
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሳይነኩት የማይነካ፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚለካ፣ ለጠላት የማይበገር፣ ሀገር ለማጽናት የሚተባበር፣ ሀገሩን የሚነኩበትን እጆች አስቀድሞ የሚሰብር፣ በግፍ የሚራመዱ እግሮችን የሚያሳጥር ጀግና ሕዝብ፡፡ መራዥ ተኳሽ፣ ዋልካና ረባዳማ መሬት አንደፋርሶ አራሽ፣ በሰርክ ፀሎት አድራሽ፣ ታሪክ ሠሪ፣ ታሪክ ጠቃሽ፡፡
በገፉት ቁጥር የሚጠነክር፣ በተንነው ሲሉት የሚያብር፣ ጀግንነቱ ወሰን ያልተገኘለት፣ ለጀብደኝነቱ ወደር ያልተፈጠረለት ድንቅ ሕዝብ፡፡ ጠላቶች በየዘመናቱ ፈተና አብዝተውበታል፣ ጦር አዝምተውበታል፣ በክብሩና በሠንደቁ መጥተውበታል፤ እርሱም የመጡትን ሁሉ በከንዱ መክቶ፣ ጀግንነቱን አሳይቶ ደምስሷቸዋል፡፡
ጦረኝነቱን ለእኔ ተውት ይላቸዋል፡፡ ተመልክት ቦሎ መተኮስ፣ ኮሎና ወይኖን፣ ዘገርና ይመርቀንን፣ ኳሊና ሸምላን ማረስ፣ በሰፊ አውድማ ላይ ወተት የመሰለ ነጭ ጤፍ ማፈስ፣ በአሻገር የመጣን ጠላት መመለስ፣ ነገሦ ማንገሥ፣ እኔ አውቅበታለሁ፣ ተወልጄ አድጌበታለሁ ይላቸዋል፡፡
እስከሞት ድረስ ያፈቅራል፣ ሀገርና ሠንደቁን ከነብሱ አስበልጦ ይወዳል፣ ታምኖ መኖር፣ አምኖ ማደር ደግ ነው ይላል፡፡ ምንም ነገር ቢፈጠር ካመነ አይከዳም፣ እምነቱን ከሚያጎድል በክብር ቢያልፍ ይመርጣል፡፡ ክብር ከምንም ነገር በላይ ናትና፡፡
ሲያምናቸው የሚከዱትን፣ ሲዋጋላቸው ከጀርባው የሚወጉትን፣ ሲደግፋቸው የሚገፉትን፣ ሲያቀርባቸው የሚያርቁትን አምርሮ ይታገላቸዋል፡፡ እርሱ ካመኑት የማይከዳ፣ ከተነሳ የማያወላዳ፣ ኩሩና ጀግና ነውና፡፡ መውደድ ያውቅበታል፡፡ ፈትፍቶ ያጎርሳል፣ የክብር ልብስ ያለብሳል፣ በጠጅና ጠላ፣ በወይና ፍርዱስ የተጠማን አንጀት ያርሳል፣ ክብሩን በክንዱ አስከብሯል፣ በአሸናፊነት ኖሯል፣ በጀግንነት ከብሯል አማራ፡፡ ወደፊትም በጀግንነት ይኖራል፡፡
የጀግንነት ትጥቁ አይላላም፣ መሳሪያው አያብልም፣ ተኩሶም አይስትም፣ በመከራዎች ብዛት አይደነግጥም፣ በጠላቶች ድምጽ አይናወጽም፣ በጽናት ወደፊት ብቻ ይገሰግሳል፣ ሁሉንም እያሸነፈ ከሚጠበቅበት የከፍታ ማማ ላይ ይደርሳል፡፡
በአያሌ አውደ ውጊያዎች ተዋግቷል፣ በአሸናፊነትም ተወጥቷል፡፡ አትንኩኝ ሲል የሚነኩት፣ በግፍ የሚወጉት፣ የሚዋጉት በተነሱ ቁጥር ፎክሮ እየተነሳ በማይስተው አፈሙዙ ነጥሎ እየጣለ አስቀርቷቸዋል፡፡ ጠመንጃ ባልነበረበት፣ ከባድ መሳሪያ ባልተጫነበት ቀደም ባለው ዘመን ጋሻ እየያዘ፣ ጎራዴውን ከሰገባው እየመዘዘ፣ በሰይፍ እየቀላ፣ በጦር እየወጋ ሀገር አስከብሯል፡፡
በረጅም ዘመናት ታሪኩ አስቸጋሪ ጊዜያት ገጥመውት ያውቃሉ፡፡ ለችግሮቹ ማሸነፊያ መፍትሔ ያጣዘት ዘመን ግን አልነበረም፡፡ በፍቅር የሚፈታውን በፍቅር፣ በጦር የሚፈታውን በጦር እየፈታ ከታሪክ ላይ ታሪክ እየጨመረ ኖረ እንጂ፡፡ መፍትሔዎቹ ሁሉ ክብሩን የሚያስጠብቁ ናቸው፡፡ ክብሩን ከሚያወርድ፣ ታሪኩን ከሚንድ ማንኛውም ሰው ጋር አይደራደርም፤ የሠንደቋን ከፍታ እንዳስጠበቀ፣ ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ እንዳላቀ ይኖራል እንጂ፡፡
ብልሃት፣ ጀግንነት፣ አርቆ አሳቢነትና አንድነት ከእርሱ ጋር ናቸውና በጥበብ ይፈታቸዋል፡፡ በድል አድራጊነት ይሻገራቸዋል፡፡ የትኛውም የችግር ውኃ ሙላት ከመንገዱ አስቀርቶት አያውቅም፡፡ ሙላቱን እየተሻገረ ከሙላቱ ባሻገር ባለው መልካም መስክ ይኖራል እንጂ፡፡ ዛሬም መንገድ ለማሳጣት፣ ከወንዙ ማዶ ሳይሻገር ለማስቀረት የሚጥሩት ብዙዎች ናቸው፡፡ እርሱ ግን በተለመደ ጥበቡ ይሻገራቸዋል፣ ያልፋቸዋል፣ ጠላቶቹን አሳፍሮ በክብር ይራመዳል፡፡ ከፈለገበት ሥፍራም ይደርሳል፡፡
በድል አድራጊነት ቀና ያለ ነፍጥ፣ በአሸናፊነት የሚራመድ ሕዝብ ነውና የትኛውንም ችግር ያልፈዋል፡፡ በአባቶቹ ጀግንነት ቀና ያለው ነፍጥ በልጆቹም ቀና እንዳለ ይኖራል፡፡ ጀግና ነፍጡን አይዘቀዝቅም፣ አንገቱንም አይደፋምና፡፡ የአተኳኮስ ታሪኩን እያወሱ ዝቅ ሊያደርጉት ከጀላቸው፣ እርሱ ግን ተኩሶ ጣላቸው፡፡ በአርበኝነት ስሙ እየጠሩ ሊሳለቁበት አማራቸው እርሱ ግን በጀግንነቱ ድል መታቸው፡፡ የሚያኮራ ታሪክ የተቀበለው፣ ከጀግና ምድር ከጀግኖች አብራክ የወጣው ጀግና ዛሬም በአሸናፊነት ይራመዳል፡፡ ማንም ጠላት ከፊቱ ላይ አይቆምም፡፡ ጠላቶች በማይደበዝዝ ብዕር፣ በማይቀደድ ብርና የተጻፈውን ታሪኩን ሊያጠለሹት፣ ቢሳካላቸው ሊያጠፉት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን የተጻፈበት ቀለምና የሰፈረበት ብራና ከጠላቶች አቅም በላይ ሆነና አልቻሉትም፡፡
ታሪኩን የጻፈው በላብ ብዛት፣ በደምና በአጥንት ክስካሽ ነውና ማንም ተነስቶ ሊፍቀው አይቻለውም፡፡ በየአቅጣጫው ሊያጠቁት የሚቋምጡ ጠላቶች ሞልተዋል፡፡ አንገት ሊያስደፉት፣ ክብሩን ሊነኩት የሚሹት ብዙዎች ናቸው፡፡ ታዲያ ለእነዚህ ጠላቶቹ አንገቱን ቀና አድርጎ፣ በአንድነት ቆሞ፣ እንደ ቀደመው ሁሉ ጀግንነቱን ማሳዬት ግድ ይለዋል፡፡
የአማራ ጀግኖች ለሀገርና ለሕዝብ ክብር ሲሉ በዱር ገደሉ ይዋደቃሉ፣ አሸናፊውን ነፍጣቸውን በኩራት ያነሳሉ፡፡ የእውነት፣ በእውነት፣ ስለእውነት ለሀገራቸው ይቆማሉ፡፡
አማራ ዛሬም ጠላቶች በዝተውበታል፣ ጦር አንስተው፣ ጦረኛ ልከው የሚዋጉት አሉ፡፡ ጦረኞቹን ተከትለው ለመግባት የሚሹም ብዙዎች ናቸው፡፡ አባቶቻቸው ባሕር አቋርጠው፣ የብስ ረግጠው ጦርነት ገጥመው ያልተሳካላቸው የውጭ ጠላቶቹም አይዟችሁ ይሏቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከፍ እንዳለች እንድትኖር፣ በክንዷ እንድትከበር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ኾኖ የተዋጋቸው ጠላቶች የበዙበት ሕዝብ ነውና ይጠሉታል፡፡ በመጥላታቸው ውስጥ ደግሞ አብዝተው ይፈሩታል፡፡ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ ክንዱ ደቋሽ ነውና ያከብሩታል፡፡ ወድደው አይደለም የሚያከብሩት፣ ወድደው አይደለም የሚፈሩት፣ በሠንደቅና በሀገር ክብር ስለማይደራደር፣ ለጦርነት ስለማይበገር እንጂ፡፡
የቀደሙት አባቶች ድል ያመጡት ከመዘላለፍ እንደጋገፍ፣ ከመነቃቀፍ እንተቃቀፍ፣ ከመለያዬት አንድነት ይሻላል ስላሉ ነው፡፡ አንድነት ድል እንደሚያመጣ፣ አንድነት የድል ፀሐይ እንደሚያወጣ አስቀድመው ያውቃሉና፡፡ አንድነታቸውን ይጠብቁታል፡፡ በአንድነታቸውም ይሻገሩበታል፡፡
ዛሬም እንደ አባቶች በአንድነት በመቆም በአሸናፊነት መራመድ ግድ ይላል፡፡ ችግሮችን በመተባበር እንጂ፣ በመወቃቀስ ብቻ መፍታት አይቻልም፡፡ ዳር ቆሞ ከመውቀስ ገባ ብሎ መሥራት፣ ለምን አይሰሩም ብሎ ከመጠየቅ በፊት ምን ሠራሁ? ማለትን ማስቀደም፡፡ ደማቅ ታሪክ የወረስነው፣ ኮርተን የምንራመደው፣ ታሪክ የምንናገረው አባቶችና እናቶች በአንድነትና በጀግንት ሠርተው ስላስረከቡን ነው፡፡ በጋራ ሥራና ቀና ብለህ ተራመድ፡፡ በአሸናፊነት ገሥግሥ፡፡ ዝቅ የሚል አንገት፣ የሚዘቀዘቅ ነፍጥ አይኑርህ፡፡ የሚስማማህ ከፍታ ብቻ ነውና፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/