
የካቲት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የካቲት 12 በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ ያለው ዕለት ነው፡፡ ለዘመናት የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያዊያንን በኃይል በማንበርከክ ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ብዙ ሞክረዋል፡፡ ሙከራዎቻቸዉም ሳይሳካ ሽንፈት ተከናንበዉ ተመልሰዋል፡፡
በ1888 ዓ.ም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የጣሊያን ጦር ዘመናዊ መሳሪያን ታጥቆ መጣ፡፡ ኾኖም ግን ባልተለመደ ሁኔታ እስከ አፍንጫዉ የታጠቀው ዘመናዊና ግዙፉ የአውሮፓዊት ሀገር የጣሊያን ጦር ብርቱ ልብ እንጂ ይኼ ነዉ የሚባል ዘመናዊ መሳሪያ ባልነበራቸው በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ተሸነፈ፡፡ ይህ ሽንፈት ለኢትዮጵያ ጊዜ የማይሽረው ታሪካዊ ድል ቢኾንም ወራሪዉን ኃይል አንገት ያስደፋ የውርደትና ቅሌት ጦርነት ነበር፡፡ ከዚህ አስከፊ ውርደት ለማገገምና ኢትዮጵያን ለመበቀል በወቅቱ የጣሊያን ገዥ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ከ40 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ወረራት፤ ለጊዜዉም ቢኾን የጦር የበላይነት አግኝቶ የተወሰኑ ከተሞችን ያዘ፡፡ ኾኖም ግን ለነፃነታቸዉ የማይተኙና ባርነትን የማይቀበሉ የኢትዮጵያ ልጆች ለወራሪዉ ኃይል የእግር እሳት ኾኑባቸዉ፡፡
በተለይም በየካቲት 12/ 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስብሰባ ሲመራ በነበረዉ የፋሺሽቱ እንደራሴ የነበረው ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ በነፃነት ታጋዮች የግድያ ሙከራ ተደረገበት፡፡ ሙከራዉን ተከትሎ ድርጊቱ ያበሳጨው የፋሺሽቱ ጦር ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈፀመ፡፡ ከ20,000 – 30,000 የሚገመቱ ንጹሐን ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት አኳኋን በጅምላ ተጨፈጨፉ፡፡ ዕለቱም እስከ ዛሬ ድረስ የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ኾኖ ይዉላል፡፡
ምንም እንኳን የጠላት ምኞት ኢትዮጵያዊያን ዳግም ለነፃነታቸዉ እንዳይታገሉ ለማስተማር የተደረገ ቅጣት ቢኾንም እርምጃዉ ጀግኖቹን ይበልጥ አጠናከራቸዉ እንጂ ከነፃነት ትግላቸዉ ፈፅሞ ሊያስቆማቸዉ አልቻለም፡፡ እንዲያዉም ኢትዮጵያዊያን በጠላት ሲጠቁ እጅ የሚሰጡ ሳይኾኑ ይበልጥ የሚጠነክሩና እንደ ንብ አንድ የሚኾኑ፣ ለጠላት የማይመቹ ሕዝቦች መሆናቸዉን አረጋገጡ፡፡ ጭፍጨፋዉ ይበልጥ ጀግኖች አርበኞች ተደራጅተዉ ጠላትን እንዲያርበደብዱ ጉልበት ፈጠረላቸዉ እንጂ ተስፋ አላስቆረጣቸዉም፡፡ ጠላትን እንቅልፍ ነሱ፣ ብሎም ከነአካቴዉ ከሀገራችን አባረሯቸው፡፡
ይህ ለጠላት የማንመችና የማንንበረከክ፣ ነፃነት ወዳድ መኾናችን ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ጠላት ምኑንም ያህል ቢደረጅ፣ ቢዶልት፣ ቢያሴርና ቢተባበር የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዉያን ይበልጥ አንድ የመኾንና ችግርን የመቋቋም እሴት ዛሬም ሀገራችንን ከብተና አድኗል፤ ለጠላት ያለመንበርከክና አሸናፊነት የጋራ ታሪካችን ብቻም ሳይኾን የጋራ ባሕላችን ኾኖ ለትውልድ ተርፏል፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት ላልገባው ጠላት የጥንካሬአችን ምንጭ ትንግርት ኾኖበታል፡፡
ዘንድሮ የየካቲት 12 ሰማእታትን ስንዘክር የጥንካሬአችን ምንጭ የኾነዉን የመተባበር ባህላችንን በማጠናከር፣ አንድነታችንን ጠብቀን ዘርፈ ብዙ ጠላቶቻችንን በማሸነፍ ኹለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በመትጋት ሊኾን ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ ዜጎቿ መስዋእትነት የጸናች ብርቱ ሀገር ለመኾኗ የየካቲት 12 ሰማእታት ህያው ምስክሮች ናቸው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
