“ዓድዋ ከአንድ ጊዜ ጦርነት ድል ባለፈ የአንድ ምዕተ ዓመት ክስተት ነበር” ዶክተር እሰይ ከበደ

192

ባሕር ዳር: የካቲት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ ጦርነት ምንጩ ሀገርክን አስረክብ ባሉ ኢምፔሪያሊስቶች እና ሀገሬን ከማስረክብ ሞትን እመርጣሉ ባሉ ጥቁር መሪዎች መካከል የተፈጠረ ክስተት ነበር፡፡ የዓድዋ ድል ምንጩ እንደ ፈጣሪ ተገዛልኝ ባሉ ቀኝ ገዢዎች እና በባርነት ከመኖር ለነጻነት ታግሎ ማለፍ ይሻለናል ባሉ ኢትዮጵያዊያን መካከል የተፈጠረ ጀብደኝነት ነው፡፡ የዓድዋ ድል አስተምህሮ ኃይል አለን ያሉ ትዕቢተኞች በሽንፈታቸው ሲሸማቀቁ ማየት እና “ጉልበታችን ፈጣሪያችን ነው” ባሉ አሸናፊዎች መካከል ያለውን የእሴት ልዩነት ለትውልዱ ማንበር ነው፡፡

የዓድዋ ድል የጥቁር መሪው ብስለት እና የዜጋው ሀገራዊ ስሜት የዓለምን ትኩረትን የሳበበት ነበር፡፡ ጣሊያናዊያኑ እስከ ጦርነቱ ቀን ድረስ የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ምድር ኹሉ ከመቆጣጠር የሚያግዳቸው ኅይል ያለ አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ከሰባት ዓመታት በላይ በቅድመ ዝግጅት እና በውስጣዊ አንድነት ላይ አተኩረው ሲሠሩ የነበሩት ዳግማዊ ምኒሊክ ለጣሊያኖች የሚታዩ ከነበራቸው አቅም እና ዝግጅት በታች ኾነው ነበር፡፡

በዓድዋ ጦርነት ነጮች በጥቁሮች ከመሸነፋቸው በላይ እጅግ ተሞኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ወራሪዎቹን ጦርነት አይጠቅምም ሲሏቸው ፍርሃት፣ ምርኮኛ ሲመልሱላቸው ሞኝነት እና ሲታገሷቸው ቂልነት እየመሰላቸው አጉል ጀብደኝነት አበዙ፡፡ ከዚያ ኹሉ ውጥረት፣ ውጣ ውረድ እና ቅድመ ዝግጅት በኋላ አይቀሬው ጦርነት በዓድዋ ተራሮች ግርጌ ተጀምሮ የማታ ማታ በኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በድል ተጠናቀቀ፡፡

ዓድዋም ጥቁሮች ባሉበት የዓለም ክፍል ኹሉ ዳግም ላይደበዝዝ 126 ዓመታትን እየተዘከረ አስቆጠረ፡፡

126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ “ዝክረ ዓድዋ የባሕል አውደ ጥናት፤ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያዊ ማንነት እና የባሕል ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ ተከብሯል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት እሰይ ከበደ (ዶ.ር) “ዓድዋ ከአንድ ጊዜ ጦርነት ድል ባለፈ የአንድ ምዕተ ዓመት ክስተት ነበር” ብለዋል፡፡ የዓድዋ ድል በዓል በየዓመቱ ሲከበር ለትውልዱ ታሪክን ከማስተላለፍ ባለፈ በትውልዱ ዘንድ የአልሸነፍምባይነት ስሜት ለመፍጠር መኾን አለበት ብለዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 126ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ሲያከብር ሦስት ወቅታዊ መነሻ ነጥቦች እንዳሉት የገለጹት ዶክተር እሰይ የሕልውና ዘመቻው ስጋት ለመቀልበስ የታየው ሀገራዊ መነሳሳት፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨት እና ዩኒቨርሲቲው የሚያከብረውን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ታሳቢዎች አድርጎ ነው ብለዋል፡፡

በአውድ ጥናቱ በቀረቡት የምርምር ሥራዎች የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይኾን አፍሪካዊያንን እና መላ ጥቁር ሕዝቦችን በጋራ ለማቆም “ስውር ማግኔት” ኾኖ አገልግሏል ተብሏል፡፡ ለዓድዋ ድል ፊት ለፊት ነፍጥ አንግበው ከተዋጉት አርበኞች በተጨማሪ ዓለም አጫዋቾች፣ እረኞች እና ሕጻናት ሳይቀር ሚና እንደነበራቸው ተነስቷል፡፡ በወራሪዎቹ እና በአንወረርም ባዮቹ መካከል ያለው የመንፈስ እና የእሴት ልዩነት ባስመዘገቡት ውጤት ላይ የነበራቸው ተፅዕኖም ለውይይት ቀርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከኪነ ጥበብ ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው ሥነ ሥዕል ከድል ማግስት በኋላ ታሪኩን በመከተብ በኩል የነበረው ሚናም ተዳሷል፡፡

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የዓድዋ ድል ትውፊትን በሰፊው በማስተዋወቅ ለአሁናዊ የሀገር ውስጥ ችግሮች እና ለአህጉራዊ መቀራረብ እንዲጠቅም አድርጎ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአማራ ክልል 40 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ድጋፍ አደረገ።
Next article‹‹በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ለመመለስ እየተሠራ ነው›› አምባሳደር ሌንጮ ባቲ