ከትኬት ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እና ለወደሙ መሠረተ ልማቶች ግንባታ እንደሚውል የተገለጸው “አቅሌማ” ፊልም ለምረቃ በቃ።

205

ፊልሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ እውቅ ተዋንያን እና ታዳሚዎች በተገኙበት በባሕር ዳር ተመርቋል።

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “አቅሌማ” መቼቱን ደቡብ ጎንደር ዞን ቆራጣ ተብላ በምትጠራ አካባቢ አድርጎ ለሀገር ገጽታ ግንባታ የተሠራ ፊልም ነው።

መኳንንት በፈቃዱ ፊልም ፕሮዳክሽን ከአቤሜሌክ ኢንተርቴይንመንት ጋር ያዘጋጁት ይህ ፊልም ዘመን በቂ ጥናት የተሠራበት እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ነባር እሴት ላይ የሚያጠነጥን ነው ተብሏል፡፡ በሀገር ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በጥልቀት ይመረምራል፣ የሚያስከትሉትን ዳፋ በውል ይተነትናል፤ ለችግሮች መውጫ መንገዶችንም እንደሚያሳይ ነው የተገለጸው፡፡

ይህ የሥነ ራዕይ ጥበብ (ፊልም) ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ የተሠራ ሲሆን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት የፊልሙ አዘጋጅ እና የአቤሜሌክ ኢንተርቴይንመንት ባለቤት ነጻነት አንበርብር ገልጻለች፡፡ ከዚህ ቀደም ከሠራቻቸው የፊልም እና የድራማ ሥራዎች በይዘቱ የተለየ እና ለዘመኑ ትውልድ በእጅጉ አስፈላጊ የኪነጥበብ ሥራ መኾኑንም ተናግራለች፡፡

ፊልሙ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ሥርዓት እና ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ መፍለቂያ ተቋማት ሀገሩን ጠንቅቆ የሚያውቅና ስብዕናን የተላበሰ ዜጋ ለማፍራት የተጓዙትን ርቀት ይፈትሻል፡፡ ሰብዓዊነት ለምን እንደጠፋ፣ ትውልዱ ለምን እርስ በእርሱ ለግጭት እንደተዳረገ፣ ለምንስ እንደሚከፋፈል የማኅበራዊ ሥሪቱን ስብራት ይመረምራል፡፡ ለዚህ ኹሉ መንስዔ የኢትዮጵያዊነትን ጥልቅ ምስጢር አለመረዳት፣ ታሪክን ጠንቅቆ አለማወቅ እና የእሴቶች መሸርሸር እንደኾነም ይተነትናል፡፡

የኢትዮጵያዊነት ምስጢር ጥልቅ ነው፤ የቀደምት አያቶቻችን እሴት ድንቅ ነው፤ ታሪካችንም የችግሮቻችን ኹሉ መፍቻ ቁልፍ ነው። ይህንን ጠንቅቀን አለማወቃችን ግን የተወሳሰበ ችግር ላይ እንድንወድቅ አድርጎናል። በዚህም መነሻነት ትውልዱን ከመፈረጁ በፊት የትምሕርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ሥርዓትን እና ሌሎች ማኅበረሰብ መፍጠሪያ ተቋማት ተጠያቂነት ሊቀድም ይገባል ሲል ይሞግታል፡፡ ለደረሰብን ችግር ብቸኛ መንገዱ ኢትዮጵያዊነትን በውል መረዳት እና መንፈሱን መላበስ ነው፡፡

በከያንያን ድንቅ የትወና ብቃት እንደተዘጋጀ የተነገረለት ይህ የኪነጥበብ ሥራም እያንዳንዱ ቤተሰብ በልጆቹ ላይ በመሥራት ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ መሰረት እንዲጥል አንኳር መልዕክት ያስተላልፋል።

የፊልሙ ኹለተኛ ክፍል በቅርቡ እንደሚሠራ አዘጋጇ ተናግራለች፡፡ በኹለተኛ ክፍሉ ይበልጥ ከገጠሙን ችግሮች የምንወጣባቸው መንገዶችን ማሳየት እንደፈለገችም ገልጻለች፡፡

ጊዜው ኢትዮጵያዊያን ፈተና ውስጥ የወደቁበት ነው፤ ሀገራችን ታምማለች፣ ሕዝቦቿ እየተገደሉ፣ ብዙዎች እየተደፈሩ፣ ለጉስቁልናም እየተጋለጡ ነው፡፡ በሌላ በኩል ድርቅና ረሃብ ከባድ ፈተና ኾኖ በመቀጠሉ እርስ በእርስ መረዳዳት በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

ነጻነት እንዳለችው ❝የፊልም ኢንዱስትሪው ቀጣይነት እና ውጤታማነት የሚኖረው የሕዝብ ኅልውና ሲረጋገጥ ብቻ ነው። የኢትዮጵያዊነት ልክ በችግር ጊዜ አንዱ ሌላውን በሚችለው አግባብ መደገፍ ነው፡፡ ሕዝብና ሀገር በዚህ ደረጃ ችግር ውስጥ በወደቁ ጊዜ የመፍትሔ አካል መኾን ደግሞ የምርጫ ጉዳይ አይደለም❞ ባይ ናት።

ፊልሙ እያዝናና ከሚሰጠው ትምሕርትና ከሀገር ገጽታ ግንባታ ፋይዳ ባለፈ ከምርቃት መርኃግብሩ የትኬት ሽያጭ የሚገኘውን ገንዘብ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እና ለወደሙ መሠረተ ልማቶች ማሟያ እንዲኾን ተወስኗል። ፊልሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ እውቅ ተዋንያን እና ታዳሚዎች በተገኙበት በባሕር ዳር ተመርቋል።

አቅም ያለው ትኬት በመግዛት፣ ትኬት የመግዛት አቅም የሌለው ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝ፣ ዘይት እና የመሳሉ ድጋፎችን ይዞ በመቅረብ ማኅበራዊ ኀላፊነትን ሊወጣ ይችላል፤ ይህን ማድረግ የማይችል ደግሞ ሐሳቡን ለሌሎች በማካፈል ትብብር እንዲያደርግ ጠይቃለች፡፡

በኪነጥበብ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትም መሠል ተግባራትን በመከወን ሕዝባቸውን ሊታደጉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፋለች።

ፊልሙ በቀጣይ ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ የሚመረቅ ሲኾን በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎችም ይቀጥላል፡፡ ከዚህ የሚገኘው ገቢም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲውል ይደረጋል ተብሏል።

ከምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ውጪ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራው ቀጣይነት ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡ ከዚህ ቀደም በተጀማመሩ ሥራዎች የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ባይቻልም አበረታች ኹኔታዎች መኖራቸውን ነጻነት ጠቅሳለች።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት(ዩኤንዲፒ) ዋና ኃላፊ ቱርሃን ሳልህና ሌሎች የልማት ድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች አሸባሪ ቡድኑ በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ያደረሰውን ጉዳት ተመለከቱ።
Next article❝የቀደሙት አያቶቻችን በመስዋእትነት ነፃነቷን ጠብቀው ያቆዩልንን ሀገር ከነክብሯና ነፃነቷ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ግዴታ አለብን❞ ዶክተር ሂሩት ካሳው