“ውስጣዊ ሰላምና አንድነትን በማጠናከር ማንኛውንም ጥቃት መመከት የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር ይገባል” አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

198

የካቲት 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ በኅልውና ዘመቻው ለተፋለሙ ጀግኖች የእውቅናና ምስጋና መርኃግብር ትናንት ተካሂዷል። የወረዳው ሕዝብ ያለ በቂ መሣሪያ በድንጋይ ናዳ ጭምር ጠላትን ፊት ለፊት የገጠመ ጀግና ነው። መስዋእትነት ጭምር በመክፈል የአሸባሪውን ቡድን ከንቱ መሻት በተደጋጋሚ አክሽፎ አሳፋሪ ሽንፈት አከናንቦታል።

የወረዳው ተወካይ አሥተዳዳሪ መብራቱ አሰፋ በክብር የተሰው ጀግኖች ቤተሰቦችን ለመደገፍ የወረዳው ሕዝብ እና መንግሥት ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል። አቶ መብራቱ እንዳሉት የተጎጂ ቤተሰቦችን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ እና ጀግኖችን ለመዘከር ሁለገብ የገበያ አዳራሽ ለመገንባት ታቅዷል፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴም ተጀምሯል።

በመርኃግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ተገኝተው እንዳሉት በርካቶች ቤተሰባቸውን ትተው፣ የግብርና ሥራቸውን ጥለው ለሀገራቸው ቅድሚያ በመስጠት የአሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን እኩይ ዓላማ እንዳይሳካ ጀብድ እየሠሩ ታግለዋል።

በወረዳው ወረራ በተፈጸመ ጊዜም የመንግሥትን ንብረት ከጠላት በመሸሸግ፣ ለጠላት መረጃ ባለመስጠት ያለውን ጥላቻ በግልጽ አሳይቷል፣ በቻለው አቅም ሁሉ ታግሏል። ትግሉ ፍሬ አፍርቶ ከአብዛኛው አካባቢዎች ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደርጓል። በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሰላም አየር መተንፈስ ተጀምሯል ብለዋል።

አቶ ገዱ የኢትዮጵያን ኅልውና ለማስቀጠል የሕይወት መስዋእትነት ለከፈሉ ጀግኖች ተገቢውን ክብር እንሰጣለን ነው ያሉት። የአማራን ሕዝብ ከውርደት፤ ኢትዮጵያንም ከመፍረስ ለመታደግ ሲባል በተከፈለው መስዋእትነት ጠላት አፍሯል ያሉት አማካሪ ሚኒስትሩ ጀግኖች በታሪክ ሲዘከሩ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ትግሉ ገና አላለቀም፤ አሁንም ከፊት ለፊት ትግል ይኖራል ብለዋል። በተለይ በኢኮኖሚ መስክ ድህነትን መዋጋት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በአጽንኦት አስገንዝበዋል። ማንኛውንም ፈተና ለመቀልበስ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ወሳኝ ነው። በተለይም በወረራው የደረሰውን ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ለማካካስ በአንድ በኩል ልማትን ማፋጠን ይጠበቃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ውስጣዊ ሰላምና አንድነትን በማጠናከር ማንኛውንም ጥቃት መመከት የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ እንደኾነ አቶ ገዱ አስረድተዋል።

በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች የደረሱ ውድመቶችን መልሶ ለመገንባት እና የተጎጂ ቤተሰቦችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ገልጸዋል። በሂደቱ ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ምንም እንኳን የጦርነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ቢጠናቀቅም አሸባሪው ቡድን ከእነ አስተሳሰቡ እስኪጠፋ ብዙ ፈተናዎች ይጠብቁናል። አንድነት፣ መናበብ፣ የውስጥ ሰላምን ማስቀጠል እና ፈተናን ለመጋፈጥ ዝግጅት ማድረግም ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለተጎጂ ቤተሰቦች ቋሚ የገቢ ማስገኛ ከመሥራት ባለፈ በቋሚነት የሚታወሱበት በስማቸው የሚጠራ ቤተ መጽሐፍት እንዲገነባም ሐሳብ አቅርበዋል።

በመርኃ ግብሩ የተገኙ ዘማቾችና የዘማች ቤተሰቦች ኀይልን ማጠናከር፤ ዓላማን አንድ አድርጎ መታገል ከተቻለ ሕዝብን ማንም አይደፍረውም ብለዋል። በአማራ ሕዝብ እና በሀገሪቱ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን መክቶ ሀገር ያጸና ባለ ታሪክ ሕዝብ መኾኑን የተናገሩት ዘማቾችና የዘማች ቤተሰቦች የውስጥን ተላላኪን በማጽዳት ጠላት እስከወዲያኛው አንገቱን እንዲደፋ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።

የወረዳው ሕዝብ የረጅም ዘመናት የተጋድሎ ታሪክ እንዳለው በማንሳት ታሪኩ በተገቢው መልኩ እንዲጻፍና ለተተኪ ትውልድ መማሪያ እንዲሆንም ሐሳብ አቅርበዋል።

ጀብድ ፈጽመው ላለፉ እና በጀግንነት ለተፋለሙ እውቅና መሰጠቱ ጥሩ ጅምር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ-ከዳውንት

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleʺየተከዜ ዳር ማዕበሎች፣ የበረሃ መብረቆች”
Next articleፋሲል ከነማ እና ዳሽን ቢራ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውል ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አራዘሙ፡፡