
የካቲት 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በካርቱም በተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት መሰረት መኾኑን የውኃ ሃብት አስተዳደር አማካሪ አቶ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ገለጹ፡፡
ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት “የውኃው መጠን ይቀንስብናል” ሲሉ የሚያቀርቡት ስጋት ትክክል አለመኾኑን በተግባር ያሳየ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ13 ተርባይኖች በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይችላል፡፡ ከእነዚህ መካከል 375 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨውና “ዩኒት 10” የተባለው ተርባይን ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተመርቆ ሥራውን አሃዱ ብሎ ጀምሯል፡፡
ኾኖም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱዳን ግድቡ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ሦስቱ ሀገራት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በካርቱም የተፈራረሙትን የመርሆች ስምምነት በጣሰ መልኩ ነው የሚል መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዳሴው ግድብ ተወካይ አምባሳደር ኦማር አልፋሩቅ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ “ሦስቱ ሀገራት የተናጥል እርምጃ እንዳይወስዱ” በሚል የተፈራረሙትን የመርሆች ስምምነት የሚጥስ ነው የሚል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የውኃ ሃብት አስተዳደር አማካሪ አቶ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ “ግብጽና ሱዳን ያወጡት መግለጫ የተለመደ የሐሰት ክስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በካርቱም የተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የለባትም የሚል አንቀጽ የለውም ብለዋል፡፡
የመርሆች ስምምነት አንቀጽ 5 “ሦስቱ ሀገራት በውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ መመሪያ ላይ ስምምነት ያደርጋሉ፤ የግድቡ ግንባታ በትይዩ ይካሄዳል” የሚል መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በመርሆች ስምምነት መመሪያ መሰረት የግድቡ ግንባታ አሁንም 84 በመቶ ስለኾነ ገና ይቀጥላል፤ የግድብ ግንባታ ማለት ደግሞ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ እንዲሁም ኃይል ማመንጨትንም ይጨምራል ብለዋል፡፡
በመኾኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውኃ እንዲይዝ የተደረገበት ዋነኛ ዓላማ ኃይል ለማመንጨት ስለኾነ ይህንኑ ሥራ ጀምሯል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አኳያ ግድቡ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ የተጣሰ የመርሆች ስምምነትም ኾነ የሚጎዳ ሕዝብ የለም ብለዋል፡፡
”ግብፅና ሱዳን የግድቡን ግንባታ እንደማይጎዳቸው ያውቃሉ” የሚሉት አቶ ፈቅ አሕመድ፤ በቀጣይ ሀገራቱ ግድቡን በሚመለከት ለሚከተሉት የተዛባ አካሄድ አስፈላጊውን ምላሽና ትንተና ለመስጠት መዘጋጀት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ይጠናቀቃል ከተባለበት ከ11 ዓመት በላይ በመጓተቱ በሕዝቡ ዘንድ “ግድቡ ያልቃል ወይ” የሚል ጥያቄ አጭሮም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ለመጓተቱ የገንዘብ እጥረት፣ የውጭ ጫና እና ሌሎች ጉዳዮች ሲጠቀሱ አሁን ላይ ኃይል ማመጨት መጀመሩ ለኢትዮጵያውያን ተስፋና መነሳሳት፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ ከድህነት መውጫ መኾኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
ግድቡን በፍጥነት አጠናቆ በጨለማ ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ የኃይል ተጠቃሚ በማድረግ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተሳሳተ መረጃ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰውን ጫና መቀነስ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ግድቡ ሲሞላም ኾነ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚሄደው ውኃ እንደማይቀንስ በተግባር መታየቱን ጠቅሰው፤ በመኾኑም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ይህንኑ ሐቅ ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
