❝ያለፉ ችግሮችን በማንሳት ከመወቃቀስ በመፍትሔ አጀንዳዎች ዙሪያ አተኩሮ መሥራት ይገባል❞ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም

335

ባሕር ዳር: የካቲት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአሁኑ ትውልድ ያለፉ ችግሮችን በማንሳት ከመወቃቀስ ወጥቶ ለቀጣይ መፍትሔ ማስቀመጥ በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ አተኩሮ መሥራት እንዳለበት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ።

”አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ ሚኒስቴሩ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ተጀምሯል።

የምክክር መድረኩ ሲጀመር የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት የመጠላለፍና የመነቃቀፍ ፖለቲካ ሲካሄድ ቆይቷል።

በዚህም የዜጎች የሰላም እጦት፣ ተረጋግቶ ያለመኖር እና ለበርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህንኑ የመነቃቀፍና የመጠላለፍ ፖለቲካ ለማስወገድ የአኹኑ ትውልድ ያለፉ መጥፎ ታሪኮችን በማስታወስ መቆዘም ሳይኾን ለቀጣይ ትውልድ መፍትሔ ሊኾን በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት መንግሥታት ዴሞክራሲን ለይስሙላ ሲጠቀሙ በመቆየታቸው በሀገሪቱ የዳበረ ዴሞክራሲ መገንባት አለመቻሉን አውስተዋል።

አሁን ላይ ሕዝቡን በጋራ ሊያግባባ የሚችል ብሔራዊ አካታች ምክክር በማስፈለጉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ነው ያሉት።

ብሔራዊ ምክክሩ ቢቻል ኹሉንም ሊያግባባ በሚችል አግባብ እንደሚከናወን ገልጸው፤ ለቀጣዩ መልካም የሥርዓት አቅጣጫ ቀይሶ ማለፍ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ለዚህም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብ በማፍለቅና አቅጣጫዎችን በማሳየት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ብናልፍ አመልክተዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የውጭ ጠላት ወረራን በድል ልታደርግ የቻለችው ከብሔርና ከዘር የፀዳ ፅኑ ብሔራዊ አንድነት በመኖሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ጠላት የቱንም ያህል ቢጥር የውስጥ አንድነት ጠንካራ እስከኾነ ድረስ ተፅዕኖ ሊፈጥር አይችልም ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በምክክር መድረኩ የሰላም ሚኒስቴርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ምሁራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በምሁራን እየቀረቡ ባሉ ጥናታዊ ጽሑፎች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየአውራምባ ማኅበረሰብ 50ኛ ዓመት በዓል እየተከበረ ነው።
Next articleየኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማኅበራዊና ልማት ኮሚሽን እና ኮርድ ኤድ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረጉ።