
ባሕር ዳር: የካቲት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደ ጥናት በአምስት ዘርፎች የሚካተቱ 35 የማዕድን አይነቶች መገኘታቸውን ቢሮው ገልጿል፡፡ ክልሉ በርካታ የማዕድን ሀብት ባለቤት እንደኾነ በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡን የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኀይሌ አበበ በተለይ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በ25 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የሥነ ምድር ካርታ እና ማዕድን ክምችት ጥናት መካሄዱን ነው አቶ ኃይሌ ያነሱት፡፡ በተደረጉ ጥናቶችም በከበሩ፣ በብረትነክ፣ በግንባታ፣ በኀይል አቅርቦት እና በኢንዱስትሪ ማዕድናት የሚካተቱ 35 የማዕድን አይነቶች በክልሉ መገኘታቸው ተረጋግጧ ብለዋል፡፡ የኢንዱስትሪ እና የግንባታ ማዕድናት ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ ነው ያሉት፡፡ ዘርፉን ለማልማት ባለፉት ዓመታት ለከፍተኛና አነስተኛ ፋብሪካዎች ፈቃድ መሰጠቱን አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ ኀላፊው እንዳሉት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ 209 ባለ ሀብቶች በከፍተኛ ኮንስትራክሽን፣ በአነስተኛ ኢንዱስትሪ እና በአነስተኛ ኮንስትራክሽን ፈቃድ ተሰጥቷል፤ 147ቱ ደግሞ ወደ ምርት ገብተዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ደግሞ 91 ባለ ሀብቶች በከፈተኛ ኮንስትራክሽን የተሰማሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ለሰባት ግዙፍ የስሚንቶ ፋብሪካዎች የግንባታ ፈቃድ መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ወደ ግንባታ ገብተዋል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ሲገቡ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የሚታየውን የሲሚንቶ እጥረት ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ኀይሌ አስገንዝበዋል፡፡
ለአስር የግራናይት እና የማርብል ፋብሪካዎችም ፈቃድ መሰጠጡን ነው አቶ ኃይሌ ያነሱት፡፡ ሶስቱ ተጠናቅቀው ሥራ ላይ ሲኾኑ ሰባቱ ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው፡፡
ፋብሪካዎቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ሀገሪቱ ከቻይና እና ከህንድ ለግራናይት ብቻ የምታወጣውን 70 ሚሊዮን ዶላር ያስቀራል ተብሏል፡፡ ለአምስት የድንጋይ ከሰል ፋብሪካዎችም የግንባታ ፈቃድ እንደተሰጠ የጠቆሙት አቶ ኀይሌ በመርሳ ከተማ በ475 ሚሊዮን ዶላር ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡ እንደ ኀላፊው ገለጻ የብረት እና ብርጭቆ ፋብሪካዎችን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለመገንባት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡
በክልሉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በማዕድን ዘርፉ ብቻ በየዓመቱ በአማካይ ለ50 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ የማዕድን ዘርፉ ባለፉት ዓመታት ውስብስብ ችግሮች እንደነበሩበት ነው አቶ ኃይሌ የገለጹት፡፡ የማዕድን ፖሊሲ አለመኖሩ፣ የነበረው ሥርዓት አማራ ክልል ያለው የማዕድን ሀብት በግልጽ እንዲታወቅ አለመፈለጉ፣ ዘርፉን ለማልማት ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቁ፣ የቴክኖሎጂ እና የክህሎት ችግሮች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡
ማዕድን ሀብቱ የድህነት መውጫ መኾኑን ከመረዳት ይልቅ ‹‹ማዕድን ከወጣ የእርስ በርስ ግጭት ምንጭ ይኾል›› የሚል የተሳሳተ አመለካከቶች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡ አቶ ኃይሌ እንዳሉትከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የማዕድን ፖሊሲ በመንደፍ መዋቅሩን በተጠና መንገድ የማስተካከል ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ የማዕድን ፍኖተ ካርታ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአካባቢያቸው የሚገኙ ማእድናትን እንዲያጠኑ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በማእድን ዘርፉ የሚታየውን ሕገ ወጥነት የመከላከል ሥራ እየተከወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
