“በቃ” (#Nomore) ንቅናቄ – የፓን አፍሪካኒዝም ማስፈጸሚያ አንዱ መንገድ

261

የካቲት 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ቅኝ ገዥዎች የሰው ኃይል ለመበዝበዝ፣ ጥሬ ሃብት ለማጋበስ እና የሸቀጣ ሸቀጦቻቸው ማራገፊያ ገበያ ለማግኘት ዋነኛ ትኩረት ካደረጉባቸው አህጉራት አንዱ አፍሪካ ነበር፡፡ ቅኝ ገዥዎች ለዚህ መሻታቸው ደግሞ አፍሪካን ለመቀራመት ሞክረዋል። የነጻነት ቀንዲሏን ኢትዮጵያን ሳይጨምር አፍሪካውያን ለ500 ዓመታት ያህል በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች እጅ ቆይተዋል፡፡ በዚህ የቅኝ ገዥዎች ጭቆና የተንገሸገሹት ጥቁር ሕዝቦች በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ፓን አፍሪካኒዝንም ወይንም የአፍሪካ አንድነት እንቅስቃሴን አቀጣጠሉት፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካ ለአፍሪካውያን ቅኝ ግዛትን እና የነጭ የበላይነትን በመቃወም መላው አፍሪካን ነፃ ማድረግ፣ በአንድነት የተሳሰረ አህጉር መመስረት፣ አፍሪካውያንን ወደ ራሳቸው ማንነት መመለስ፣ በአፍሪካ የባሕል ህዳሴ እና የኢኮኖሚ ተሃድሶ ማምጣት እና መሰል ዓላማዎችን ይዞ ነበር የተነሳው፡፡ በተለይም ደግሞ በ1888 ዓ.ም ከዓድዋ ድል በኋላ የጥቁር ሕዝቦች ጸረ ቅኝ ገዢ ትግል የበለጠ እንዲጎለብት አድርጓል፡፡
ሳሞራ ቱሬ በምዕራብ አፍሪካ ሕዝቡን አስተባብሮ በፈረንሳይ ላይ ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ፈረንሳይ ምዕራብ አፍሪካን ለመቆጣጠር ያደረገችውን ግስጋሴ እንዲገታ አድርጓል፡፡ ይህ ትግል የፓን አፍሪካኒዚም እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጓል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር መምህር የሽዋስ እስከዚያው እንዳሉት የመላው አፍሪካ ንቅናቄ ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ እስከ 1950 (እ.አ.አ) ትልቅ ደረጃ ደርሶ የነበረ የጥቁር ሕዝቦች ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ ንቅናቄ ነው፡፡ የዚህ ንቅናቄ መነሻ ደግሞ በካሪቢያን ሀገራት እና በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩ ጥቁሮች ይደርስባቸው የነበረውን የዘር መድልኦ፣ ባርነት እና ቅኝ አገዛዝ ጫናዎችን ለመታገል ያለመ እንደነበር አንስተዋል።
እንደ መምህር የሽዋስ ገለጻ የንቅናቄው ዓላማ በተለይም ደግሞ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ባርነትን እና ቅኝ አገዛዝን ከአፍሪካ ማስወገድ እና አንድ አፍሪካን ለመፍጠር ያለመ ነበር። በዚህም በርካታ ጉባኤዎችን በማካሄድ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። በተለይም ደግሞ (እ.አ.አ) በ1945 በእንግሊዝ የተካሄደው የፓን አፍሪካኒዝም ጉባኤም የአፍሪካ ምሁራን የተሳተፉበት ነበር፡፡ በዚህም የአፍሪካን ነፃነት በይፋ በማቀንቀን ከቅኝ አገዛዝ፣ ከባርነት እና ጭቆና ሥርዓት እንዲላቀቁ አድርጓል፡፡ በመላ ዓለም ይኖሩ የነበሩ ጥቁር ሕዝቦችን በአንድነት አስተሳስሯል፡፡ ከቅኝ አገዛዝ በፊት የነበረው የአፍሪካ ዕሴቶችን ምሁራን እንደገና እንዲያጠኑ እና እንዲመረምሩ እድል ሰጥቷል፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም እነዚህን ለውጦች ቢያመጣም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የነበረውን ፍጥነት ይዞ ሊጓዝ አለመቻሉን ነው መምህር የሽዋስ ያነሱት፡፡ በተለይም ደግሞ አፍሪካ ነፃ ከኾነች በኋላ አፍሪካውያን የውጭን ጫና ለመቋቋም ፓን አፍሪካኒዚምን እንቅስቃሴ እየተጠቀሙበት አለመኾኑ እንደምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ፓን አፍሪካኒዝም በፖለቲካዊ ነፃነት ላይ የተቀዳጀውን ድል ያህል የኢኮኖሚ ነፃነትን አብሮ ይዞ መምጣት አልቻለም፡፡ በአፍሪካውያን መካከል ፖለቲካዊ ውህደት እና የኢኮኖሚ ትብብርን አልፈጠረም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፓን አፍሪካኒዝምን አስመልክቶ የጠራና በምክንያት የተደገፈ ስትራቴጂ አለመኖሩን አንስተዋል።
ፓን አፍሪካኒዝም ሰፊ አስተሳሰብ እንደኾነ ያነሱት አቶ የሽዋስ በቅርቡ አንዳንድ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ያደረጉትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በመላው ዓለም ላይ እየተደረገ ያለው የ”በቃ” (#Nomore) ንቅናቄ የፓን አፍሪካኒዝም ዓላማዎች ማሳኪያ አንዱ መንገድ እንደኾነ ነው ያነሱት፡፡ የበቃ ንቅናቄም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመቃወም የተደረገ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ በዘመቻውም እንደ ፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ የአንዳንድ ምዕራባውያንን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ጣልቃ ገብነት እና ብዝበዛ ተቃውሞ እና ውግዘት ተንጸባርቆበታል፡፡ አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉም አሳይቷል፡፡
የበቃ ንቅናቄ በዋናነት በኢትዮጵያ ላይ የተዘረጉ የጣልቃ ገብነት እጆች እንዲሰበሰቡ በኢትዮጵያውያን ቢቀነቀንም በሂደት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት፣ በካረቢያን፣ በአሜሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች፣ ፖለቲከኞች እና ምሁራንም ዘመቻውን መቀላቀላቸውን መምህሩ አንስተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በምዕራብ አፍሪካ የፈረንሳይን ጣልቃ ገብነት ለመቃወም ዘመቻ መካሄዱን ለአብነት አንስተዋል፡፡ የዴንማርክን ጦርም ማስወጣት ተችሏል፡፡
የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንደገና እንዲቀጣጠል፣ በአፍሪካውያን መካከል ትስስርን እና የዓላማ አንድነትን ለመፍጠር ዕድል ሰጥቷል ብለዋል። የዲፕሎማሲ የበላይነትን ማግኘት ቢቻልም የመጨረሻ ግቡን መትቷል ማለት እንዳልኾነ ነው መምህር የሽዋስ ያስገነዘቡት፡፡
የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት ለመቋቋም ከተፈለገ አኹን የተጀመረውን የበቃ ንቅናቄ በታቀደ እና በተጠና መንገድ ማካሔድ ያስፈልጋል ሲሉም ምክረ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ዘመቻውን ወደ ፓን አፍሪካኒዝም ማሳደግ እና ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ከጥቂት ምሁራን፣ ወጣቶች እና ፖለቲከኛ አቀንቃኝነት ወደ መላው አፍሪካውያን ተሳታፊነት ማምጣት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለበቃ ንቅናቄ ብዙኀን መገናኛ በሰፊው መጠቀም ሌላው እና ዋነኛው ስልት መኾኑን ነው የመከሩት፡፡ ይህ ካልኾነ ግን ምዕራባውያን አፍሪካን እንደፈለጉ እንዲቀራመጡ ዕድል እንደሚፈጥር ነው ያስጠነቀቁት፡፡
ተጨማሪ የመረጃ ምንጭ፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና ፓን አፍሪካኒዝም (ኤርሚያስ ጉልላት 2009) መጽሐፍ
በዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com

Previous articleአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሐን ላይ ጭፍጨፋ፣ ዘረፋ እና አስገድዶ መድፈር መፈጸሙን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የልዑካን ቡድናቸው ስድስተኛውን የአውሮፓ ኅብረት እና የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች የጋራ ጉባኤ ለመታደም በቤልጂየም ብራሰልስ ተገኝተዋል።