❝የዕለት እንጀራን እስከ መስጠት የዘለቀው ፍቅር❞

232

የካቲት 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ትክክለኛ ሰጪ ካለው ላይ ከፍሎ ይሰጣል፡፡ ከሌለው ደግሞ ባለው መልካም ልብ መልካም ይኾን ዘንድ መልካሙን ይመኛል፡፡ ካለህ ላይ ስጥ እንጂ ከሌላህ ላይ ስጥ ያለ የለም፡፡ መስጠት ትርጉም የሚኖረው ካለ ላይ ሲሰጡ እንጂ ከተረፈ ላይ ሲኾን አይደለም፡፡ ማነው ከዕለት ጉርሱ ላይ ቀንሶ ለተራበ ያበላ? ማነው ከዓመት ልብሱ ላይ ከፍሎ ለታረዘ ያለበሰ? ማነው በጽዋ ለክቶ ቀዝቃዛ ውኃ ለተጠማ ያጠጣ? ደግ ልቦች ደግነትን ብቻ ያደርጋሉ፣ የደግነትን መንገድ ብቻም ይፈልጋሉ፡፡ ካላቸው ላይ ሰጥተው ፈጣያቸውን አመስግነው በሰላም ይተኛሉ፡፡ ረፍት የሚሰጥ እንቅልፍም ይወስዳቸዋል፡፡ መኝታቸው ላይመች ይችላል ህሊናቸው ግን ምቹ ነውና ደስ ብሏቸው ይተኛሉ፣ ሰናይ ሌሊትም ያሳልፋሉ፡፡ ማዕልቱን በመልካም ነገር የሚያሳልፍ ሌሊቱንም በሰላም ያሳልፋል፡፡ ሕይወት የተግባራችን ውጤት ናትና፡፡

ʺበሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ኾኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ኹሉና ዕውቀትን ኹሉ ባውቅ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ኹሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ኹሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፤ የራሱንም አይፈልግም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ኹሉን ይታገሣል፤ ኹሉን ያምናል፤ ኹሉን ተስፋ ያደርጋል፤ በኹሉ ይጸናል።

ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። እንዲህም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” እንዳለ መጽሐፍ ከሁሉም የበለጠ ፍቅር ከሁሉም ትበልጣላችና ስለ ፍቅር መልካሙን ነገር አድርጓል፡፡

በተመቻቸ ሕይወት ውስጥ አይኖርም፣ ደልቶት አያደርም፣ አማርጦ አይመገብም፣ አማርጦም አይጠጣም፤ አንደኛውን ሲሰፉት በሌላኛው እየተቀደደ የሚያስቸግረው ሕይወት እርሱንም ፈትኖታል፡፡ ዳሩ በሕይዎት ቀዳዳ መብዛት ተሰላችቶ፣ ተስፋ ቆርጦ አልተወውም፡፡ በተቀደደው ኹሉ እንደ አቅሙ እየሰፋ መኖርን መርጧል እንጂ፡፡ አድካሚው የሕይዎት ጉዞ ዝቅ እንዲል ቢያደርገውም፣ ከፍ እንደሚል ያምናልና አልተበሳጨበትም፡፡ ኹሉንም በትግዕስትና በትግል ማለፍ እንደሚገባው በለጋ ዕድሜው ተምሯል፡፡

ለደንበኞቹ ጫማ ውበት እየሰጠ፣ ደንበኞቹ በሚሰጡት ትንሽ ፍራንክ ነው ሕይወቱን የሚመራት፣ ምን ይሄ ብቻ እርሱ መንገድ ላይ ተቀምጦ ጫማ እያስዋበ በሚያገኛት ገንዘብ የቤተሰቦቹን ኑሮም ይደጉማል። መተዳደሪያቸውም ያችው ናት፡፡ በዚህ ብቻ አያርፍም እርሱ ከሥራው ጎን ለጎንም ይማራል፡፡ የ11ኛ ክፍል ተማሪም ነው፡፡ ሕይዎት እረፍት አትሰጠውም፤ ጥንካሬን እና መልካምነት ግን ተምሮባታል የ17 ዓመቱ ታምራት ቀጸላ፡፡ ታምራት ከሊማሊሞ ራስጌ፣ ከራስ ደጀን ግርጌ ከተቆረቆረችው ከተማ ደባርቅ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡

ከመልካም ሕዝብ መልካምነትን፣ ከደግ ሕዝብ ደግነትን፣ ከአርቆ አሳቢ ሕዝብ አርቆ አሳቢነትን፣ ከጀግና ሕዝብ ጀግንነትን፣ ከጽኑ ሕዝብ ጽናትን ሲማር ነው ያደገው፡፡

“ሀገራችን ጎንደር ስሜን አባራስ
ዋልያ የሚያሳድግ እያበላ ገብስ” እንደተባለ እንኳን የሰው ልጅ ዋልያ እንኳን ገብስ እየበላ የሚያድግበት፣ ደግነትና መልካምነት የበዛበት አካባቢ ታምራትም ተቀድቷልና ደግነትን ለብሶት አድጓል፣ ፍቅርን ተምሯል፣ በፍቅርም ኖሯል፡፡ ታምራት ነገ ቀና ብሎ እንደሚሄድ ልቡ እየነገረው፣ ተስፋም ሰንቆ ዛሬ ላይ ዝቅ ብሎ ጫማ ሲያስውብ ይውላል፡፡

ʺአንገቴን ለሥራ ጎንበስ እንዳረኩት
ችግሬን በብሩሽ ሲጠረግ አየሁት” እንዳለ ገጣሚው በብሩሹ የደንበኞቹን ጫማ ሲያጸዳ፣ ነገ የእርሱ ችግርም በብሩሽ ሲጸዳ ይታየዋል፡፡ መልካም ሕይወት እንደሚገጥመው ልቡ ተስፋ ታደርጋለች፡፡

አካባቢው በጉም ተሸፍኗል፣ ሰማዩ የተበሳ ይመስል፣ ያለ ማቋረጥ ዝናብ ያወርዳል፣ የክረመቱ ቆፈን እጅና እግርን አሳስሮ ይጥላል፡፡ የሚጎተተው ጉም በአሻገር ያለውን ጋራና ተረራ አያሳይም፡፡ በዚያ ጉምና ዝናብ በበዛበት ጨለማ መሳይ ቀን ውስጥ ኾነው ሲያዩ ሰማይና ምድር የተገናኙ ይመስላል፡፡ ጉሙ ከምድር ላይ ተነስቶ፣ ሰማዩም ጠርቶ ያቺ ተናፋቂዋ ጀንበር የምትመለስ አትመስልም ነበር፡፡ በዚህ ሥፍራ ታዲያ ሕዝብና ሀገርን ሊያዋርድ የመጣ ጠላትን ለመደምሰስ ቆፈኑ ሳይበግራቸው፣ ጉሙ ሳያሰለቻቸው፣ ብርዱ ተስፋ ሳያስቆርጣቸው፣ ጭቃ በበዛበት ምሽግ የሚኖሩ ነበሩ፡፡

መነሻውን ከትግራይ ያደረገው የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ቡድን በሕዝብ ማዕበል እየተመመ ደባርቅና ደባትን ለመያዝ ይፍጨረጨር ነበር፡፡ ደባርቅና ዳባትን ይዞ ወደ ጎንደር ለመገስገስ ነበር ሕልሙ፡፡ ቅዠት ኾነበት እንጂ፡፡ እኒያ በምሽግ ውስጥ የነበሩ ጀግኖችም ከጠላት ጋር ተናነቁ፣ በፍጹም አይደረግም አሉ፡፡ በጭና ቆርጦ በወቅን ተራራዎች ለመምጣት ነበር የጠላት ግብግቡ፡፡ የጀግኖች ክንድ እሳት ኾኖ በክረምት በላው እንጂ፡፡

የአካባቢው ሰውም ክብር ሊያረክስ የመጣውን ጠላት እየተናነቀው ነው፡፡ የጀግኖችን ሀገር ደፍሮ ማለፍ በፍጹም አይቻልም ብሏል፡፡ ያን ጊዜ ወጣቶች በመዋጋት፣ ስንቅ በማቀበል፣ ትጥቅ በማቅረብና ቦታ በመጠቆም ትግሉን ተቀላቅለዋል፡፡ ታምራትም ከአብሮ አደጎቹ ጋር ኾኖ አስቸጋሪ ወደ ኾኑ ተራራዎች እየወጣ፣ ስንቅ ያቀብላል፡፡ ታምራት ለወላጆቹ አንድያ ልጅ ነው፡፡

በወቅን ተራራዎችና በጭና ለሠራዊቱ ስንቅና ትጥቅ በሚያቀብልበት ጊዜ የሠራዊቱን ለሀገር መሰጠት፣ ጀግንት፣ አንድነትና ጽናት ተመለከተ፡፡ ልቡ አብዝታ ተገረመች፡፡ እነርሱ ለሀገራቸው ሲሉ ሞትን ሳይፈሩ ሲዋደቁ አይቷልና፡፡ ልቡ በሠራዊቱ ፍቅር ተነደፈች፡፡ ጀግኖቹ ጠላትን እንደ ቅጠል አርግፈው ሲጥሉት ተመለከተ፡፡ ፍቅሩ የበለጠ ጨመረበት፡፡ ዳባትና ደባርቅን ሊቆጣጠር አስቦ የነበረው ጠላት በየጥሻው ጭዳ ኾኖ ቀረ፡፡ ጀግኖቹ ደግሞ በድል አድራጊነት ተንጎማለሉ፡፡

ይህን ያዬው ታምራት ምን ላድርግላቸው? ሲል አሰበ፡፡ ሀብት የለው አይሰጣቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው ኑሮው፣ አይሸልማቸው ኪሱ ባዶ ነው፡፡ ምን ያደርግ ዘንድ አብዝቶ አሰበ፡፡ አንድ ሐሳብ መጣለት፡፡ “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለእኔ ሲል በምንም በማንም የማይተካውን ህይወቱን ለሚከፍልልኝ ጀግናው ሠራዊታችን ባለኝ ነገር ለመደገፍ ወሰንኩ” ይላል ታምራት። በሙያው ያገለግላቸው ዘንድ ከራሱ ጋር ቃል ገባ፡፡ እንደሚያደርገውም አመነ፡፡

“እኔን እና ቤተሰቦቼን የማስተዳድረው በሊስትሮ ሥራ ነው። አቅሜ የሚፈቅደው ደግሞ ለጀግናው ሠራዊታችን ጫማቸውን በነፃ መቀባት ነው። በዚህም በምሠራበት አካባቢ ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችን በነፃ ጫማ እንቀባለን ብዬ ፅፌ ለሠራዊቱ በነፃ ጫማ እቀባለሁ”ታምራት እንዳለው አደረገው፡፡ እኒያ ሲዋደቁ ያያቸውን ጀግኖች ጊዜ ኖሯቸው ከምሽግ ወጥተው፣ በከተማ ሲያልፉ ጫማቸውን ማስዋብ ካስፈለጉ በነጻ ያስውባላቸዋል፡፡ ለእኔ ስትሉ ሞታችኋልና ክብር ለእናንተ ሲል ይሸኛቸዋል፡፡

ታምራት በዚህ አላበቃም፡፡ ጫማቸውን ማስዋቡ ብቻ አላረካውም፡፡ ካለችው ላይ አካፍሎ መስጠት ወደደ፡፡ አደረገውም፡፡ “በየዕለቱ ከማገኘው ገቢ 15 ከመቶውን በመቀነስ በየወሩ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እደግፋለሁ። አሁንም ይህን ተግባር አጠናክሬ እቀጥላለሁ” ነው ያለው።

የደባርቅ ከተማ ነዋሪው አቶ ጌታቸው አሰፋ ታምራት ለሠራዊቱ ጫማቸውን በነፃ በመቀባቱ የአካባቢው ነዋሪ የእሱን ሰናይ ተግባር ተመልክተው በቻሉት መንገድ ኹሉ ጀግናውን ሠራዊት እንዲደግፉ ከፍተኛ የሆኾ መነቃቃትን የፈጠረ ጀግና ወጣት ነው ሲሉ ያሞካሽትል።

የሠራዊቱ ፍቅር የዕለት እንጀራን ከፍሎ እስከ መስጠት አደረሰው፡፡ መስጠት ማለት ይህ ነው ካለው ላይ ቀንሶ ማበርከት፡፡ እንካችሁ ማለት፡፡ ደግ ሕዝብ ውለታን አይረሳም፡፡ ጀግናን ያከብራል፣ አክብሮ ይከበራል፣ ጀግና ሕዝብ ጀግና ይፈጥራል፣ አጀግኖ ያኖራል፡፡ እየኾነ ያለውም ይሄው ነው፡፡ ወዳጄ የሚሞትልህን ውደደው፣ የሚሞትልህን አክብረው፡፡ ያን ጊዜ አንተም ሀገርህም ትከበራለች፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article5ሺህ ሰዎች የተገኙበት የፍቅር ምሳ ግብዣ በደሴ ከተማ አይጠየፍ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
Next articleኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ሚኒስቴሩ ገለጸ፡፡