
የካቲት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2014 ዓ.ም ከ8 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ እንደሚለሙ አስታውቋል፡፡ በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር እስመለዓለም ምሕረት በተለይ ለአሚኮ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራው በክልል ደረጃ በንቅናቄ መጀመሩን ተናግረዋል።
ንቅናቄው በክልል ደረጃ ይጀመር እንጂ እንደ ዞኖች እና ወረዳዎች ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ሥራ ያልገቡ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች የሥራ መሳሪያ እና የሚሠራ የሰው ኀይል የመለየት ተግባር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የመኸር ሰብል ዘግይቶ በሚደርስባቸው ወረዳዎች ሥራው እንዳልተጀመረ ያነሱት ዳይሬክተሩ ቀድመው በጀመሩ አካባቢዎች ልማቱ በተጠናከረ መንገድ እየተከወነ መኾኑን ተናግረዋል። አሸባሪው ቡድን በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች የለሙ ተፋሰሶችን በማውደሙ አዳዲስ ተፋሰሶች ለመሥራት ሳይኾን የወደሙትን ለመጠገን ጥረት እንደሚደረግ ነው አቶ እስመለዓለም ያስረዱት።
እስካሁን በተሠራው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ከ9 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ከልቅ ግጦሽ ነፃ ኾነው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሠጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተፋሰሶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በኅብረት ሥራ ማኅበር ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 1223 መሠረት ተፋሰሶች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ እያንዳንዱ ወረዳ አርዓያ የሚሆን ተፋሰስ መፍጠር እንዳለበትም ስምምነት ላይ መደረሱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሲከናወን በቆየው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ ተፋሰሶች አገግመው በማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ለውጥ መምጣቱን አቶ እስመለዓለም ገልጸዋል፡፡
70 በመቶ የነበረውን የአፈር መሸርሸር ወደ 30 በመቶ ዝቅ አድርጓል፤ ምርታማነትን ጨምሯል፤ ለጎርፍ መሸርሸር ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎች አገግመው ኹለት እና ሦስት ጊዜ ምርት መስጠት መጀምራቸውን አስረድተዋል፡፡ ልማቱ በእንስሳት ልማት ላይም ኹለንተናዊ ለውጥ ማምጣቱን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ከደን ውጤቶች በዓመት ከ1 ነጥብ 9፡ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እየተገኘ መሆኑን አንስተዋል።
በ2014 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ዘመቻ
.8 ሺህ 145 ተፋሰሶች ይለማሉ
. ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ
. በዘመቻው 306 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል
ዘመቻው በተጀመረባቸው አካባቢዎች በተጠናከረ መንገድ እየተካሄደ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡ ንቅናቄው በሚካሄድባቸው ኹሉም ወረዳዎች አርዓያ ተፋሰስ ለመፍጠር እየሠሩ መኾኑን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
