
ባሕር ዳር: የካቲት 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሐሰተኛ ትርክቶች ማሳያ ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ሐውልት ትክክለኛ ወካይ የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡ የዚህ አካል የሆነው የኪነ ቅርጾች ምረቃ ዛሬ በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡
ማዕከሉ በአማራ ሕዝብ ሀብት የተሠራ ቢሆንም በስልታዊ መንገድ የሕዝቡ ትክክለኛ ወካይ እንዳይሆን በመደረጉ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ነበር፡፡ ከስያሜው ጀምሮ ማዕከሉ ከ1973 እስከ 1983 ዓ.ም ያሉትን የ10 ዓመታት ታሪክ ብቻ የሚያንጸባርቅ እንደነበር የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ኀላፊ አዲስ በየነ ገልጸዋል፡፡ በውስጡ የሚገኙ ኪነ ቅርጾችና ማሕደረ ስዕሎችም የሕዝቡን ትክክለኛ ታሪክ፣ ሥነ ልቦና፣ ቋንቋ፣ የጀግንነት ወኔ፣ የሀገረ መንግሥት ምስረታና የተጋድሎ ታሪክ የማይወክል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ማዕከሉ እንዲቀየርም ከፍተኛ የሕዝብ ግፊት ነበረበት፡፡
በዚህም መሠረት የአማራ ሕዝብን የረጅም ዘመናት ታሪክ መሠረት በማድረግ በጥናት ላይ የተመሠረተ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ ማስተካከያው አዲስ እየተፈጠሩ ያሉ ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮችን ጭምር ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሠራ መሆኑን አቶ አዲስ አብራርተዋል፡፡ በማዕከሉ ውስጥ የሚገኝ ቤተ መዘክርና ማሕደረ ስዕሎች የአማራ ሕዝብን የጥንታዊ፣ የመካከለኛ እና ዘመናዊ ታሪኮች ባካተተ መልኩ ተስተካክለዋል፡፡
ሕዝቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲያድርበት አሁንም የተነሱ ቅሬታዎችን በሙሉ የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በግቢው የሚገኝን 27 ሄክታር መሬት በዘመናዊ መልኩ ለማልማት ልምድና ዕውቀት ባካበቱ ባለሙያዎች ዲዛይን ተሠርቷል፡፡ በቅርቡም ወደ ሥራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ የሺጥላ እንዳሉት ለሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቀ ሴራ እና ደባ የፈጠራቸው የሕዝብ መብትና ጥቅም መነጠቅ ድምር ውጤት ሀገራዊ ለውጥ አስከትሏል፡፡ የአማራ ሕዝብ አንድነት እንዲሸረሸርም በታሪኩ፣ በባሕሉ፣ በቋንቋው እና በማንነቱ ስውር ደባ ተፈጽሟል ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ማዕከሉ የነበረው ቁመና የአሸባሪው ትህነግ ሴራ ስለነበረበት የአማራ ክልልን ጥንተ ታሪክ የሚወክል፣ የክልሉን ሕዝብ ብዝኀነት እና ሁለንተናዊ ቁመና የማይገልጽ ነበር ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ያዘነ፣ የተከዘ፣ ባዕድነት እና ገለልተኝነት እንዲሠማው የሚያደርጉ፣ የጀግንነት እና የአርበኝነት ታሪኩን የሚያደበዝዙ ነገሮችን የያዘና ከሐሰተኛ ትርክቶች መገለጫ አንደኛው ነበር ነው ያሉት፡፡
እንደ አቶ ግርማ ማብራሪያ በሀሰት ሲተረክ የነበረውን እሳቤ በማስወገድ ሕዝቡን ሊወክል የሚችል ትክክለኛ ዝክረ ታሪክ ማዕከል እንዲኖር ሕጸጾች እንዲስተካከሉ ተደርጓል፡፡ ማስተካከያው የሕዝቡን ታሪክ በሚያውቁ እውነተኛ ሰዎች አማካኝነት ክልሉን በሚወክልና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አንድነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተሠራ ነው፡፡
‹‹አይበገሬው አማራ ለጠላቱ የማይታጠፍ ክንድ ያለው፤ ለወዳጆቹ ፍቅር የሚለግስ ነው›› ያሉት አቶ ግርማ ዛሬም ከታሪካዊ ጠላቶቹ ጋር በጀግንነት እየተፋለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከሉ የትናንት እና የዛሬ ተጋድሎን በሚገልጽ መልኩ እንዲስተካከል ተደርጓል፡፡ አማራ በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ቅርስ እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችም ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡
አሁን መስዋእትነት ከፍለው ሀገራቸውን ለታደጉት እና በጀግንነት እየተዋደቁ ላሉ የአማራ ልጆች አንድ ኪነቅርጽ ለማሠራት እቅድ መያዙም ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/