
የካቲት 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለቃል ኪዳን ሲሉ ከሞት ጋር ተፋጠጡ፣ ለሰብዓዊነት ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፣ ቃልን ሳያጎድሉ መሞት፣ ከእነ ክብር መሰናበት ይሻላል አሉ፡፡ በሚመችም በማይመችም ዘመን ለቃላቸው አድረዋል፣ እምነታቸውን ጠብቀዋል፣ ያ ገና በለጋ እድሜያቸው ቀኝ እጃቸውን አንስተው ያሠሩትን ቃል ኪዳን፣ የገቡትን ማሕላ አጥብቀው ይዘዋል፡፡ በመልካሙ ዘመን ቃላቸውን ይጠብቁ ነበር፣ በክፉው ዘመንም ቃላቸውን የበለጠ ጠብቀዋል፣ ለእርሳቸው ቃል ኪዳን በድሎት ዘመን የሚይዙት፣ በክፉ ዘመን የሚጥሉት አልነበረም፡፡ ከልባቸው ላይ የጻፉት፣ እስከ ሕይዎት ፍጻሜ ድረስ የሚጠብቁት፣ ከፍም አድርገው የሚያከብሩት ነው እንጂ፡፡
በመከራ ቀን መጽናት፣ ክፉውን ቀን በጽናት ማለፍ ምን አይነት መታደል ነው? ገና በልጅነት ዘመናቸው ከመምህር አባታቸው የወረሱት ታላቅ ነገር ነበር፡፡ ለሙያ መታመንን፡፡ በፍቅር ከተማዋ ደሴ ነው የተወለዱት፡፡ አባታቸው መምህር ነበሩ፡፡ ሙያዬ ክብር አለው የሚሉት አባት ልጆቻቸውም ሙያቸውን እንዲያከብሩ አደራ ይሏቸው ነበር፡፡ በዚያ ቅኝት ያደጉት እኒህ እናት የነርሲንግ ሙያቸውን ሲማሩ ደግሞ ታማሚ ባዩ ቁጥር የሚያለቅሱ ነርስ አስተማሯቸው፡፡ ለሙያ መታመንን በዚያ ዘመን ተማሩ፡፡ አጥብቀውም ያዙት ሲሰተር አልማዝ ወርቁ፡፡ የመጀመሪያ ሥራቸውን ሲቀጠሩ ራያ ቆቦ ውስጥ አምዜ ማርያም በምትባል ገጠር ነበር የጀመሩት፡፡ በአንድ ወቅት በጥይት የተመቱ ሰዎች ሕክምና ለማግኘት እርሳቸው ወደ አሉበት ይመጣሉ፡፡ ደማቸውን የሚያቆሙበት አልነበራቸውም፡፡ እኒያ ሰዎች ደግሞ ደም ይፈስሳቸዋል፡፡ አንድ ሐሳብ መጣላቸው፡፡ የሚለብሱትን የአንገት ጥምጣም (ስካርፍ) ቀድደው ደማቸው እንዳይፈስ አደረጉ፡፡ ለተጨማሪ ሕክምና ይዘዋቸውም ሄዱ፡፡ በየቤቱ እየሄዱ ኹሉ አክመዋል፡፡
ሲስተር አልማዝ የተሻለ ቦታ ሄደው መሥራት የሚችሉበት አጋጣሚ አላጡም ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ከዓመታት በፊት በገጠሩ ማኅበረሰብ ያዩት የሕክምና ጉድለት አካባቢውን ለቅቀው እንዳይሄዱ አስሮ አስቀርቷቸዋል፡፡ በሚያደርጉት ነገርም ደስተኛ ናቸው፡፡ ከቤተሰባቸው ውስጥ ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ እርሳቸው እንደኾኑ ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን በሚወዱት ሙያ ውስጥ ስለሚኖሩ ደስተኛ ናቸው፡፡ የገጠር ሰዎችን መርዳት ነው ለእኔ ትልቁ ደስታ ይላሉ፡፡
በጤና ባለሙያነት 23 ዓመታትን አገልግለዋል፡፡ በእነዚያ 23 ዓመታት ጉዞ ‹‹አድንኑን ሞትን፣ ተጎዳን ደግፉን›› የሙሉ ድምጾችን ሰምተዋል፣ በቅንነት የሚቻላቸውን አድርገዋል፡፡ ያልቻሉት ደግሞ ከህመሙ ሳያገገም ሲያልፍ ተመልክተዋል፡፡ እንድ ቀን ሲያለቅሱ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲስቁ ነው የኖሩት፡፡ ሕመም የጠናበት ሰው ሲድን ደስ ሲላቸው፣ ሕመም የጠናበት በዚያው ሲያሸለብ ደግሞ ሲከፋቸው ነው የኖሩት፡፡ እንደ እናት ሲያለቅሱ፣ እንደ ሐኪምም ሲያክሙ ነው የኖሩት፡፡
የሐምሌ ሰማይ ጠቋቁሯል፣ ደመናውም ከብዷል፣ የጠቆረው ሰማይ ዝናቡን ያወርዳል፣ ያ ወቅት ለወልድያ መልካም አልነበረም፡፡ ከጠቆረውና ከከበደው የሐምሌ ሰማይ ተጨማሪ ክፉ መንፈስ ከብቧታል፡፡ መነሻውን ከትግራይ ያደረገው ወራሪና አሸባሪ ቡድን ወልድያን ሊይዝ በሕዝብ ማዕበል ይጎርፋል፣ ጀግኖቹ ደግሞ ከተማቸውን ላለማስያዝ ከጠላት ጋር ይተናነቃሉ፣ ትንቅንቁ በቀንና በማታ ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡ ወልድያን ከበው በቆሙት ተራራዎች የማያበራ የጥይት ተኩስ ይሰማል፡፡
ጠላትን እንደ ቅጠል ሲያርግፉ የነበሩት ጀግኖች ጊዜ ያገኙ ዘንድ ቦታ መቀየር ነበረባቸውና ሥፍራ ቀየሩ፡፡ ለወትሮው ሰው የሚበዛበት፣ ጠያቂና ሕሙማን የማይታጣበት፣ ነጫጭ የለበሱ የጤና ባለሙያዎች ለአገልግሎት የሚፋጠኑበት የወልድያ ሆስፒታል ጭር ብሏል፡፡ ሲሰተር አልማዝ በዚያ ሆስፒታል ይሠራሉ፡፡ እኒያ ነርስ በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር ውስጣቸው አዝኗል፡፡ ነገር ግን ወልድያን ለቅቀው መውጣት ፈጽመው አልፈለጉም ነበር፡፡ ‹‹ሙያህን ትርጉም ከሰጠኸው ከባድ ነው፡፡ ለሙያህ በቂ ትርጉም ለመስጠት በቂ ምክንያት ሊኖርህ ይገባል፡፡ ልጄ እንሂድ ስትለኝ አይ አይሆንም አልሄድም፡፡ አንቺ ልጆችን ይዘሽ ሂጂ፡፡ እኔ የጤና ባለሙያ ነኝ ምንም አልኾንም አልኳት፡፡ የጤና ባለሙያ ማለት ሕመምን መጋራት ነው፡፡ በሰላም ቀንማ መንግሥትም ይከፍልሃል፣ ለእንጀራ ብለህ ነው የምትሠራው፣ በክፉ ቀን መገኘት ነው ትልቁ ነገር›› የነርሷ ቃል ነበር፡፡ ሕሙም ጥዬ ሄጄ በኅሊናዬም በታሪክም አልወቀስም ያሉት ነርስ የሚመጣውን ኹሉ ስለ ቃል ኪዳን ይቀበሉ ዘንድ ወደዱ፡፡
አንዲት እናት በወልድያ ሆስፒታል ውስጥ ታመው ነበር፡፡ ያችን እናት ደግሞ ሲስተር አልማዝ ይከታተሏቸው ነበር፡፡ ጠላት ወልድያን ከመያዙ አስቀድሞ በጠዋት የእነዚያ እናት ሕይወት አለፈ፡፡ ሆስፒታሉ ሰው እየራበው ነበር፡፡ የእኒያን እናት አስከሬን የት ያስቀምጡት ግራ ገባቸው፡፡ አማራጭ ሲጠፋ በሆስፒታሉ ውስጥ በተገኘ አንድ ሥፍራ ላይ እኒያን እናት አፈር እንዲቀምሱ አደረጉ፡፡ እኒያን እናት የቀበሯቸው ሰዎች ቁጥራቸው አራት ብቻ ነበር፡፡ ሲስተር አልማዝ በመራር ሐዘን እኒያን እናት ቀብረው ወደቤታቸው አቀኑ፡፡
ጠላት ወልድያን ለመቆጣጠር ትግል ላይ ነው፡፡ ሲስተር አልማዝም ከመኖሪያ ቤታቸው ደርሰዋል፡፡ የሐምሌ ሰማይ የበለጠ ከብዷል፡፡ በሆስፒታል አንድ አስታማሚ ያልነበራቸው አባት ብቻቸውን ተኝተዋል፡፡ ሲስተር አልማዝ በጠዋት መድኃኒት ሰጥተዋቸው ወደቤታቸው አቅንተዋል፡፡ ያ ሰው ተለይቶት የማያውቀው ግቢ ውር የሚልበት ጠፍቷል፡፡ በግቢው ውስጥ ሕመም የበረታባቸው አባት ብቻ ነውና ያሉበት፡፡ ‹‹ፍርሃት አልነበረኝም፡፡ ንዴት ግን ውስጤን እየፈተነው ነው፡፡ ለምን ይህ ኾነ በሚል ተበሳጭቻለሁ፡፡ እኔ እንዲህ እኾናለሁ የሚል ሐሳብ አንድ ቀን አስቤ አላውቅም›› ሲስተር አልማዝ በሆስፒታል ውስጥ ብቻቸውን ያሉት ሰው ጉዳይ አሳስቧቸዋል፡፡ ረፍትም ነስቷቸዋል፡፡ ወልድያስ ለምን እንደዚህ ኾነች የሚለው ሐሳብ አናውዟቸዋል፡፡ በዚያች ከተማ ሐዘን የገባቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡
ክፉ ቀን ተደራረበ፡፡ ሲስተር አልማዝ ወደ ቤታቸው ሲገቡ የልጅ ልጃቸው ታማ እያቃሳተች ያገኟታል፡፡ ደነገጡ፡፡ በጠዋት የእነዚያ እናት ሞት፣ በሆስታል ውስጥ አስታማሚ የሌላቸው አባት፣ ከቤት የልጅ ልጃቸው ሕመም፣ ከዚያ በላይ የሚወዷት ከተማ ወልድያ ሕዝብ ስጋት ረፍት ነሳቸው፡፡ ለልጅ ልጃቸው ሽሮፕ ይገዙ ዘንድ ወደ ፋርማሲ አቀኑ፡፡ አካባቢው በጥይት እየታመሰ ነው፡፡ ያ ለእርሳቸው ከባዱ ጊዜ ነበር፡፡ ጥይቱ ሲበዛ ወደ አንድ ቤት ተጠግተው ቆሙ፡፡ አንድ የሰሙት ድምጽ ልባቸውን አደማው፡፡ ‹‹አንድ ሰው በመገናኛ ሬድዮ ወልድያን ተቆጣጥረናል ሲል ለአለቆቹ አሰማ፡፡ ያን ጊዜ ውስጤ ሲቀዘቅዝ ተሰማኝ፡፡ ተቆጣጥረናል የሚለው ድምጽ ረበሸኝ፡፡ እያለቀስኩ ወደቤቴ ገባሁ›› የቀያቸው በጠላት መደፈር አበሳጫቸው፣ እንባቸውን በጉንጫቸው እያወረዱ የውስጣቸውን ምሬት ያጥቡ ጀመር፡፡ በዚያ ቀን መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ የጥይት በረዶ ከየአቅጣጫው ይወርዳል፡፡
ሲስተር አልማዝ በቤታቸው ኾነው በሆስፒታል ውስጥ ያሉት አባት የሕመም ድምጽ በዕዝነ ልቦናቸው እያቃጫለ አላሳርፍ አላቸው፡፡ ምን ያደርጉ በክንፍ ሄደው አይደርሱላቸው ነገር፡፡ እያሰቧቸው ያለቅሳሉ፡፡ ይገድሏቸዋል የሚል ጭንቀት አናወዛቸው፡፡ እንዳያልፍ የለ ቀኑ መሽቶ ነጋ፡፡ በጠዋት ተነስተው ፈጣሪያቸውን ይማጸኑ ዘንድ ወደ ቤተክርስቲያን አቀኑ፡፡ ፈጣሪያቸው መልካም ነገር ያደርግ ዘንድ ተማጽነው ተመለሱ፡፡ ወደ ሆስፒታልም አቀኑ፡፡ በጠላት ታጣቂዎች አትገቢም ተብለው ተከለከሉ፡፡ ‹‹አንድ ታማሚ ሰው አሉ ከዚህ አልኳቸው፡፡ አይነተናቸዋል አሉኝ፡፡ አላመንኳቸውም ገድለዋቸዋል ብዬ፡፡ ማዬት ብቻ ነበር የፈለኩት ማሳዬት አልፈለጉም፡፡ በማግስቱ ተመለሽ አሉኝ፡፡ ሄድኩኝ፣ በአጃቢ አስገቡኝ፡፡ ከነበሩበት ቦታ ሳጣቸው ደነገጥኩ፡፡ ከእነ አልጋው ገፍተው ወደ አንድ ቦታ አስገብተዋቸው ነበር፡፡ በሕይወት ሳገኛቸው ደስ አለኝ›› ብቻቸውን የሰነበቱት አባት ስቃይ ውስጥ ነበሩ፡፡ ብቻቸውን አገላብጠው ሕክምና ለመስጠት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ግን አልችልም ብለው አልተዋቸውም፡፡ አጥበው፤ መድኃኒት ሰጧቸው፡፡ እኒያ በሆስፒታል ብቻቸውን የነበሩት ሰውም ተስፋ ሰነቁ፡፡ እንደሚመለሱ ነግረዋቸው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
በከተማዋ መልካም ነገር የለም፡፡ የሽብር ቡድኑ አባላት ሕዝብ ያሰቃያሉ፡፡ እንዲያም ኾኖ ሲስተር አልማዝ መልካም ነገር ከማድረግ አልቦዘኑም፡፡ በከተማዋ ያገኟቸውን ወጣቶች አስተባብረው ወደ እነዚያ አባት በድጋሜ ሄዱ፡፡ አጠቧቸው፡፡ ልብሳቸውንም ቀየሩላቸው፡፡
ሲስተር አልማዝ ከችግር ጋር እየተጋፈጡ እንደ ቀደመው ኹሉ በሥራቸው ቀጠሉ፡፡ የሆስፒታሉን መድኃኒቶችና መሳሪያዎች ግን የሽብር ቡድኑ አባላት ያጉዙት ጀምርዋል፡፡ የማይፈልጉትን ደግሞ እዛው እየሰበሩ ይጥሉታል፡፡ ይሄን ሲያዩ ዝም ማለት አልቻሉም፡፡ ለምን ብለው ጠየቁ፡፡ እንዴት የሕዝብ ሀብት ይነካል ብለው በእልህ ጮሁ፡፡ ሰሚ ግን አልነበራቸውም፡፡ ለሃይማኖት አባቶችም ተናገሩ፡፡ ብቻቸውን ምንም ማድረግ ስለማይችሉ የሃይማኖት አባቶች መስማታቸው ግድ ነበር፡፡ የሃይማኖት አባቶችም የተጠየቁትን አደረጉ፡፡
በጠንካራዋ ባለሙያ ምክንያት አባቶች ሰምተው ሆስፒታሉ ባለው እንዲሠራ ተደረገ፡፡ ሳይወጡ የቀሩ ባለሙያዎችም እየተሰባሰቡ መጥተው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡ የመድኃኒት እጦት ግን ከባድ ነበር፡፡ ያም ኾኖ ባለው እየታገሉ ብዙዎችን ከሞት ታደጉ፡፡ በእርሳቸው ጥረት፣ ታማኝነት እና በአባቶች ታላቅ ረዳትነት ብዙዎች ከሞት ተረፉ፡፡
‹‹ወታደር የሚቆስለው፣ የሚሞተው ለማን ብሎ ነው? ለብቻው የተሰጠችው ሀገር የለችውም እኮ፡፡ ኹሉንም የሚያደርገው ለሀገሩ ነው፡፡ እኛም መሥራት አለብን፡፡ እኔም ታካሚዎችን መታደግ ግድ ይለኛል፡፡ እየሠራሁ ብሞት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ኹሉም ሰው መታገል ያለበት በሙያው ነው›› ነው የሚሉት፡፡ ለቃልኪዳናቸው ሲሉ ከሞት ጋር ተናነቁ፣ ሊገድሏቸው ይችላሉ፡፡ እርሳቸው ግን እስትንፋሳቸው እስካለች ድረስ እርዳታቸውን የሚጠይቁ ዜጎችን ለመርዳት ቆረጡ፡፡
ከሃይማኖት አባቶች፣ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በመኾን ለወራት ታገሉ፡፡ የሦስት ወር መድኃኒት ያለው የአንድ ወሩን ቀንሶ ለሌለው እየሰጠ መልካሙን ኹሉ በማድረግ ተባበረ፡፡ ሲስተር አልማዝ መሸነፍ አይወዱም፡፡ በችግር ውስጥ ኾኜ የታመሙ ሰዎችን ሳግዝ ውዬ ቤቴ ስገባ ደስ ይለኛል፡፡ ነብሴ ሐሴትን ታገኛለች፡፡ የገንዘብ ችግር ውስጥም ገብተን ነበር መቋቋም ግን ግድ ይላል፡፡ ‹‹ከሠራሁበት 23 ዓመታት በችግር ጊዜ የሠራኋቸው ወራት ለእኔ ትልቅ ቦታ ነበራቸው፤ የረካሁትም በእነዚያ ወራት ነው›› ብለውኛል፡፡
ወራት ተቆጥረው፣ ሥራቸውም ቀጥሎ፣ እኒያ በሆስፒታል ውስጥ ብቻቸውን የነበሩት አባትም ሕክምና እየተሰጣቸው ቆዩ፡፡ ዳሩ የመጨረሻውን ጊዜ ማዬት አልታደሉም ነበር፡፡ ዳግም ላይመለሱ አሸለቡ፡፡ ‹‹እርሳቸው ሕይወታቸው ሲያልፍ የተሰማኝ ስሜት ከባድ ነበር፡፡ ሕይወታቸው እንደተቀማ ነው የምቆጥረው፣ የተሻለ ሕክምና አግኝተው ቢኾን ይተርፉ ነበር፡፡ ታዲያ በየት ሄደው ያገኛሉ›› እኒያ ከሞት ጋር ተጋፍጠው የረዷቸው አባት ሲሞቱ ሲሰተር አልማዝ ልባቸው ተሰበረ፡፡ አምርረው አለቀሱ፡፡ ምን አለበት መልካሙን ቀን ቢያዩ ሲሉ እንባቸውን አፈሰሱ፡፡ መድኃኒት ከጠላት ፊት እየሰወሩ ያከሟቸው አባት ጥለዋቸው ሲሰናበቱ የእንባ ማዕበል ወሰዳቸው፡፡
በሙያዬ የፈለገው ፈተና ይምጣ፣ ሞትም ቢኾን፣ መሰቃዬትም ቢኾን፣ ግርፋትም ቢኾን፣ እነርሱም የጤና ባለሙያ እንደገደሉ ይወቁት ይላሉ፡፡
‹‹ለሙያ መታመን መታደል ነው፡፡ ኹሉም ለሙያው ታማኝ ቢሆን ሀገራችን እንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ አትገባም ነበር፡፡ ኹሉም ለሙያው ቢታመን ያተርፋል፡፡ ሲደላማ ኹሉም ያግዛል፡፡ ሥነ ምግባሩ “ነርስ እናት ናት ነው” የሚል፣ እናት የፈለገ ጊዜ ቢቸግራት ጦሟን አድራ ነው ልጆቿን የምታበላው፡፡ ታዲያ እናትነቴን መቼ ልግለጸው? ለእኔ ንጉሤ ታሞ የመጣው ሰው ነው፡፡ ያ ታማሚ የሞቀ ቤቱን ጥሎ የመጣው የጤና ባለሙያውን አምኖ ነው፡፡ ታዲያ ያን ሰው እንዴት አድርጌ ጥዬው እሄዳለሁ፡፡ በሙያ መታመን ለአንድ ሀገር እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በሙያህ ካልታመንክ ሌባ ነህ፡፡ ተበድረሽ አምጭ የሚለኝ የለም፡፡ ባለኝ ዕውቀት ግን የምችለውን ማድረግ አለብኝ፡፡ በዘመኔ እንደዚያ ጊዜ ረክቼ አላውቅም›› ነው ያሉኝ፡፡
ወዳጅ ዘመዶቻቸው ከተማውን ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቀው ነበር፡፡ ልጃቸው በአንድ ወቅት ካልወጣን ስትል አስቸገረቻቸው፡፡ አይኾንም አሉ ሲስተር አልማዝ፡፡ ልጃቸው ግን አይኾንም አለች፡፡ ወደ ሆስፒታል ወስደው የታመሙ ሰዎችን እንድታይ አደረጓት፡፡ እነዚህን ሰዎች ጥዬ ልሂድ ወይ አሏት፡፡ ልጃቸውም ይቅርታ ጠይቃ በእናቷ ሥራ ተደነቀች፡፡ እኒህ ሰው በጠፋበት ጊዜ ሰው የኾኑት ታማኝ ባለሙያ በመካከለኛው ምሥራቅ በዱባይ በሚካሄደው የምርጥ ነርሶች አዋርድ (ሽልማት) ላይ በእጩነት ቀርበዋል፡፡ በዚያ ጊዜ ያላደረጉት ነገር የለም፡፡ ብዙ የተቸገሩ ሕሙማን አግዘዋል፡፡ ከፈጣሪ በታች ኾነው ብዙዎች ተጨማሪ ዘመን እንዲኖሩ አድርገዋል፡፡ እስትንፋሳቸውን አስቀጥለዋል፡፡ መልካሟ እናት፡፡
የሀገር ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚሰጥ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወታደር ኾነህ ጥይት ፈርተህ አትቀርም፣ የኤሌክትሪክ ባለሙያም ኾነህ ይይዘኛል ብለህ አትቀርም፣ እንዳይዝህ መጠንቀቅ ነው እንጂ፡፡ የሙያህን መወጣት ግድ ነው፣ እያንዳንዱ ባለሙያ በሙያ ሥነምግባር ታንጾ ግዴታውን ካልተወጣ ሀገር እንደ ሀገር አትቀጥልም›› የሲስተር አልማዝ የመጨረሻ መልእክት ነበር፡፡
ዛሬ ላይ በወልድያ ሰላም ወርዶ ጠላትም ተመትቶ ሲስተር አልማዝ በሰላም እየሠሩ ነው፡፡ ወዳጄ ለቃልህ እስከ መጨረሻው ታመን፡፡ ያን ጊዜ ትረካለህ፡፡ ሰላምም ታገኛለህ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/