
የካቲት 17/2014 ዓ.ም(አሚኮ) ከነጫካ አስተሳሰቡ ሳይሻሻል እና መለወጥ ተስኖት ከተራ ሽፍትነት እስከ መንግሥትነት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያንዣበበው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለሀገሪቱ እዳ፤ ለሕዝቧ መከራ ኾኖ የኖረበትን ጊዜ ዛሬ ላይ ኾነው ማስታወስ የማይፈልጉት አያሌ ኢትዮጵያውያን ናቸው። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ምንም እንኳን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የፈተና ዘመኑ መዘውር ኾኖ መቆየቱ ጥያቄ የማያስነሳ ሃቅ ነው፤ ለአማራ ሕዝብ በተለይም ደግሞ ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አማራዎች ደግሞ ያሳለፉት ያ የመከራ ጊዜ ከሰብዓዊ እሳቤ አንጻር ሲመረመር እጅግ የመረረ ነበር።
በታሪክ፣ በባሕል እና በሥነ ልቦና ውቅር ከሥረ መሠረቱ ማንነቱ አማራ የኾነ ሕዝብ እና አካባቢዎች አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወደ መንበረ መንግሥትነት ከተንጠላጠለበት ጊዜ ጀምሮ የሚመዘዝ የግፍ እና የመከራ ሕይዎትን አሳልፈዋል።
በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ማንነቱን አላስነካም በማለቱ እና የተውሶ ማንነት ይቅርብኝ ስላለ ብቻ ከሰብዓዊነት በታች እንዲኖር ተደርጓል። ከነእውነተኛ ማንነታቸው በግፍ የተረሸኑት ብዙዎች ናቸው። አማራ ነን ስላሉ ብቻ ከቀያቸው የተሰደዱት እልፎች ነበሩ። የመከራ ዘመን ተሸኝቶ እውነተኛ ማንነታቸው በትግል ይመለሳል ሲሉ በእስር ፣ በግዞት የኖሩት፣ በማስፈራሪያ የተዋከቡት እና በድብደባ አካላቸውን ያጡት ሕያው ምስክር ለመኾን በቅተዋል።
“በግፍ የከበረ በኃይል ይደኽያል” እንዲሉ በግፍ ሥልጣን ላይ የቆየው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በኃይል ይገረሰስ ዘንድ የሕዝቡ የምሬት መብዛቱ እንደተጠበቀ ኾኖ ቀዳሚ ምክንያት የኾነው ግን የወልቃይት እና የራያ ሕዝብ ዘመን አይሽሬ የነጻነት ትግል ነበር። በራሱ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ሳይቀር የማይታበይ አንድ ሃቅ ቢኖር “ወልቃይት ኾይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” በሚል የተለኮሰው የነጻነት ትግል ነው፤ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንን ገና በሥልጣን ዘመኑ እና በቆራጭ ፈላጭ ወንበሩ ላይ እያለ በእንብርክክ አስኪዶታል።
የሽብር ቡድኑ መሪዎች እና አባላቱ ከሥልጣን ማማ ተንሸራተው፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ወደ መቀሌ ተባረው እንኳን የአማራ ማንነት ጥያቄን ለማዳፈን እስከሚችሉት አምቧትረዋል፤ አልቻሉም፤ ምክንያቱንም ማንነትን መቀማት ስለማይቻል።
በአማራ ሕዝብ መራር ተጋድሎ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ከአሸባሪው ቡድን የዓመታት የኃይል አፈናና ጭቆና ነጻ ወጥቷል።
እንዳለመታደል ኾኖ ዛሬም እንኳን ከመቃብራቸው አፋፍ እና ከመጥፋታቸው በራፍ ላይ ቆመው ከስሕተቶቻቸው ለመማር የማይፈቅዱት የጥፋት አበጋዞች የኢትዮጵያ ሕዝብ ሸክም እና የአማራ ሕዝብ ፈተና ከመኾን አልቦዘኑም። የሽብር ቡድኑ ዘዋሪዎች እነርሱ አይሞቱምና ለማሰብ የሚከብድ ቀቢጸ ተስፋቸውን፣ የማይመረመር የቀን ቅዥታቸውን እና የማይፈታ የሌሊት ሕልማቸውን ለማሳካት በተሳሳተ የሒሳብ ስሌት ብዙ ጥረዋል።
በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሱትን ጥፋት ታሪክ ይቅር አይለውም። አሁንም ለሌላ ጥፋት እና እጥፋት እንደሚዘጋጁ መስማት ደግሞ ሰዋዊ ኾነው እስከመፈጠራቸው ያጠራጥራል።
የኢንተርሃሞይ የእርስ በእርስ እልቂት አቀንቃኞቹ፣ የዩጎዝላቪያ መፈረካከስ አራማጆቹ እና የቁሞ ቀሩ አፓርታይድ ሥርዓት አስተምህሮ ሰባኪዎቹ “ጉዶች” ለዳግም ወረራ እየተዘጋጁ ነው ይባላልና ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል? ስንል በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለውን ጠየቅናቸው። “አያደርጉትም እንዳንል ተስፋ መቁረጣቸውን እናያለን፤ ያደርጉታል እንዳንልም ያደጉበትን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እናውቃለን” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው እንዳመጣጣቸው ማስተናገድ ግን ለነገ የማንለው ሥራችን እንደኾነ ካወቅን ቆይተናል ብለዋል።
አቶ አሸተ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የሽብር ቡድኑን ተፈጥሯዊ ስሪት እና አቅም ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ነው የገለጹት፡፡ እነርሱም የወልቃይትን ሕዝብ ማንነት ካልሳቱ በቀር ያውቁታል ብለዋል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አባላት ተሳስተው እንኳን ወሰን ከተሻገሩ ግን ዳግም እንዳያስቡት በሚያስችል መልኩ ይደመሰሳሉ ብለዋል። አቶ አሸተ ሕዝቡ አምርሮ የሚጠላው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ነው፤ ያመረረ እና የመረረው ሕዝብ ደግሞ ምን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት አይከብድም ባይ ናቸው።
አካባቢው የኹለት ሀገራት ድንበር ከመኾኑም በላይ የሽብር ቡድኑ ለዘመናት የተወዳጇቸው የውጭ አበጋዞቻቸው መገናኛ መኾኑን አቶ አሸተ ጠቅሰዋል፡፡ ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፤ ዞኑም በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል። መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ካሳለፈበት ጊዜ አንስቶ አሸባሪዎቹ ወደ አካባቢው ሰርጎ ለመግባት ከ25 ጊዜ በላይ ሙከራ እንዳረገ ጠቅሰው ቀድሞ በነቃ እና በተጠነቀቀ ሕዝብ መካከል የገቡት ሰርጎገቦች መውጣት የመግባትን ያክል ቀላል አልኾነላቸውም ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አሸተ እንደገለጹት ሕዝቡን ከማስታጠቅ ባለፈ በሥነ ልቦና የማንቃት እና የማብቃት ሥራዎች በበቂ ተሠርተዋል። ሕዝቡም የደረሰበትን ግፍና መከራ፣ እንግልትና ስቃይ፣ ስደትና ሞት ስለማይረሳ ራሱን ለዳግም ወረራ አጋልጦ አይሰጥም ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንን የግፍ አገዛዝ የደረሰበትን ኹሉ ለመገንዘብ አስረጂ አይሻም፤ ከሞት በላይ ዋጋ ቢኖር እንኳን እሱን ለመክፈል ዝግጁ ነው ብለዋል። በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል ድርሻው ሕዝቡን ማደራጀት ብቻ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው እሱም ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶት ተሠርቷል ብለዋል። በዚህ ኹሉ መካከል ግን የመምጣታቸው አጋጣሚ ከተፈጠረ በወልቃይት ምድር ዳግም ላይሞክሩ ይቀበራሉ ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው ሕዝቡ ከነጻነቱ ማግስት ጀምሮ ሰላሙን በማስጠበቅ፣ ፀጥታውን በመጠበቅ እና ለኅልውናው በመጠንቀቅ እንደቆየ ጠቁመዋል፤ ከዚህ ጎን ለጎን ግን እንደግለሰብ የመልማት እና ጸጋዎቹንም የማልማት ጽኑ ፍላጎት አለው ነው ያሉት። ዞኑ ያሳለፈውን ግፍ እና የደረሰበትን ውድመት ለማካካስ የፌዴራል መንግሥቱ እስከአሁን ምንም ነገር አለማድረጉ ሕዝቡን ቅር እንዳሰኘው አስታውቀዋል።
ዞኑ በጦርነቱ ክፉኛ እንደተጎዳ እየታወቀ የሠራተኛ ደመወዝን ጨምሮ በበጀት እየደገፈው ያለው ክልሉ መኾኑን አቶ አሸተ ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምና ግንባታ እቅዱ ውስጥ እንኳን አልተካተተም ብለዋል። ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር 100 ሚሊየን ብር የደጎመ አካል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምንም አለማድረጉ ቅሬታ ፈጥሯል ብለዋል። የፌዴሬል መንግሥት በጀት እንዲመድብም ጠይቀዋል።
“የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ ባለፉት 15 ወራት በደም የተገኘ ነጻነቱን መብራት፤ የናፈቀውን እውነተኛ ማንነቱን እራት አድርጎ በጽናት ይጠብቃል” ነው ያሉት አቶ አሸተ፡፡ የቆሙ የልማት ፕሮጀክቶችን ማስቀጠል፣ ድጋፍ፣ የውኃ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ሊሟሉ ይገባልም ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት የዞኑን ሕዝብ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ይዞ በትኩረት እየሠራበት መሆኑን ያወሱት አቶ አሸተ ፈጣን እና ተገቢ ምላሽ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
