
የካቲት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በዓድዋ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል አራት አስርት ዓመታትን ተዘጋጅታ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጰያን የወረርችው ጣሊያን በርካታ ሰብዓዊነት የጎደለው ግፍ በኢትዮጰያውያን ላይ ፈጽማለች፡፡ በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከተገኙበት የጦር ግንባር ጀምሮ ጣሊያን ባሰለፈቻቸው 400 አውሮፕላን በመታገዝ አሰቃቂ መርዝ በሕዝቡ ላይ በመርጨት ኢ-ሞራላዊ እና ኢ-ሰብዓዊ ወንጀሎችን ፈጽማለች፡፡
የፋሽስቷ ጣሊያን የጦር መሪ ጀኔራል ግራዚያኒ አንድም በኔፕልስ አዲስ ልዑል መወለድን ምክንያት በማድረግ፤ ሌላም በደቡብ ኢትዮጵያ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት አለመጎዳቱን ለሕዝብ ለማሳየት የካቲት 12/1929 ዓ.ም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት እንዲሰበሰብ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡
ግራዚያኒ የጣሊያንን መንግሥት ኃያልነት እና ቸርነት ሲደስኩር ያልታሰበ ክስተት ተፈጠረ፡፡ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ወጣቶች አከታትለው ሦስት ቦምብ ወደ መድረኩ ወረወሩ፡፡ ግራዚያኒ ቆስሎ ወደ ያኔው ኦስፔዳሌ ኢጣሊያኖ ወይም ወደ አሁኑ ራስ ደስታ ሆስፒታል ገባ፡፡ ይህን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጰያውንን ለማጥፋት የቋመጠው የጣሊያን ጦር ከየካቲት 12/1928 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባና አካባቢው 30 ሺህ ዜጎችን ጨፈጨፈ፡፡
በጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የታሪክ መምህር አቶ አሳምነው ዱባለ ክስተቱ በዕለቱ ከነበረው አጋጣሚ በላይ ጣሊያን ለረጅም ጊዜ ተዘጋጅታ ትጠብቀው የነበረው የበቀል እርምጃ ማሳያ መኾኑን ይናገራሉ፡፡ 40 ዓመታትን ሙሉ የተዘጋጀችው ለበቀል በመኾኑ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ የፈፀመችው ግፍ የእብሪቷ ማሳያ መኾኑን በርካታ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያውያን ግፍና መከራ ሲደርስባቸው አሜን ብለው አንገታቸውን እንደማይደፉ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ ዛሬ በዚህ ዘመንም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በፈፀመው አስነዋሪ ወንጀል ታሪክ የማይረሳው ግፍ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ቢፈፀምም አንገቱን ደፍቶ እና ሥነ ልቦናው ተጎድቶ የሚቆዝም ሕዝብ የለም። ከዚያ ይልቅ ከደረሰበት ጉዳት በፍጥነት አገግሞ ጠላትን የሚመክት ሕዝብ ነው ያለው ይላሉ መምህሩ። ከታሪክም ይህን ነው የምንማረው ነው ያሉት።
የካቲት 12/1929 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ያደረሰው ጭፍጨፋ ኹሉም በተለያየ መልክ ለሀገሩ ነፃነት ይበልጥ እንዲታገል ምክንያት ኾኗል ይላሉ የታሪክ መምህሩ፡፡ በገጠራማው ክፍል ብቻ ተወስኖ የነበረው አርበኝነት ይበልጥ እንዲቀጣጠልና የውስጥ አርበኝነትም በከተማ እንዲጠናከር ክስተቱ ምክንያት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ ዛሬም ሀገር የሚያፀና መንፈሳዊ ምሰሶ ነው ባይ ናቸው። ትውልዱ የነፃነትን ዋጋ ከጀግኖች አባቶች ተጋድሎ መማር እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድም ለፋሽስት ያደሩ የባንዳ ልጆች ለፈጸሙት ግፍ ተንበርካኪ እንደማይኾን አሳይቷል ብለዋል።
ጠላት ሊገዛን ሲፈልግ በዘር፣ በሃይማኖት እና በተለያየ አመለካከት በመከፋፈል፤ ሊያጠፋን ሲፈልግ ደግሞ በጅምላ ያለ ልዩነት መሆኑን የተናገሩት አቶ አሳምነው ከዚህም ፋሽስት ሰራሹ የዘር ክፍፍል ርዕዮት አንድነትን እንደሚያላላ እንዲሁም ጠላት ሲያጠቃ በጅምላ መኾኑን በመረዳት ከነበረው ክስተት የአሁኑ ትውልድ ሊማርበት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የታሪክ መምህሩ ነፃነቷ የተነጠቀ ተንበርካኪ ሀገር ለልጆቻችን አናስተላልፍም ያሉ አርበኞች በዱር በገደል ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው እና አንድያ ነብሳቸውን ሰጥተው ሰንደቋ ከፍ ያለች ኢትዮጵያን አቆይተዋል ነው ያሉት፡፡
የአሁኑ ትውልድም ነፃ እና ሉዓላዊነቷ በዓለም አደባባይ ከፍ ያለች ኢትዮጵያን ካስረከቡን ጀግኖች አርበኞች የነፃነት ዋጋ ተመን እንደሌለው ተረድቶ ዛሬም የሀገሩን ነጻነት ጠብቆ ለማስቀጠል ባለበት ሙያ ኹሉ የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ -ከጎንደር
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/