዋል የሚሉ አሉ፡፡
በ1937 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ከእንግሊዛውያን ጋር የተፈራረሙትን እና የእንግሊዝን ተፅዕኖ ከትከሻቸው ላይ ያሽቀነጠረላቸውን ስምምነት በማዘጋጀት ያገዛቸው ፕሮፌሰር ስፔንሰር ነው ይባላል፡፡
“ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳልን” የተካኑት ንጉሠ ነገሥቱ አሜሪካ ኢትዮጵያን የምታይበት መንገድ እንዲቀየር አደረጉ፡፡ ለርእሰ ብሔር ሩዝቬልት የአድናቆት እና የአጋርነት መልዕክት እየላኩም ቀልባቸውን ሳቧቸው፡፡
በመጨረሻም በ1934 ዓ.ም ርእሰ ብሔር ሩዝቬልት የአሜሪካ ሕዝብ ኢትዮጵያ በሞሶሎኒ በገጠማት ወረራ እንዳዘኑ እና ነፃነቷን መልሳ እስክታገኝ ድረስ በትብብር አብረው እንደሚሠሩ ቃል ገቡላቸው፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት መሻሻል እንደ መልካም ዕድል የወሰዱት ንጉሠ ነገሥቱ ርእሰ ብሔር ሩዝቬልትን በአካል የሚያገኙበትን ወቅት በትዕግስት ሲጠባበቁ ቆዩ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን የጥቁሮች ታሪካዊ ወር በሆነችው የካቲት የንጉሠ ነገሥቱ የዘመናት መሻት ዕውን ሆነ፡፡
አፄ ኀይለሥላሴ ከርእሰ ብሔር ሩዝቬልት ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት እንግሊዝ እንዳታውቅ ተብሎ በአንድ የአሜሪካ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ካይሮ በምሽት በረሩ፡፡
ንጉሠ ነገሥት አፄ ኀይለሥላሴ ለርእሰ ብሔር ሩዝቬልት ማንሳት የሚፈልጓቸው ስድስት የስትራቴጂክ አጋርነት ጥያቄዎች ነበሯቸው ይባላል፡፡ እነዚያን ስድስት ጥያቄዎች ይዘው በምሽት እና በድብቅ ካይሮ የገቡት ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ የካቲት 6/1937 ዓ.ም ርእሰ ብሔር ሩዝቬልትን በአሜሪካዊያኑ መርከብ ላይ በስዊዝ ካናል በሐይቅ ቢተር አገኟቸው፡፡
90 ደቂቃ በሐይቅ ቢተር በዘለቀው የሁለቱ መሪዎች ድብቅ ውይይት ንጉሠ ነገሥቱ ኢትዮጵያ በአዲሱ የተባበሩት መንግሥታት መሥራች ሀገር መካከል አንዷ እንድትሆን ተወያዩ፤ በዓባይ ወንዝ ላይ ጥናት ለማድረግ አሜሪካ እንድትተባበር እና ሌሎች አራት ጥያቄዎችን በማቅረብ እንደተነጋገሩ ይነገራል፡፡ የኋላ ኋላ ምንም እንኳን እንግሊዝ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ማሳደር ባትችልም የሁለቱ መሪዎች ዝግ ውይይት በካይሮ እስስቶቹ አማካኝነት ተነግሯቸው ነበር ይባላል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ርእሰ ብሔር ሩዝቬልትን አግኝተው በዓባይ ወንዝ ላይ ጥናት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ተከትሎም የያኔው ቦርደር ዳም የአሁኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥናት ከ1958 እስከ 1964 (እ.አ.አ) በአሜሪካዊያኑ ባለሙያዎች እንዲጠና መሰረት ጣለ፡፡ ሐይቅ ላይ ያውም በመርከብ ውስጥ የቀረበው ጥያቄ ከዘመናት በኋላ ሌላ ግድብ በሀገራቸው እንደሚወልድ ንጉሠ ነገሥቱ ያውቁ ነበር፡፡ ያ ጥናት ዘመናትን አልፎ ጊዜ እና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ግንባታው የተጀመረው ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ ኃይል ማመንጨት የጀመረው በያዝነው ዓመት በወርሃ የካቲት ነው፡፡
ምንጭ፡- ሃጋይ ኤርሊክስ (ኀይለሥላሴ አነሳሳቸው እና አወዳደቃቸው) መጽሐፍ
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ብልጽግና ትግል እና ለውጥ የወለደው ፓርቲ ነው” አቶ ብናልፍ አንዱዓለም
Next articleበኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይል በማዕከላዊ አየር ምድብ የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ እና በሥራ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የሠራዊት አባላት የማዕረግ ሹመት ተሰጠ።