
የካቲት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የምክር ቤት አባላት ካነሷቸው አንኳር የሕዝብ ጥያቄዎች መካከል የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት አንዱ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ምሬት ውስጥ አስገብቶታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም ይሕንኑ ነው ያረጋገጡት፡፡ በተለይ ከምግብ ነክ ሸቀጦች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት መፈጠሩን አመላክተዋል፡፡ ይህም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በልቶ ማደር እንዳይችሉ አድርጓል፤ እንዲማረሩም ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት፡፡
የዋጋ ግሽበት በአንድ ምክንያት ብቻ የሚፈጠር አለመኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሑራን በርካታ ምክንያቶች ያነሳሉ ብለዋል፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች መካከል በሕዝብ ቁጥር እድገት የተፈጠረው የፍላጎት መጨመር አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሌላኛው የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ምክንያት የአቅርቦት እድገቱ ከፍላጎት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑ ነው፡፡ ነጋዴው የዋጋ ጭማሬን በመጠበቅ ምርትን መሸሸግ እና ሸማቾች ውድነቱን በመስጋት ለመግዛት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ ተነስቷል፡፡ በነጋዴና ሸማቾች የተዛባ አመለካከት ምክንያት ምርት እያለ እንኳን የዋጋ መናር እያጋጠመ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የዓለም የሸቀጥ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩም ለችግሩ መባባስ አንዱ ነው፡፡ የኮሮናቫይረስ በዓለም የንግድ ሥርዓት ላይ በፈጠረው ተጽዕኖ መሠረት የዓለም ኢኮኖሚ መቀነሱንም አመላክተዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ሸማችን ከምርት ጋር የማገናኘት ችግሩ የዋጋ ግሽበቱን እንዳናረው ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ሕዝቡ ገዝቶ መብላት ስላልቻለ በከፍተኛ ደረጃ ተማርሯል ነው ያሉት፡፡ የዋጋ ግሽበቱ የፈጠረውን መዛባት ለመቀነስ መንግሥት በግምጃ ቤት ሰነድ እንዲሟላ አድርጓል ብለዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያትም ገንዘብ በገበያ ውስጥ በተሰራጨ መጠን ግሽበቱ ስለሚባባስ 80 በመቶ በግምጃ ቤት ሰነድ ለመተካት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም የተሠራው ሥራ ቀላል እንዳልሆነ ነው ለምክር ቤት አባላቱ ያብራሩት፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት የምግብ ሸቀጥ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ኮታ መሰጠቱንም አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለነዳጅና ለአፈር ማዳበሪያ መንግሥት ድጎማ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ የከተማ ግብርና እንዲያድግም ተደርጓል ብለዋል፡፡ አሁንም በከተሞች የጓሮ አትክልት መልማት የሚችል ከሆነ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት፡፡ ለዋጋ ግሽበቱ ዋንኛው የችግር መሠረት የምግብ ሸቀጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት እንደ ሀገር የምግብ እህል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ ለዚህም የሁሉንም ርብርብ ይሻል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
