
ባሕር ዳር: የካቲት 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “ከግዛቴ ቆርሰው ለመውሰድ ከማይመኙ ሀገራት ጋር ሁሉ ግንኙነት ለመፍጠር የምናፍቀው ነገር ነው” ዳግማዊ አጼ ምኒልክ
አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ተብለው በ1882 ዓ.ም ተቀብተው ከመንገሳቸው በፊት መሳሪያ ለማግኘት ሲሉ ከጣሊያኖች ጋር በስፋት ሲሠሩ እንደቆዩ የታሪክ ተመራማሪዎች ጽፈዋል። ምኒልክ ከእርሳቸው በፊት የነበሩትን የአጼ ዮሐንስን ብሔራዊ ፖሊሲዎች እና የአመራር በተለይም የውጭ ፖሊሲን በተግባር አልደገፉም። ይልቁንም በአውሮፓውያን የሃይማኖት፣ የንግድ እና የፖለቲካ ወኪሎች ብግብጽ ጳጳስ አቡነ ማቲያስ፣ በእነ አንቶኔሊ እና በእነ አልፍሬድ ኤግል ፖለቲካዊ ምክር እና ድጋፍ በታጅራና የአሰብ የንግድ በሮች በኩል የአጼ ዮሐንስን የውጭ ፖሊሲ በተግባር በተጻረረ መልኩ ከአውሮፓውያን ጋር በተለይም ከጣሊያን መንግሥት ጋር የውጭ ግንኙነት ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983” በሚል ርእስ 2007 ዓ.ም ላይ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ሁኔታውን በዝርዝር ሲገልጹ “አጼ ምኒልክ ከውጫሌ ውል በፊት ሁለት ውሎችን ከጣሊያኖች ጋር ፈጽመዋል። የመጀመሪያው ውል በ1875 ዓ.ም የተፈጸመ ሲሆን ትኩረቱም በቆንስላ ልውውጥ፣ ነጻ ንግድ፣ የዜጎች በሌላ ሀገር በነጻ መንቀሳቀስ እና የሃይማኖት ስብከት ላይ ያተኩሩ ነበሩ።
ሁለተኛው ስምምነት በ1880 ዓ.ም የተደረገ ሲሆን ጣሊያኖች በዶጋሊ ጦርነት ተሸንፈው በአጼ ዮሐንስ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ በሚዘጋጁበት ወቅት በመሆኑ ምኒልክ ገለልተኛ እንዲሆኑ ለማግባባት የተደረገ ስምምነት ነው” ሲሉ ይገልጹታል።
አጼ ዮሐንስ መሞታቸው እንደተሰማ የሽዋው ንጉስ ምኒልክ እንደሚነግሱ ያወቀው የጣሊያን መንግሥት በኤርትራ የያዛቸውን ቦታዎች ለማጽናት ወዳጅ መስሎ ቀረበ። ጣሊያኖች የተሻለ ጊዜ እስኪመጣም ከአዲሱ የአጼ ምኒልክ መንግሥት ጋር መሥራት እና መስማማት የተሻለ እንደሆነ አመኑ። በሚያዚያ 1881 ዓ.ም ወሎ አምባሰል ላይ በመልዕክተኛቸው በኮንት አንቶኔሊ አማካኝነት የውጫሌ ስምምነት እንዲፈረም አደረጉ።
አጼ ምኒልክም መንግሥታቸውን እስኪያጸኑ የሀገሪቷን ሉዓላዊነት የሚገዳደር ኀይል ለማስወገድ በመፈለጋቸው ከጣሊያን መንግሥት ተወካይ ጋር “የውጫሌ ስምምነት” በመባል የሚታወቀውን እና አወዛጋቢውን ስምምነት ተፈራረሙ። ነገር ግን ወደ ሽዋ እንደተመለሱ የውሉ 17ኛው አንቀጽ የአማርኛው እና የጣሊያንኛው ቅጅ የትርጉም መዛባት ችግር እንዳለበት አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ በተባሉ ቋንቋ አዋቂ እና የጅቡቲ አምባሳደር አማካኝነት ተረዱ።
የዚህ አንቀጽ የአማርኛ ትርጓሜ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓ ነገስታት ጋር ለሚያደርገው ጉዳይ ሁሉ በጣሊያን መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል” የሚል ሲሆን፤ የጣሊያንኛው ትርጉም ግን “የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓ ነገስታት ጋር የሚያደርገው ጉዳይ ሁሉ በጣሊያን መንግሥት በኩል መሆን ይገባል” የሚል ነበር። ይህን ልዩነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማስታረቅ ባለመቻሉ የኋላ ኋላ ጉዳዩ ለዓድዋ ጦርነት መንስኤ ሆነ።
የጣሊያን መንግሥት አጭበርባሪነት ከውጭ ግንኙነት ፋይዳ አኳያ ሲታይ መሠረታዊ ችግር ያለበት ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ መጣስም ነበር። ውጤቱም ጦርነት እስከማማዘዝ መድረሱ አስገራሚ አልነበረም። አጼ ምኒልክ ውሉን ሲፈራረሙ ሉዓላዊነትን ላለማስደፈር በማሰብ ቢሆንም ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆነባቸው። በዚህም የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ጉልበት ሳይጠና ወደ ጦርነት ለመግባት ተገደዱ።
ፕሮፌሰር ላጲሶ ድሌቦ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዳአማት እስከ አዲስ አበባ” በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚሉት “በ1886 ዓ.ም የውጫሌ ውል መሠረዙን አጼ ምኒልክ ለዓለም በይፋ ባሳወቁበት ወቅት የፈረንሳይ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሟል” ይሉናል። የውጫሌ ውል መሠረዝን ምክንያት አድርጎ ከተነሳው የአድዋ ጦርነት በፊት ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በሕዳር 1888 ዓ.ም በአምባላጌ እና በመቀሌ እንዳየሱስ ምሽግ ተዋግተው ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከዚያም በጥቁር ሕዝብ ታሪክ ትልቁ እና የመጀመሪያው የነጭ እና የጥቁር ጦርነት የሚባለውን የአድዋ ጦርነት የካቲት 23/1888 ዓ.ም ተደረገ። ጦርነቱ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በኢትዮጵያ ሠራዊት ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ። አጼ ምኒልክም በውጫሌ ውል ስምምነት ምክንያት ሊደፈር የተቃጣውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በኀይላቸው ማስጠበቅ ቻሉ።
በአጼ ምኒልክ ዲፕሎማሲ ሌላው ጎልቶ የወጣው ጉዳይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ከሌሎች ሀገራት ጋር ጠንካራ አጋርነትን መፍጠር መቻላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በአድዋ ጦርነት ወቅት የእንግሊዝ መንግሥት የጣሊያን አቻውን ሲደግፍ የፈረንሳይ፣ የቱርክ እና የሩሲያ ኀያላን ሀገራት መንግሥታት ግን የእንግሊዞችን እና የጣሊያኖችን ጥምረት እና ጥቅም ለማዳከም ሲሉ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ እና በጦር መሳሪያ ድጋፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ነጻነት እና አንድነት ደጋፊዎች ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያም ባገኘችው ዲፕሎማሲያዊ ድል እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ1889 እስከ 1896 ድረስ ለአድዋ ጦርነት ስትዘጋጅ ከላይ ከተጠቀሱት አውሮፓዊያን ሀገራት የጦር መሳሪያ ድጋፍ አግኝታለች፡፡
አጼ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት የጣሊያንን ወራሪ ኀይል ዓለም ባልጠበቀው ሁኔታ አንድ ቀን እንኳን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብትንትኑን በማውጣት ታሪክ ሊዘነጋው የማይችል ደማቅ ድልን ተጎናጽፈዋል፡፡ ከድሉ ጋር ተያይዞ አጼ ምኒልክ የጠላትን ምርኮኛ ወታደሮች አክብረው እና ጠብቀው ይዘው ማቆየታቸውን ብዙ የታሪክ ልሂቃን ጽፈውታል፡፡ ከአድዋ ጦርነት ሽንፈት ማግስት ጣሊያን ብዙም ሳትቆይ ከኢትዮጵያ ጋር እርቅ ለማወረድ በመጠየቋ አጼ ምኒልክ እርቅ ማውረድ ብቻ ሳይሆን የውጫሌን ውል የሚሽር ሌላ ውል ጣሊያን እንድትፈርም ካደረጉ በኋላ ምርኮኞቹን በምህረት ለቀዋቸዋል፡፡ ይህም በዚያ ዘመን ሳይቀር አጼ ምኒልክ የዓለም አቀፍ የጦር ምርኮኞችን አያያዝ ሕግ ያከበሩ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በቀለኛ አለመሆናቸውን እና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መካኒክ መሆናቸውን ያሳያል፡፡
ሌላው የአጼ ምኒልክ የዲፕሎማሲያዊ የበላይነት፣ በራስ መተማመን እና መካኒክ መሆናቸውን የሚያሳይ ማሳያ አለ፡፡ ከአድዋ ጦርነት ሽንፈት በኋላ እንኳን የአውሮፓዊያን ድብቅ ሴራ አልተቋረጠም ነበር፡፡ ታኅሣሥ 5/1889 ዓ.ም የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ እና የጣሊያን መንግሥታት ኢትዮጵያን አግልለው ቀጣናውን የሚመለከት ውል ከተዋዋሉ በኋላ ግልባጩን ለአጼ ምኒልክ ላኩላቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ውሉን ተመልክተው ምንም እንኳን ስምምነቱ ከጅቡቲ አዲስ አበባ የሚዘረጋውን የባቡር መስመር እውቅና መስጠቱ ቢያስደስታቸውም ተዋዋይ ወገኖች እርሳቸውን ሳያካትቱ የተስማሙበትን ውል ሀገራቸው ለመቀበል የሚያስገድዳት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ እንቅጩን ነገሯቸው፡፡ በዚህም እንደ አንድ ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር ማመናቸው ብቻ ሳይሆን እነርሱንም እንዲያምኑ ማስገደዳቸው የምኒልክን የዲፕሎማሲያዊ ብልጫ አጉልቶ ያሳያል፡፡
አጼ ምኒልክ ከአደዋ ጦርት መልስ በውጭ ግንኙነታቸው ሀገራቸውን ዙሪያዋን ከከበቧት የአውሮፓ ኀያላን ጋር በመታገል እና የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቀው ለመጓዝ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ንጉሡ ከጎረቤት ቅኝ ገዥዎች ጋር በሚያካሂዱት የውጭ ግንኙነት ሁሉ እጅግ የላቀ ጥንቃቄን ያደርጉ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡ የጥንቃቄያቸው ምክንያት ደግሞ ሁለት አንኳር ነጥቦችን ያቀፈ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ሀገራቸው በወቅቱ በአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ዙሪያዋን ተከባ ብቸኛ ነጻ እና ሉዓላዊት ሀገር በመሆኗ ፈላጊዎቿ በርካታ እንደነበሩ ያውቃሉ፡፡ ሁለተኛው የመጀመሪያው ወረራ ጣሊያን በእንግሊዝ እርዳታ በኤርትራ በኩል እንድትገባ ስለፈቀደች የተፈጠረ ነበርና ሊተባበሩ ቢችሉ የሚፈጠረውን ብሔራዊ ስጋት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ለዚያም ሲባል ከአንደኛው ጋር ወግነው ሌላኛውን አስከፍተው ከመጓዝ ይልቅ ሚዛን መጠበቅ የተሻለ እንደነበር አምነዋል፡፡
የአድዋ ጦርነት ድል ውጤት ዘርፈ ብዙ፣ እስከዚህ ትውልድ የደረሰ እና ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች አብዮት መነሳት ምክንያት ነው የሚሉት ብዙ ናቸው፡፡ ከትሩፋቶቹ መካከል አንዱ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያስገኘው ዓለም አቀፋዊ ቅቡልነት ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡ ከድሉ ማግስት ጀምሮ ራሷን ተሸናፊዋን ጣሊያንን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት እና ኢምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ለመክፈት ሲሯሯጡ ተስተውሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን በአካባቢው በቅኝ ግዛት በያዟቸው አካባቢዎች በፍጥነት ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር መካለል መፈለጋቸውም እንዲሁ ታይቷል፡፡
የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን ለማጠናከር አጼ ምኒልክ ከድሉ በኋላ በ1900 ዓ.ም የውጭ ግንኙነት ፈጻሚ መስሪያ ቤት ማቋቋማቸው ዓለም ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ እንዳዞረ አመላካች ሆኖ ታይቷል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከአውሮፓ ኀያላን ጋር የሚያደርጉትን የውጭ ግንኙነት ሥራ የልዑካን ቡድኖችን ወደ ውጭ በመላክ ያጠናክሩም ነበር፡፡ ጣሊያን፣ እንግሊዝ እና ሌሎች የአረቡ ዓለም ሀገራት ምኒልክ ቀደምት ልዑካንን ከላኩባቸው አካባቢዎች ማካከል እንደሆኑ ይነገራል፡፡
አጼ ምኒልክ በዘመናቸው ከውጭ መንግሥታት ጋር ለሚያደርጓቸው ግንኙነቶች የማይታለፍ መርሕ አድርገው የያዙት የሀገር ዳር ድንበር መከበርን ነው፡፡ ለዚህ እንደማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው የምኒልክ ወዳጅ ዊሊያም ኤሊስ የአሜሪካ መንግሥት መልዕክተኛ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ላይ መሆኑ ሲነገራቸው በደስታ “ከግዛቴ ቆርሰው ለመውሰድ ከማይመኙ ሀገራት ጋር ሁሉ ግንኙነት ለመፍጠር የምናፍቀው ነገር ነው” ማለታቸው ይጠቀሳል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ በውጭ ሀገሮች የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች” በሚል ርእስ በሳተሙት መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት አጼ ምኒልክ በንግስና ዘመናቸው ከውጭ ሀገራት መንግሥታት ጋር ከ750 በላይ ደብዳቤዎችን መጻጻፋቸውን ጠቅሰው 404 ከፈረንሳይ፣ 127 ከጣሊያን፣ 82 ከእንግሊዝ እና በጥቅሉ ከ25 ሀገራት ጋር መልዕክቶችን ተላልከው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የመልዕክቶቹን ጭብጦች ሲያስቀምጡም የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማሻሻል፣ የድንበር ጉዳይ፣ ወደብ፣ ጦር መሳሪያ ሽያጭ፣ በይለፍ ፈቃድ፣ በንግድ፣ በባቡር መንገድ ግንባታ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ስጦታዎችን መለዋወጥ እና ምስጋና መቀያየር ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
በመጨረሻም የዲፕሎማሲው መካኒክ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ጣሊያን በ1904 ደግሞ ከአሜሪካ ጋር በተደረገ ስምምነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ይፋዊ እውቅና እንዲሰጡ ማድረግ ችለዋል፡፡
የአድዋ ጦርነት የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መደምደሚያ እንጂ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩበት ምክንያት ጭብጥም ይህ ነበር፡፡
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/