
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ቀናት በወራት፣ ወራትም በዓመታት እየተሻሩ ዘመን እንደ ጅረት ነጎደ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ግን ዛሬም እንደ አዲስ ይነገራል፤ ይጻፋል፤ ይደመጣል፡፡ እነሆ ከ126 ዓመታት በፊት በታሪካዊቷ ምድር የተፈጸመ ታላቅ ጀብድ ዛሬም ከአድማስ ባሻገር እንደ ፀሐይ ደምቆ ይታያል፡፡
ቀደም ብሎ በ1881 ዓ.ም በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት በሆነች ሀገር እና በወራሪዋ ኢጣሊያ መካከል የመጀመሪያው ሕጋዊ ስምምነት ውጫሌ ላይ ተፈረመ፡፡ የዚህ ስምምነት አካል የሆኑ አንቀጾች በጠነሰሱት ሴራ ኢትዮጵያ እና ጣልያን አይቀሬ ወደነበረው ጦርነት አመሩ፡፡ እናም ከሰባት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1888 ዓ.ም የአፍሪካ ትልቁ ጦርነት በሰሜን ኢትዮጵያ ዓድዋ ምድር ላይ ተካሄደ፡፡
የዓድዋ ጦርነት ሲታወስ የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩት ጀግና ኢትዮጵያዊ ስም ይጠቀሳል፡፡ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ የውጫሌ ውል ጣልያንኛ ትርጉም ኢትዮጵያን ጥገኛ በማድረግ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ቀድመው የተረዱ ታላቅ ሊቅ ናቸው፡፡ እኝህ ሊቅ አጤ ምኒልክ የውሉን ይዘት እንዲመረምሩ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሠረት 17ኛው አንቀጽ ትርጉሙ የተዛባ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ እና ሉዓላዊነቷን የሚዳፈር መሆኑን ቀደም ብለው በምስጢር ለንጉሠ ነገሥቱ እና ለእቴጌ ጣይቱ አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ ለትምሕርት ተብሎ ወደ ጣልያን ተልከው የነበሩት አፈወርቅ ገብረየሱስም ጣልያን ውስጥ ታትመው የተሰራጩ ጋዜጦችን አንብበው ስህተት መኖሩን ተገንዝበዋል፤ ይህንን ስህተት በወቅቱ የኢትዮጵያን ልዑክ ይዘው ወደ ጣልያን ለተጓዙት ራስ መኮንን ወልደሚካኤል እዛው ጣሊያን አግኝተው አብራርተውላቸዋል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግም ራስ መኮንን ለጣልያን መንግሥት ቁጣ የተቀላቀለበት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡
በስምምነቱ ወቅት የነበሩት ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤም የጣልያንን ድብቅ ሴራ ከተገነዘቡት መካከል አንዱ ናቸው ተብሎ ይነገራል፡፡ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ ግን ሴራውን በመረዳት ቀዳሚው ናቸው ነው የሚባለው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የጣልያንን ስውር አጀንዳ የተረዱ ኢትዮጵያውያን ለንጉሡ እና ለንግሥቲቱ በተደጋጋሚ ይነግሯቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አጤ ምኒልክ በአንድ በኩል መንበረ መንግሥታቸው እንዳይናወጥ በሌላ በኩል ደግሞ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት እንዳይሻክር በማሰብ ነገሮችን በጥንቃቄ ነበር የሚከታተሉት፡፡ የትርጉም ስህተት መኖሩን በተገነዘቡ ጊዜ እንኳን ነገሮችን ለማመቻቸት ጥበብ የተሞላበት አካሄድን መርጠዋል፡፡ የሚደርሳቸውን ምስጢራዊ መረጃ በአጽንኦት እየተመለከቱ ከኢጣልያ ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ለማስመሰልም ጥረት አድርገዋል፡፡ ጣልያኖችም ዓይናቸውን በጨው አጥበው ንጉሠ ነገሥቱን ለማግባባት ጥረት ሲያደርጉ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠልሸት እየሠሩ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ርምጃ እንዲወስዱባቸው ሀሰተኛ ክስ ማቅረባቸውን ተከትሎም በቤተ መንግሥት እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡
አለቃ አጽመጊዮርጊስ ግን የውሉን ትርጉም ቀድመው መገንዘባቸው ሁኔታዎችን መልክ ለማስያዝ ጠቃሚ ግብዓት ሆኗል፡፡ ስምምነቱን የማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀመርም አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡
የውጫሌ ውል ያስከተለው ዳፋ ለነገሮች ጠንቃቃ መሆን፣ ነገሮችን በስክነት መመልከት እና ሁል ጊዜም ዝግጁ መሆን እንደሚገባ ይሰብካል፡፡ ሴራዎችን ማጋለጥ፣ በሀገርና በሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችልን ጥቃት ለመከላከል ትውልዱ ከአለቃ አጽመ ጊዮርጊስ ታሪክ ሊማር ይገባል፡፡ ጣልያን ውስጥ ይማሩ የነበሩት አፈወርቅ ገብረየሱስም የጣልያንኛ ቋንቋ እውቀት እንደሌላቸው በመግለጽ ለማድበስበስ ጥረዋል፡፡ ሆኖም አጤ ምኒልክ ጉዳዩን በጥንቃቄ መርምረዋል፡፡ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ ነገሮች በጊዜያቸው ግልጽ እየሆኑ አለመግባባቱም እየጠነከረ ሄዶ አይቀሬው የጦርነት ጊዜ ተቃረበ፡፡
ፍትሐዊ ጦርነት ያደረገችው ኢትዮጵያ የድሉ ባለቤት ሆና የዓለምን ታሪክ ቀየረች፡፡ በእብሪት ተነሳስተው ኢትዮጵያን በቅኝ ሊገዙ ምድሯን የረገጡ የጣልያን ወራሪዎች በጦርነቱ ተሸንፈው በዓለም አደባባይ ተዋረዱ፡፡ ኢትዮጵያውያን “እጄን ሳልንተራስ፣ በገላዬ ላይ አፈር ሳይፈስ የኢትዮጵያን ክብር አሳልፌ አልሰጥም” ብለው ተማማሉ፡፡
እነሆ ለቀሪው ትውልድ መመኪያ ይሆን ዘንድ በየዘመኑ አድማሳትን ተሻግሮ እንደ አዲስ የሚተረክ የጀግንነት ታሪካቸውን በወርቃማ ብዕር ከትበው በክብር አኖሩ፡፡ ይህ ድል ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ፣ ስለማንነታቸውም እንዲያስተጋቡ ያደረገ ታላቅ ድል ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከማስከበር አልፈው በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ወድቀው ለነበሩ ጭቁን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የተስፋ ብርሃን የፈነጠቁበት የነጻነት አልፋና ኦሜጋ የዓድዋ ድል ነው፡፡ በጀግንነት ያኖሩት የማይደበዝዝ አሻራ ሰብዓዊነትን በውል ለማያውቁ ፍጡራን በቂ ትምሕርት የሰጠ የዚያ ዘመን ፍኖትም ነው፡፡
የዓድዋን ድል ተከትሎ የኢትዮጵያ አርበኞች የአሸናፊነት ጥበብ እና የንጉሰ ነገሥቱ በሳል የመሪነት ሚና ከአድማስ ባሻገር ከፍ ብሎ ተደመጠ፡፡ የጣልያን መንግሥት የፈጸመውን የወረራ እቅድ ቀድመው ይቃወሙ የነበሩ የጣልያን ዜጎችም በሮማ አደባባይ ወጥተው ቪቫ ምኒልክ ቪቫ ጣይቱ ብለው ድምጻቸውን ሲያሰሙ የቀደማቸው አልነበረም፡፡ ጣልያን ገና በጠዋቱ ወደ ኢትዮጵያ የወረራ ጉዞዋን የጀመረችው በሽንፈት ነው፡፡ ዶጋሊ ላይ የመረብ መላሹ ገዢ አሉላ አባ ነጋ 505 የጣልያን ወታደሮችን ለመርዶ ነጋሪ እንኳን ሳያስተርፍ ድባቅ በመምታት ወደ መቃብር አውርደዋቸዋል፡፡ በዚህም አሉላ አባነጋ ተጨማሪ የጦር መሣሪያና ስንቅን ማርከዋል፡፡ እናም ጠላት አድዋ ላይ ሲመጣ ከዶጋሊ የተማረከው የጦር መሣሪያ ከሀበሻ ጦርና ጎራዴ ጋር ተደምሮ ሞታቸውን ለማፋጠን አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ከአድዋ ጦርነት አስቀድሞ አምባላጌና መቀሌ ላይ ጦርነቶች ተካሂደው እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል፡፡ የጣልያን ጦር አምባላጌ ላይ ሽንፈትን ካስተናገደ በኋላ ወደ ኋላ አፈግፍጎ መቀሌ ላይ መሸገ፡፡ በራስ መኮንን የተመራው የኢትዮጵያ ጦር ምሽጉን ከብቦ ከኋላ የሚመጣውን የንጉሠ ነገሥቱን ጦር ይጠባበቅ እንደነበርም ይነገራል፡፡ በዚህ ጊዜ ራስ መኮንን ከጣልያኑ ተወካዮች ጋር ደብዳቤዎችን ይለዋወጡ ስለነበር ቁስለኞችን የሚያክምላቸው አንድ ሐኪም እንዲላክላቸው የጣልያን ወገኖችን ጠይቀው ነበር፡፡ የጣልያን ተወካዮችም ጥያቄውን ተቀብለው አንድ ሐኪም ላኩላቸው፡፡ የራስ መኮንን እቅድ ለሀኪሙ የተዛባ መረጃ በመስጠት የጠላትን ጦር እንዲያዘናጋ ማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ወገን የንጉሱን ዕቅድ ውስጠ ምስጢር፤ ከኋላ 100 ሺህ ጦር እየተጠጋ መሆኑን እና የጦርነቱ ግብ ጣልያንን ከአፍሪካ ምድር ጠራርጎ ማስወጣት እንደሆነ ለሀኪሙ ተነገራቸው፡፡ ገዢ ቦታ ይዘው የነበሩት የጣልያን ወታደሮች በደረሳቸው መረጃ መሠረት አሰላለፋቸውን ስላስተካከሉ ለኢትዮጵያ ጦር ፈታኝ ሆነ፡፡
መቀሌ ላይ ጠላት ገዢ ቦታ ይዞ ስለነበር ምሽጉን ለማስለቀቅ የተሰለፉ ኢትዮጵያውያን መስዋእት ሆኑ፡፡ የኢትዮጵያ ጦርም አምባላጌ ላይ የተገኘውን ድል ቶሎ ማግኘት ተሳነው፡፡ በዚህ ጊዜ የእቴጌ ጣይቱ የጦር መሐንዲስነት ነበር በመቀሌው ጦርነት ኢትዮጵያን ድል ያቀዳጀው፡፡ በምሽጉ ዙሪያ የሚገኙ ወንዞችን በታማኝ ወታደሮች በማስጠበቅ ወራሪውን ለውኃ ጥም አጋለጡት፡፡ ስንቅና ትጥቅ እንዳይቀበልም ዙሪውን አጠሩት፤ መውጫ መግቢያ አሳጡት፡፡ እናም በመጨረሻ የጣልያን ተዋጊዎች ለኢትዮጵያ አርበኞች እጅ ሰጡ፤ የመቀሌው ጦርነትም በድል ተቋጨ፡፡ ይህም ዓድዋ ላይ ለተደረገው ጦርነት ጥሩ መነቃቃት እና ወኔ ያስታጠቀ ነበር፡፡
የዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ጾታ፣ ብሔር እና ሃይማኖት ሳይለያቸው ለሕልውናቸው በአንድነት፣ ለጋራ ድላቸውም በሕብረት ዘምተው የተዋደቁበት አውደ ውጊያ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በጦር መሪነት፣ በትጥቅና ስንቅ አቅርቦት እንዲሁም የሕክምና ዘርፉን በመምራትና በማስተባበር ደማቅ ታሪክ የጻፉት እቴጌ ጣይቱ የዚህ ጹሑፋችን ማጠንጠኛ ይሆናሉ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ የጎላ ሥፍራ ካላቸው ሴቶች መካከል እቴጌ ጣይቱ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ ከዳግማዊ አጤ ምኒልክ ጋር በትዳር ከተቆራኙ በኋላ በዘመናዊት ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የአስተዳደር እና የሥልጣኔ አውዶች ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው በታሪክ ይታወቃል፡፡ በዓድዋው ጦርነት ኢትዮጵያ አሸናፊ እንድትሆን የነበራቸው ብልሃት የተሞላው የመሪነት ሚና እንዲሁም የአልደፈር ባይነት ወኔያቸው ከታሪካቸው ሁሉ የጎላ ነው ይባላል፡፡
የእቴጌይቱ ሀገርን ከወራሪ የማዳን ጥበብ ረቂቅ ነው፤ የአልደፈር ባይነት ኢትዮጵያዊ ወኔያቸውም ድንቅ ነው፡፡ ውጫሌ ላይ በተደረገው ስምምነት የአንቀጽ 17 ጣልያንኛ ትርጉም ኢጣልያ ኢትዮጵያን በሞግዚትነት የማስተዳደር ከንቱ መሻት እንዳላት በታወቀ ጊዜ ቁጣቸውን ቀድመው ያሰሙት ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ይህ አንቀጽ በፈጠረው ጭቅጭቅ ውሉ የሚፈርስ ከሆነ ከባድ ጦርነት እንደሚካሄድ የጣልያን ተወካዮች ቢዝቱም እቴጌይቱ በሀገራቸው እንደማይደራደሩ ቆራጥ አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡ በትርጓሜው ሳቢያ በተነሣው አለመግባባት እና ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ እቴጌ ጣይቱ ከፍ ያለ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የትርጉሙን ስህተት ባወቁ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ የእልፍኝ አዳራሽ ግብር እየተመገቡ ለነበሩ መኳንንትና መሳፍንት “እንግዲህ በቃ! በአንድነት ሆነን ከጣልያን ጋር ጦርነት እንገጥማለን፤ እንፋለማለን እንጂ የጣልያን አሽከር አንሆንም” ብለው በቁጣ ጮኸው ተናግረዋል፡፡
በማይናወጽ አቋማቸውም የውጫሌው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡ እቴጌ ጣይቱ፣ እነ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስን፣ ራስ አሉላን፣ ራስ አባተን እና ፊታውራሪ ገበየሁን ከመሳሰሉ ባለዝና የጦር አዛዦች ጋር ተሠልፈው ዓድዋ ላይ የተካሄደውን ጦርነት መርተዋል፡፡ በተሳተፉበት አውደ ውጊያ ወታደሮችን አሰልፈው በመምራትም ትልቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ ወደ ዓድዋ በእግራቸው ተጉዘውም አዋግተዋል፡፡ ዘማቹ የኢትዮጵያ አርበኛም ንግሥቲቷን ተመልክቶ ነበር እና በተጨማሪ ጉልበት፣ ቁጭት እና ወኔ ወደፊት ገስገሰ፡፡
ንግሥት ጣይቱም ከኋላ እየተከተሉ ግፋ በለው ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ እሳቸው የዘመቱት ተዋጊ ሠራዊት ብቻ ይዘው አልነበረም፤ አዋጊ እና ወኔ ቀስቃሽ አዝማሪዎችን ጭምር አሰልፈው ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ በደህናው ጊዜ በገና ወዳድ ናቸው ይባላል፤ በጦርነቱ ጊዜ ደግሞ ለሠራዊቱ የወኔ ትጥቅ እንዲያቀብሉ በርካታ አዝማርያን እና በገና ደርዳሪዎችን አስከትለዋል፡፡ አዝማሪዎቹም የዘመቻ ዘፈኖችን ፉከራዎችንና ሽለላዎችን እያሰሙ ለኢትዮጵያ አርበኞች በወኔ ላይ ወኔ ጨምረዋል፡፡
በቅድመ ጦርነቱ ለሠራዊቱ በቂ ስንቅ ተሰናድቶ እንዲቀርብ የማስተባበር ኀላፊነትም ነበረባቸው፡፡ አስተዋይነት በተሞላው መሪነት ስንቅ ለማዘጋጀት የሚያገለግል ቁሳቁስ ተሰባስቦ ወረ ኢሉ እንዲከማች፣ ከዚያም ወደ ዓድዋ እንዲጓጓዝ የማድረግ ሚናቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል፡፡ በጦርነቱ ላይ ስንቅ ባነሰ ጊዜም ተጨማሪ ምግብ እንዲቀርብ ማድረጋቸው ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት እንዲጠናቀቅ የነበረውን ሚና ታሪክ ይመሰክራል፡፡
እቴጌ ጣይቱ የሚመሩት ሠራዊት በወሳኙ ጦርነት ተሰልፎ ከመዋጋቱ ባሻገር ለተዋጊዎች ውኃ በማቅረብ፣ ቁስለኛ በማንሣትና በማከም ሥራ ተሠማርቶ ነበር፡፡
እቴጌ ጣይቱ በድሕረ አድዋ የነበራቸው ፖለቲካዊ ተሳትፎም እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ለሀገር ክብር ከከፈሉት ተጋድሎ ባለፈም በኢትዮጵያ ታሪክ እቴጌይቱ የላቀ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ከባለቤታቸው ከአጤ ምኒልክ ጋር በመሆን ስልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርገዋል። ንግሥት ጣይቱ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ በዚህ ታሪካቸውና በቀሪ ዘመናቸው የፈጸሙት ታሪክ የኢትዮጵያ የምን ጊዜም ጀግና ንግሥት ሆነው ዛሬም እንደ አዲስ ስማቸው ይነሳል፡፡ እኛም እንደ ትውልድ ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳይሆን ዘመኑ በሚጠይቀው አውድ የአዲስ ምዕራፍ አብሳሪ ልንሆን የግድ ይላል፡፡ የብሩክ መኮንን እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እና ሌሎችም መጽሐፍትን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡ ቸር እንሰንብት!
በደጀኔ በቀለ
ምሥል፡ ከማኅበራዊ ገጽ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
Amhara Media Corporation – YouTube
youtube.com
