“በጠላት ላይ በአንድነት እንደዘመትነው ሁሉ ሀገር ከእኛ በምትፈልጋቸው ጉዳዮች ቀድመን በመገኘት ለሀገር ግንባታ በአንድነት መሥራት ያስፈልጋል” የሰሜን ሸዋ ዞን ጀግኖች አርበኞች

86

ደብረ ብርሃን: የካቲት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ)
ኸረ ጥራኝ ጫካው ኸረ ጥራኝ ዱሩ
ላንተም ይሻልሀል ብቻን ከማደሩ!

ሰዎች መገፋት ሲበዛባቸው ለነፃነታቸው ፍኖት ጅማሮ የሚያደርጉት በሽለላ ነው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ በሀገራቸው ጉዳይ ለመጣባቸው ጠላት ክንዳቸው የበረታ ነው።

“እንኳን ከጎረቤት ከወንዜ ለጠጣ፣
ቋያ እሳት ነው ክንዴ ከሩቅም ለመጣ” እንዳለ ከያኒው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሀገራቸውን ከጠላት ወረራ መክተው ለዚህ ትውልድ አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በእውር ድንበር ጉዞ ከቅርብም ከሩቅም በተለያዩ ጊዜያት የወረራ ሙከራ ቢያደርጉም ከምኞት የዘለለ አልሆነም። ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይነጥፍ፣ ላይከስም፣ ላይፋቅ እና ላይደበዝዝ ልክ እንደ ሰንደቋ ከፍ ባለ የሥነ ልቦና ልዕልና አንዴ ተሰቅሏልና ጠላቶቿ ሊደፍሯት ከቶም አልቻሉም።

መላ አፍሪካ በጨለማ ተውጦ ባለበት በዚያ ዘመን የብርሃን ችቦ ይዛ ብቅ ያለችው ኢትዮጵያ ባሕር ተሻግሮ የመጣን ጠላት በአድዋ ሰንሰለታማ ተራራዎች ቀብራ የነፃነት ቀንዲልነትን አሳይታለች።

ኢትዮጵያን ቀኝ ለመግዛት አልሞ ህልሙ እንደ ጠዋት ጤዛ ረግፎ፣ እንደ ጉም በኖ የቀረው ፋሽስቱ ጣሊያን ዳግም ለመውረር ወደ በመጣ ጊዜም ኢትዮጵያውያን በእሳት አለሎ አቃጥለው ልኩን አሳይተውታል።

ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰሜን ሸዋ ዞን ጀግኖች አርበኞች ማኀበር አባላት ኢትዮጵያዊነት አይደፈሬነት፣ ጀግንነትና ለሀገር መሞት ነው ይላሉ።

“ጀብዱ በጦር ሜዳ ይሠራል። አባቶቻችን የተዋጣላቸው ጀብደኞች ናቸው” ያሉት የሰሜን ሸዋ ዞን ጀግኖች አርበኞች ማኀበር ዋና ፀሐፊ አባት አርበኛ ተፈራ ወልደ አማኑኤል ናቸው ። “ጀብዱ መሥራት ከጦር ሜዳ ውሎ የተሻገረ ሀገር መገንባትንም ይጠይቃል” ነው ያሉት።
ከሩቅም ከቅርብም የመጣ ጠላት ኢትዮጵያን የማይደፍረው ኢትዮጵያዊነት የሚባል ጠንካራ ገመድ ስላስተሳሰረን ነው ብለዋል አባት አርበኛው።

ሁሌም ጦርነትን ሳንጠብቅ ሀገርን ማስከበር እንችላለን የሚሉት ጀግኖች አባት አርበኞች ትውልዱ በየተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ ውጤታማ ሥራን በመሥራት ሀገሩን ማስከበር ይጠበቅበታል ብለዋል።

“ትላንት አባቶቻችን የሠሩት ገድል እልፍ ዓመታትን የሚሻገር ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የእነዛ ጀግኖች ልጆች ነን። ስለሆነም በጠላት ላይ በአንድነት እንደዘመትነው ሁሉ ሀገር ከእኛ በምትፈልጋቸው ጉዳዮች ቀድመን በመገኘት ለሀገር ግንባታ በአንድነት መሥራት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ጀግኖች አርበኞች ማኀበር አባል አቶ ድንቅነህ ሸንክፌ መከባበርን መሰረት ያደረገ የሰከነ ውይይት በማድረግ ሊለያዩን ካሰቡ አካላት ሴራ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በልዩነት ላይ አንድነትን፣ የኀብረ ቀለም ውበትን ተላብሰን የኖርን መሆናችንን በመገንዘብ በጊዜያዊ እና ጥቃቅን ችግሮች መጠመድ የለብንም ሲሉ አስገንዘበዋል።

ጥያቄዎች ሊኖሩን ይችላሉ የሚሉት ጀግኖች አርበኞች ጥያቄዎችን ስናቀርብ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ሊጎዳ በሚችል መንገድ ሳይሆን በሰከነና በተጠና መንገድ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

ጀግኖች አርበኞች በተለያዩ አውደ ውጊያዎች የከፈሉትን መስዋእትነት እያሰብን ሀገራችን የታፈረች ሆና እንድትኖር ሁላችንም እንረባረብ የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:-ኤልያስ ፈጠነ-ከደብረብርሃን

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleʺየንፁሐን ደም በግፍ ፈሰሰ፣ ከተማዋ በዋይታ ተመላች”
Next article“የካቲት 12 እኛ ኢትዮጵያዊያን በጠላት ስንነካና ስንጠቃ ይበልጥ የምንጠናከርና የምንሰባሰብ ስለመኾናችን ምስክር ነው!” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት