የዓድዋ ድል በዓል በልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።

114

የካቲት 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) 126ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፣ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል።

በዓሉን በፌዴራል ደረጃ በድምቀት ለማክበር የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ገልጸዋል።

በዓሉን በደመቀ ሁኔታ በመላ ሀገሪቱ ለማክበር የሰላም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማኅበር፣ የቅርስ ባለሥልጣን፣ መከላከያ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት የተካተቱበት ዐቢይ ኮሚቴ፣ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው እንቅስቃሴ እያደረጉ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲኾን የሀገር ውስጥ ምሁራን የሚሳተፉበት ሲምፖዚየም እንዲሁም የውጭ ዲፕሎማቶችን እና ዲያስፖራውን የሚያሳትፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሲምፖዚየምም እንደሚኖርም አመልክተዋል።

ኤግዚቢሽኖች እና የስፖርት ኹነቶች መዘጋጀታቸውንም ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ የፈረስ ትርዒቶችም የበዓሉ ድምቀቶች እንደሚኾኑ ተናግረዋል።

በዓሉ በክልል ደረጃም ተመሳሳይ ዝግጅት ተደርጎ እንደሚከበርም ጠቁመዋል።

ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካውያንም ትልቅ በታሪክ የተመዘገበ ድል ነው ያሉት አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ የዓድዋ ጦርነት በተደረገበት ወቅት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ወደ አፍሪካ ተስማምተው የዘመቱበት እና አብዛኛዎቹን የአፍሪካን ሀገሮች መቆጣጠር የቻሉበት ቢኾንም በኢትዮጵያ ያልጠበቁትን ሽንፈት ተከናንበው የተመለሱበት መኾኑን አስታውሰዋል።

የተገኘው ድል በወቅቱ ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ የጦር መሳሪያ ባትታጠቅም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የዳበሩ የውጊያ ስልቶች እና በሌሎች ዘንድ ያልተለመደውን የፈረስ ውጊያ ስልቶችን በመጠቀም የተገኘ ትልቅ ድል መኾኑን ተናግረዋል።

ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ኹሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ልምድ እና ችሎታ በመጠቀም በጋራ እና በአንድነት ቆመው ጦርነቱን ማሸነፍ ችለዋል ብለዋል።

አቶ ቀጄላ እንዳሉት ወጣቶች ከዓድዋ ድል ሀገር ወዳድነትን እና ለሀገር ነጻነት መቆምን መማር ይኖርባቸዋል።

በዓሉን ወጣቶችና ኹሉም ሕዝብ በነቂስ በመውጣት እንዲያከብርና ለበዓሉ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽንም እንዲጎበኝ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article❝በአሸባሪ ቡድኖች የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም የእህትማማች ከተሞች ትስስር መፈጠሩ ለጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ለከተሞች በፍጥነት መልሶ መገንባት ያግዛል❞ የከሚሴ ከተማ አስተዳደር
Next article❝እንኳን ለዐቢይ ጾም አደረሳችሁ❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)