
ደብረማርቆስ: የካቲት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የያኔው ቦርደር ዳም ዠየአሁኑ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ከ1958 ዓ.ም እስከ 1964 ዓ.ም በአሜሪካውያን ባለሙያዎች ሲያስጠኑ የሰጡት ስያሜ ነበር።
ብርሃን መስጠት የጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ይሁንታ እና ግፊት በአሜሪካዊያን ሙያተኞች ለስድስት ዓመታት ተጠንቶ ለአሁኑ ትውልድ የተቀመጠ ፕሮጀክት መኾኑን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው አንዳርጌ ተናግረዋል፡፡
ንጉሡ ቦርደር ዳም ብለው ያስጠኑት የአሁኑ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የጥናት ሰነድና ዲዛይን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ቤተ መዛግብት ይገኛል፡፡
የዘመናት ቁጭትና ለሀገሩ ባዕድ የኾነው የዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያዊያንን ሊክስ እና የተስፋዋን ምድር በብርሃን ሊያረሰርስ ጉባ በርሃ ውስጥ ብርሃን መለገስ ጀምሯል፡፡
የዛሬው የአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ግድብ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ ንግሥና ሐሳቡ በንድፍ ተፀንሶ በዛሬው ትውልድ ገቢር ለመኾን በቅቷል፡፡ ትናንት ኢትዮጵያ በውኃ ሃብቷ ለመጠቀም ተደጋጋሚ ጥያቄ ያነሳችበት በአንጻሩ ደግሞ ግብፅ እና ሱዳን የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ውል እንዲተገበር ያሴሩበት ዓባይ እጅ ሰጥቷል፡፡
የግብጻዊያን አካሄድ ያልተዋጠላቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በወቅቱ ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን መልካም ግንኙነት በመጠቀም ስድስት ዓመታትን የፈጀ ጥናት አስጠኑ፤ ይህም ጥናት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መዛግብት ማዕከል ውስጥ ይገኛል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ እና የሐዲስ ዓለማየሁ የባሕል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው አንዳርጌ፥ ንጉሡ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ባስጠኑት ጥናት መሠረት የአሁኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የያኔው ቦርደር ዳም 6 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ኃይል ሊያመነጭ እንደሚችልም ጥናቱ ያመላክት ነበር ይላሉ፡፡
ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ በዓባይ ተፋሰስ ያስጠኑት ጥናት አራት ግዙፍ የኃይል ማመንጫ እና ሌሎች 29 አነስተኛ ግድቦች መገንባት የሚያስችል ነበር ያሉት መምህሩ በወቅቱ ሀገሪቱ እነዚህን ፕሮጀክቶች እውን ማድረግ የሚያስችል የገንዘብ አቅም ስላልነበራት ለቀጣዩ ትውልድ አደራ ጥለውለት አልፈዋል ብለዋል፡፡
የንጉሡ የጥናት ሰነድ እንደሚያሳየው በዓባይ ተፋሰስ ሊገነቡ ከተጠኑ 33 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በመስኖ የሚለማ 420 ሺህ ሄክታር መሬት እና ከአራት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት እንደሚላቀቁ ያለመ ንድፍም ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ቋሚ ሃብት የኾነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ሥራውን ትናንት በይፋ ጀምሯል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው -ከደብረ ማርቆስ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.co
