
ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2012 ዓ/ም (አብመድ) የከባድ ጭነት ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት አጄንሲ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጄንሲ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚፈጥሩትን የእንቅስቃሴ ተፅዕኖ ለመቀነስ መመሪያ አዘጋጅቶ ተግባራዊ አድርጎ ነበር፡፡ የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ጅሬኛ ሂርጳ (ኢንጂነር) እንዳስታወቁት የከተማዋን ትራፊክ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
በተሻሻለው መመሪያ መሠረትም ማንኛውም የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ከጠዋቱ 12፡30 እስከ 4፡00 እና ከቀኑ 10፡00 እስከ ምሽቱ 2፡00 ካለው ጊዜ ውጪ መንቀሳቀስ የሚፈቅድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የከባድ ጭነት ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 4፡00 እስከ ቀኑ 10፡00 ድረስ በከተማዋ ውስጥ መዘዋወርና ማንኛውንም አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ቅዳሜ፣ እሑድ እና በበዓል ቀናት ማንኛውም የጭነት ተሽከርካሪ ያለምንም የሰዓት ገደብ መንቀሳቀስ እንዲሁም ዕቃ መጫንና ማራገፍ እንደሚችሉ ኢንጂነር ጅሬኛ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የከተማዋ ትራፊክ ፖሊስና የደንብና ቁጥጥር አካላት የተደረገውን ማሻሻያ በመረዳት እንደወትሮው ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ በከተማዋ ውስጥ ሠላማዊና ምቹ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ጥረት እንዲያደርጉ ዋና ዳሬክተሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን አዲስ ዘመን ዘግቧል፡፡
ኤጄንሲው የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓትን የሚያሻሽል የጭነት፣ የማሽነሪዎችና መሰል ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ለመወሰን የወጣውን መመሪያ ቁጥር 03/2011 መነሻ በማድረግ በከተማዋ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ ለመቀነስ መመሪያ አዘጋጅቶ ከሰኔ 30/2011 ዓ.ም ጀምሮ በተግባር ላይ ማዋሉ ይታወሳል፡፡