“የእንግዳ ማረፊያ ነበረ ቤታቸው፤ ኖሩ በዋሻ ውስጥ ዘመን ቢገፋቸው”

303

ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እንግዳ የገባበት፣ ወጭና ወራጁ ያረፈበት፣ ጮማ የተቆረጠበት፣ ጠጅ የተጠጣበት፣ ልጆች የተዳሩበት፣ ዓለም የታየበት፤ አባት ለልጁ ያስረከበው፣ ልጅ የአባቱን ባድማ የጠበቀው የተከበረ ሥፍራ ነበራቸው፡፡ በቀዬው ኮርማዎች አግስተውበታል፤ ላሞች ታልበውበታል፤ እንቦሶች በሜዳው እንዳሻቸው ፈንጥዘውበታል፤ ሜዳውን አዳርሰውታል፤ ባዝራዎች ጭራቸውን እየነሰነሱ ተመላልሰውበታል፤ እረኞች በዋሽንታቸው እያዜሙ ተደስተውበታል፡፡

በሚያምረው ቤታቸው፣ በተዋበው አጥራቸው ውስጥ ዓለም አይተዋል፤ ደስታም አይተዋል፡፡ በግቢያቸው ውስጥ ልጆች ተጫውተውበታል፤ እናትና አባቶች የልጆቻቸውን ደስታ እያዩ ፈጣሪያቸውን አመሥግነውበታል፤ ጠላ እየወረደ፣ ጮማ እየተቆረጠ እንግዳ ተቀማጥሎበታል፤ ድግስ ተደግሶ በአዳራሹ ዳር እስከ ዳር ሰው ሞልቶበታል፤ እልል እየተባለ ደስታ ታይቶበታል፡፡

በዚያ አዳራሽ ውስጥ ወተት የሚታለብበት ግሬራው፣ እርጎ የሚረጋበት ካቦው፣ የሚታረስበት ማረሻው፣ ነጭና ጥቁር የሚቀመጥበት ጎተራው ተቀምጦ ነበር፡፡ የእረኞች ደስታ፣ የበግና ፍየሉ ጋጋታ ደስ ይል ነበር፡፡

አሁን ግን ሁሉም ትዝታ ኾኗል፡፡ እንቦሶች በባድማው አይቦርቁም፤ እረኞች በጋራ አይቀመጡም፤ የዋሽንታቸውን ዜማ አያስደምጡም፤ እንግዶች ወደ ቤት አይመጡም፤ የቀዬው ሰዎች በጋራ አይቀመጡም፡፡ አሁን ላይ ያ ማዕረግ ጠፍቷል፡፡ አደራሹ የለምና፤ ላምና በሬዎች ተወስደዋልና፡፡

ደመና ያዘለው የሐምሌ ሰማይ ያጉረመርማል፡፡ ተራራዎቹ ሁሉ በጉም ተሸፍነዋል፡፡ የዚያ ቀዬ ነዋሪዎች በማለዳ እየተነሱ ወደ ማሳቸው ይጓዛሉ፡፡ ውሏቸውም በዚያው በማሳቸው ነው፡፡ ጎተራው እንዳይጎድል፣ ምርቱ እንዳይቀንስ ብርዱን ችለው በሥራ ያሳልፋሉ፡፡ ቁሩ ሳይበግራቸው፣ ውጣ ውረድ ሳያስመርራቸው ይሠራሉ፡፡ ከወፍ አዕላፍ አውጥህ አብላኝ ያሉትን ፈጣሪ ተማምነው በሥራቸው ተጠምደዋል፡፡ እነርሱ የክረምቱ ወቅት አልፎ የበጋው ወቅት ሲመጣ የማሳውን ሰብል አጭደውና ወቅተው ወደ ጎተራ የሚያስገቡበት ዘመን ናፍቋቸዋል፡፡ በጋው ሲመጣ አዝመራው ሲሸከፍ ልጆች ይዳራሉ፤ ሰርግ ይኖራል፤ በቀየው ደስታ ከፍ ይላልና፡፡ ዳሩ እነዚያ ደግ አርሶ አደሮች ያሰቡትና ያቀዱት አልሆነም፡፡

መነሻውን ከትግራይ ያደረገው ወራሪና አሸባሪ ቡድን ሀገር መውረር ጀምሮ ነበር፡፡ በሕዝብ ማዕበል እየወረረ ቀዬ ያረክሳል፤ የተሠራውን ያፈርሳል፤ የወረራ አድማሱን አስፍቶ እነዚያ ደግ ሰዎች ወደ አሉበት ቀዬ ደረሰ፡፡ ያቺ የቅኔ ምድር ዋድላ ቅኔ እንዳልተዘረፈባት፣ ዲያቆናትና ቀሳውት፣ ሊቃውንት እንዳልፈለቁባት ጠላት በዛባት፤ የክፉ ስብስብ ወረራት፡፡ ቅኔ ዘራፊዎች፣ ምስጢር አመስጣሪዎች፣ ጥበብ አፍላቂዎች እኒያ ደጎች በክፉዎች ተገፉ፡፡

በወረሃ ሐምሌ በክረምት ተሰቃዩ፡፡ የሽብር ቡድኑ ሃብት ይዘርፋል፤ የተረፈውን ያወድማል፡፡ የዋድላ ገበሬዎች በሥራቸው እንደተጠመዱ ነው፡፡ የሽብር ቡድኑም ወደ ቀያቸው ዘለቀ፡፡ ቀያቸውንም እንዳልነበር አደረጋት፡፡ እንኳን ሰው ማገዶ ወደ ቤት በሚገባበት፣ ብርድና ዝናብ በበዛበት በወረሃ ሐምሌ እኒያ ደግ ሰዎች ቤታቸው ፈርሶ መድረሻ ቸገራቸው፡፡ ዝናብ መታቸው፤ ብርድ አሰቃያቸው፡፡ በዚያ ቁር በበዛበት፣ ወንዞች ሁሉ በሚሞሉበት፣ መሻጋሪያ በሚያሳጡበት ወቅት ቤታቸው ፈርሶ መጠለያ ጠፋባቸው፡፡ ልጆቻቸውን ይዘው የት እንድረስ ሲሉ ዝናብ በበዛበት የክረምት ወቅት ተንከራተቱ፡፡

ቀያቸውን ለቅቀው የሚያርፉበት፣ ክፉውን ቀን የሚያሳልፉበት አጡ፡፡ የክረምት ወቅት ባይሆን ኖሮ ዳስ ጥለው፣ ወይንም ከዛፍ ስር ተጠልለው ያሳልፉት ነበር፡፡ ነገር ግን የክረምት ወቅት ነው፡፡ በዚያ ላይ የሽብር ቡድኑ በደል እየፈፀመ ነው፡፡ ልጆቻቸውን አስከትለው መጠለያ ያገኙ ዘንድ ባዘኑ፡፡ በአንድ ሥፍራም ይኖሩ ዘንድ ወደዱ፡፡ ያም ሥፍራ የሰው እጅ ያላረፈበት፣ ማገርና ግድግዳ ያልቆመበት፣ ጣሪያ ያልተሰቀለበት በተፈጥሮ የተሰራ ዋሻ ነበር፡፡ ለእነዚያ ደገኛ ሰዎች ከዚያ ዋሻ ውጭ ሌላ መጠለያ አልነበራቸውም፡፡

በዚያ ክረምት ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በውስጡ ምን ይኑረው በማይታወቅበት፣ አመሻሽ ላይ ምን እንደሚመጣበት በማይገመትበት ዋሻ ውስጥ ገቡ፡፡ በዚያ ዋሻ ውስጥ ተሳቢ እንስሳት ቢነድፋቸው፣ የሚወዷቸውን ልጆች ቢነጥቋቸው ከፈጣሪ ውጭ ማንም ደራሽ አልነበረም፡፡ መልካም ነገር ሁሉ ይሆን ዘንድ ለፈጣሪያቸው ጸሎት እያቀረቡ በዛች ዋሻ መኖር ጀመሩ፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን የዋድላ ወረዳ አጤ ውኃ አካባቢ ነዋሪዎች አያሌ መከራዎችን አሳልፈዋል፡፡ “እኛ ገበሬዎች ነን፤ ማዳበሪያ አውጥተን፣ ስንዴውን አተሩን ዘርተን እንዳበቃን እንጠቀማለን ስንል ወራሪው ትግሬ መጣብን፤ ሲያፍነን ወደዚህም ወደዚያም መውጫ የለንም፤ ቤተሰብ ይዘን የሚያስጠጋንም የለም፤ ንብረታችንን ጥለን ልጆቻችን ይዘን ከዚህ ዋሻ ውስጥ ተሸጉጠን ሕይወታችን አትርፈናል” በዚያ በሞቀ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው ይሄን ያሉት፡፡ መድረሻ አጥተው፣ በዋሻ ውስጥ ተሸጎጡ፤ በዋሻ ውስጥ የክረምት ጎርፍ ቢያስቸግራቸው፣ አካባቢው በናዳ ቢዘጋባቸው ከእነ ልጆቻቸው የበለጠ መከራ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይሄም አስግቷቸዋል፡፡ ግን ምርጫ የለም፡፡

ʺየያዝነው ነገር የለም፤ ልብስ አልያዝንም፤ ልጆቻችን ይዘን ነው የወጣነው፤ አሁንም በዋሻ ውስጥ ነን፤ ጎመኑን ለመቀንጠስ፣ ድንቹን ለመማስ ስንደርስ የትግራይ ወራሪ መጥቶ ወረረን፤ ባቄላውም፣ ስንዴውም ሁሉም ዝም ብሎ ወድሞ ቀረ፡፡ ውኃ ጥሙ እየበረታ፣ ውርጩ እየመታን እየተሰቃዬን ነው ያለነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚያች የነብስ መዳኛ በሆነች ዋሻ ውስጥ የሚገኙት ንጹሃን ወገኖች ብዙ መከራዎችን እያሳለፉ ነው፡፡ በዚያች ዋሻ ውስጥ መኖር ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በከፋ ችግር ውስጥ ሆነው ድንጋይ ተንተርሰው ያድራሉ፤ በዚኽ ሰሞን እማ ነብር እየመጣ ነው ይላሉ፤ በዚያች ዋሻ ውስጥ የክረምቱን ወራት ያሳለፉት ብዙዎች ናቸው፡፡

ጠላት በወገን ጦር ተቀጥቅጦ ሲወጣ ዘመድ ያላቸው ወጥተዋል፡፡ መድረሻ ያጡት ግን አሁንም እዛው አሉ፡፡ ዛሬም ከዱር እንስሳት ጋር ይፋጠጣሉ፤ ዛሬም ከአዕዋፋትና ከዱር እንስሳት ጋር ውኃ ተካፍለው ይጠጣሉ፡፡

ʺሰብላችን በፊትም ሳይታረም ቀረ፤ በኋላም ተቃጠለ፤ አዝመራም የለም፤ ቤታችንም ወድሟል፡፡ ምንም የያዝነው ነገር የለም፡፡ ከሞቱትም በላይ ካሉትም በታች ሆነን ነው ያለነው፡፡ ለጊዜው ሕይወታችንን ይዘን ወጥተናል፡፡ ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ የፈረሰውን ቤታችን እንዳንሠራው ገንዘብ የለንም፡፡ መንግሥትም ዞሮ አላየን፤ ድንጋዩ ይጫነን ይሆን እያለን በስጋት እንኖራለን፡፡ ጨንቆን ነው የምንኖረው፤ መመለሻ አጣን፤ መግቢያ የለንም” ብለዋል፡፡

እነርሱ ወዳሉበት ዋሻ ውስጥ ነብር ይመጣል፡፡ ምግብ የለመደው ጅብም እነርሱ ወዳሉበት በየቀኑ ይሄዳል፡፡ ልጆቻቸውን እንዳይነጥቃቸው ሲከላከሉ ያድራሉ፡፡ በዚያ ዋሻ ውስጥ የሰላም እንቅልፍ የለም፡፡ በዚያ ዋሻ ውስጥ ደስታ የለም፡፡ በዚያ ዋሻ ውስጥ ተድላ የለም፡፡ በዚያ ውስጥ ትዝታ፣ ሐዘን፣ ጥምና ረሃብ ነው ያለው፡፡ የደስታ ቤታቸው ፈራርሶ፣ የካበተው ንብረታቸው ተወርሶ በዋሻ ውስጥ በሐዘን ተኮማትረው ይኖራሉና፡፡

መንግሥት ካልደረሰልን ሰቆቃ ውስጥ ነንም ብለዋል፡፡ ምግብ እንዲያቀርብላቸው፣ ልብስም ቢሰጣቸው፣ መጠለያቸውን እንዲሠራላቸውም መንግሥትንና በጎ አድራጊዎችን ጠይቀዋል፡፡

በዚያ ዋሻ ውስጥም ኾነው ደግነታቸው አልነጠፈም፣ እጃቸው አልታጠፈም፣ ከዕለት ጉርሳቸው እየከፈሉ ሊጠይቃቸው የሄደውን ስሞት ብላ ይላሉ፡፡ ደጎች ናቸውና ያላቸውን ተካፍለው መብላት ያውቁበታል፡፡ በዋሻ ውስጥ እየኖሩ ምግብ ካልበላችሁ እያሉ ሲጠይቁም አንጀት ይበላሉ። እነዚያ ደጎች ቤት አጥተው፣ እንደ ዱር እንስሳ በዋሻ ውስጥ ተጠልለው ኑሮን ሲገፉ ማየት ያሳዝናል፡፡

“የእንግዳ ማረፊያ ነበረ ቤታቸው፤
ኖሩ በዋሻ ውስጥ ዘመን ቢገፋቸው፡፡” ዛሬ ላይ ዘመን ገፍቷቸው፣ ወራሪ ቡድን ቤትና ንብረት አሳጥቷቸው በዋሻ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ደጋግ ሰዎች ከዋሻ ውስጥ ወጥተው ወደ ሞቀ ቤታቸው ይመለሱ ዘንድ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃሉ፡፡ ቤታቸውን በመሥራት፣ የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ በማቅረብ ደስታቸውን መመለስ የኢትዮጵያውያንን መልካም መልካምነት ይጠይቃል፡፡ ቤታቸው ይሠራላቸው፤ ደስታቸው ይመለስላቸው፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Amhara Media Corporation – YouTube
youtube.com

Previous article‹‹በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ለመመለስ እየተሠራ ነው›› አምባሳደር ሌንጮ ባቲ
Next articleየሀገርን ሰላም ለማደፍረስ እረፍት አልባ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለውን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በቅንጅት መደምሰስ እንደሚገባ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አመላከቱ፡፡