የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት እንደሚሠራ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

130

አዲስ አበባ: የካቲት 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት “የፌዴራል ዳኝነት አሁናዊ ሁኔታ እና የወደፊት ዕይታ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የ2013 በጀት ዓመት እና 2014 ዓ.ም ግማሽ በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ እያካሄደ ነው። በግምገማ መድረኩ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በ2013 በጀት ዓመት እና በ2014 ግማሽ ዓመት የተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበዋል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኝነትን አስመልክቶ ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችና አዋጆች፣ የዳኞች የሥነምግባር ደንብ፣ የዳኞች ጥቅማጥቅም መምሪያ እና መሰል ማሻሻያዎች ፀድቀው ወደ ትግበራ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡ የማሻሻያ አዋጆችን መፅደቅ ተከትሎ የዳኝነት ዘርፉ ተቋማዊ ነፃነቱን የሚያረጋግጥባቸውን ደንቦች እና መመሪያዎች በማውጣት ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ወይዘሮ መዓዛ የፍርድ ቤቱን ፍላጎት በአጥጋቢ ሁኔታ ያሟላ ነው ባይባልም ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት የተሻለ የበጀት አቀራረብና አመዳደብ ሥርዓት መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል። ግልፅነት እና ተጠያቂነትን የሚያጠናክሩ 14 መመሪያዎች እና የአሠራር መግለጫዎች ተዘጋጅተዋልም ብለዋል።
በሦስቱም ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከተገልጋይ ለተቋሙ አመራሮች፣ ለሬጅስትራር ጽሕፈት ቤት እና ለኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ከቀረቡ 1 ሺህ 721 ቅሬታዎች መካከል 1 ሺህ 533 በተለያዩ ደረጃዎች ምላሽ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል።
የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍናን በተመለከተም ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት በሦስቱም ፍርድ ቤቶች፣
• በ2013 በጀት ዓመት 171 ሺህ 276
• በ2014 መንፈቀ ዓመት ደግሞ 79 ሺህ 679 መዛግብት
• በአጠቃላይ 250 ሺህ 955 መዛግብት ዕልባት አግኝተዋል።
በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በሚታዩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መሥጠት አለመቻሉ፤ የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዛትና ውሳኔዎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በወቅቱ ያለመፈፀም ያጋጠሙ ችግሮች ተብለዋው ተነስተዋል፡፡
በኀላፊነት ስሜት የሚሠሩ ዳኞች የመኖራቸውን ያህል ኀላፊነት የጎደላቸው ዳኞች በሚፈፅሟቸው ተግባራት ሕዝቡ ለእንግልት እየተዳረገ መሆኑን እና ቅሬታዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውም ተነስቷል። ችግሩን ለመቅረፍ ኅብረተሰቡ አጋርነቱን እንዲያሳይም ተጠይቋል።
በመድረኩ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረግ ስትራቴጂክ እቅድ ቀርቧል። የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኝነትን ማረጋገጥ፤ ግልፅ አሠራር እና የሥነምግባር መርሆዎችን መሠረት ያደረገ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት እና የዳኝነት ቅልጥፍናን ማሳደግ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ተብለው ተለይተዋል።
ዘጋቢ፡-በለጠ ታረቀኝ- ከአዲስ አበባ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ተናገሩ፡፡
Next articleበሀገር መከላከያ ሠራዊት ደቡብ ዕዝ የሠራዊት አባላት የማዕረግ ማልበስ መርሃ- ግብር እየተካሄደ ነው።