
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ታላላቅ ታሪኮች እንደ ጅረት እና ኩረት ተዋህደው የገነቧት የታሪክ ማኽደር ናት-ኢትዮጵያ፡፡ ታሪክ የአንድን ሕዝብ ያለፈ ሁነት ብቻ የሚያወሳ እና ወደ ኋላ ተጠምዝዞ የቆመ ሳይሆን ወደ ፊት ስለሚሆነው ፍንጭ የሚሰጥ እና የሚያስተምር የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ዘርፍ ነው፡፡
ታሪክ ያለፈውን ነገር እንደወረደ የሚያወሳው አንድም ያለፈን መልካም ነገር ጠብቆ ለማቆየት ሌላም ካለፈ ስሕተት ለመማር ነው፡፡ በርካታ ሀገራት በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረን መልካም ወይም መጥፎ ክስተት የታሪካቸው አንድ አካል አድርገው እንደነበር ይቀበሉታል እንጂ አያጠፉትም፡፡ በመልካም የታሪክ ትሩፋቶቻቸው እየኮሩ ከአሳዛኝ የታሪክ አጋጣሚዎቻቸው እየተማሩ ለሌላ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ራሳቸውን እና ትውልዱን ያዘጋጃሉ፡፡
እነዚህ ሀገራት ያለፈ ጊዜ የታሪክ ተወቃሽ ወይም ተሞጋሽ ለመሆን በቅድሚያ ታሪኩ ተጠብቆ እና በትውልድ እየታወሰ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ የደረሱ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ የሚመዘዝ በርካታ መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ እና ተፈጥሯዊ ታሪክ አላት፡፡ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን ጠብቀው እና በየዘመናቸው አዳዲስ ታሪኮችን እያስመዘገቡ አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዘመን ሽግግር ክስተት በሆነው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ዑደት መካከል የታሪክ አሻራ ያልነጠፈባት ሀገር ናት፡፡
ከቅርብ ዘመን ጀምሮ ብቅ ብቅ ያለው የምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብ በነባሩ የታሪክ አረዳዳችን እና አቀባበላችን ላይ ዓሉታዊ ተፅዕኖ ሳያሳድር አልቀረም ብለው የሚያስቡ በርካቶች ናችው፡፡ በተለይም ደግሞ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ እንደወረርሽኝ እየተስፋፋ የመጣው ጎሳ ተኮር ፌዴራሊዝም በታሪክ አረዳድ ላይ ከቅርብ ዘመን ያልዘለለ እና ከመንደር ያልተሻገረ ዕሳቤ እንዲኖር አድርጓል ይባላል፡፡ ለዚህ ሲባል ደግሞ ትውልዱ ሆን ተብሎ ታሪኩን መርሳትን እንደተለማመደም ይጠቀሳል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የሥልጣን ዘመን ትውልዱ ሆን ተብሎ ታሪኩን እንዲረሳ ተደርጓል ያሉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶክተር) ናቸው፡፡ አንድ ሕዝብ የረጅም ዘመን ታሪኩን ሲያወሳ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ዕሳቤ ያዳብራል ያሉት ዶክተር ዳኛቸው ይኽ ደግሞ ለአምባገነን እና ጥቅመኛ መሪዎች አይመችም ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ሲባል ትውልዱ ሆን ተብሎ ታሪኩን መርሳት እንዲለማመድ ተደርጓል ባይ ናቸው፡፡
ታሪክ ሕያውነት ስላለው ተንቀሳቃሽ ነው የሚሉት ዶክተር ዳኛቸው ተንቀሳቃሽ ስለሆነም ያለፈው ታሪክ ከሚመጣው አዲስ ትውልድ ጋር ግንኙነት አለው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ታሪኩን ከማውሳት እና ከማስተላለፍ በተጨማሪም ታሪክ የሚቀርብበት እና የሚመዘገብበት መንገድ አብሮ መጤን አለበት ብለው ያምናሉ፡፡
ዶክተር ዳኛቸው ዕውቁን ጀርመናዊ ፈላስፋ ፍሬዴሪክ ኒቼን ዋቢ አድርገው ታሪክ በሦስት መንገድ ለትውልድ ይተላለፋል ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው የታሪክ አመዘጋገብ ትምሕርት የምንቀስምበት ጀግንነት፣ ታላቅነት፣ ሞራል እና ወኔ ቀስቃሽ ሂደትን የሚከተል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ወግ አጥባቂ የሚባል፣ ያለፈውን ሥርዓት በእንክብካቤ የሚይዝ እና አይተችም፣ አይነቀፍም እና አይነቀስም የሚባልለት ሂደት ነው ይላሉ፡፡
ከሦስተኛው ግን በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን ልንጠነቀቅበት የሚገባ ነው የሚሉት የፍልስፍና ምሁሩ ያለፈውን በመርገም ላይ ያተኮረ፣ ከባዶ መጀመር እና ያለወፈውን ስሕተት ነቅሶና መርምሮ ማውጣት ላይ የተጠመደ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶክተር ዳኛቸው ገለጻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ከባዶ ለመጀመር የሚፈልጉት በዝተው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ዳኛቸው እንደሚሉት ይኽ ትውልድ አድዋን ሲያወሳ እና ሲዘክር የአባቶቹን ተፈጥሯዊ ጽናት፣ የጠለቀ እምነት፣ አይበገሬነት፣ መስዋእትነት እና ከፍተኛ የሆነ የሀገር ፍቅር ስሜት እያሰረጽን ነው፡፡ ይኽ እኩል የማያስማማው ኢትዮጵያዊ ቢኖር እንኳን የጣሊያን ግፍ፣ በደል እና በጥቁር ሕዝቦች ላይ የነበራቸው ጥላቻ ያግባባናል ነው ያሉን፡፡
“ታሪኩን የማያስታውስ ሕዝብ ለመገዛት ይመቻል” ያሉት የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ልክ እንደ አባቶቹ ለሀገር ውጭ መሰሪ የማይበገር ትውልድ እና ለአምባገነን መሪዎች የማይመች ማኅበረሰብ ለመፍጠር አድዋ መዘከር ታሪክን ከመርሳት ይታደጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
Amhara Media Corporation – YouTube
youtube.com
