ኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ሚኒስቴሩ ገለጸ፡፡

154

ባሕር ዳር: የካቲት 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በ2025 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፉ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ስልት መንደፉን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ሕዝብ በኢኮኖሚው ቀጥተኛ ተሳታፊ ሲሆን ትልቅ ዕሴት ይኖረዋል፡፡ ሕዝብን በኢኮኖሚ ውስጥ የነቃ ተሳታፊ ለማድረግ ደግሞ ዲጂታል የኢኮኖሚ ሥርዓት የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የገበያ ደላሎችን በማስወገድ፣ አቅርቦት እና ፍላጎት እንዲጣጣም በማድረግ ጤነኛ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ ነው።
ዲጂታል ኢኮኖሚ ትላልቅ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አውታሮችን፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችሉ መተግበሪዎችን (አፕሊኬሽን) እና በመተግበሪያዎቹ የሚፈጠሩ ዳታዎችን መሠረት አድርጎ የሚተገበር ዘመናዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ነው። ይህ ዲጂታል ቴክኖሎጂ በአካል የሚከወን ልማዳዊ የንግድ ልውውጥን በማስቀረት ጊዜና ቦታ ሳይወስን ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መከወን የሚያስችል ነው። በዚህ ጊዜም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተላለፈ ነው የሚገኘው።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ ውሏል። በአማካይ 62 ነጥብ 5 በመቶ የሚገመት የዓለም ሕዝብ የኦንላይን ግብይት ተጠቃሚ ነው፡፡ የአፍሪካ አማካይ ግምታዊ የኢንተርኔት ተጠቃሚ 29 በመቶ ሲሆን ኢትዮጵያ ካላት ሕዝብ መካከል 22 በመቶ የሚሆነው የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንደኾነ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንፎርሜሽን ፕሮግራም ኃላፊ አብዮት ባዩ ገልጸዋል።
ይህ አሐዛዊ መረጃ 78 በመቶ ገደማ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደራሽ አለመሆኑን ያመላክታል፡፡ ነገር ግን ባለው ተጠቃሚ ብዙ መሥራት የሚቻልበት እድል መኖሩን አቶ አብዮት አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገር በተለይ በዲጂታል ክፍያ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ተደርጓል። የኢትዮጵያ የኢ-ትራንዛክሽን ሕግ ጸድቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በብሔራዊ ባንክ አማካኝነትም የዲጂታል ክፍያ መመሪያዎች እየወጡ ድርጅቶችና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉበት እየተደረገ ነው፡፡ ይህም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ለመኾኑ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ተብሏል።
ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማስፋፋት ከሚተገበሩት መካከል ቴሌ-ብር ወደ ሥራ መግባቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ 54 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ የቴሌኮም ተጠቃሚ እንደኾነ ይነገራል፡፡ ቴሌ ብር በቀላሉ በተንቀሳቃሽ ስልክ ክፍያ መፈጸም የሚያስችል ሲሆን ሕዝቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው፡፡
ኢትዮጵያ በ2025 ዓ.ም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፉ እድገት ለማስመዝገብ ስትራቴጂያዊ ስልት ነድፋለች፡፡ ይህን ለማሳካት መንግሥት የሚከናውናቸው ተግባራት ቢኖሩም መሠረቱን ያደረገው የግል ሴክተሩን እንደኾነ አቶ አብዮት አብራርተዋል። እንደ አቶ አብዮት ማብራሪያ ዲጂታል ኢኮኖሚው የጎላ ፋይዳ የሚኖረው የገጠሩ ማኅበረሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሲሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የግል ሴክተሩ በመሪነት መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ የግል ሴክተሩን ተሳትፎ ለማሳደግም በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ግል እንዲዛወር የማድረግ ሂደቱ አዳዲስ አሠራር፣ ተጨማሪ መሠረተ ልማት እና የግንኙነት አዎታሮችን በማስፋፋት ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎም ተስፋ ተጥሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article❝የዕለት እንጀራን እስከ መስጠት የዘለቀው ፍቅር❞
Next article“ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ ከ3 ሺህ 400 በላይ የሳይበር ጥቃቶችን መመከት ተችሏል” የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ