❝ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መደገፍ አለባቸው❞ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

205

የካቲት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በፍጥነት እንድታጠናቅቅ ግብፅ ማበረታታት አለባት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከአል-አረቢያ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የግድቡ መገንባት ግብፅን በድርቅ ወቅት እንኳ የውኃ ቋት ኾኖ የሚያገለግል ፕሮጀክት በመኾኑ ፕሮጀክቱን ልትደግፈው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሱዳን በአነስተኛ ግድቦቿ ላይ ይደርስብኛል ብላ የምታነሳውን የደኅንነት ስጋት በሚመለከት መደበኛ የኾነ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደኾነች አቋሟን አስረድታለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሀገሪቱ ግን አኹን ላይ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የሦስተኛ ወገን ጉዳይ አስፈፃሚ እየኾነች መምጣቷን ገልጸዋል።

❝ኢትዮጵያ አንድ ወገን ብቻ ከዓባይ ሀብት ተጠቃሚ ሲኾን ዘላለም ዓለሟን መጠበቅ አትችልም❞ ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ሱዳን እና ግብፅ አኹን ከያዙት ግትር አቋም መላቀቅ አለባቸው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ተቀመጫነቱን ዱባይ ካደረገው የአል-አረቢያ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በሚመለከት ብዙ አዎንታዊ የኾኑ እድሎችን አቅርባ እንደነበር ገልጸው ግብፅና ሱዳን ባለመቀበላቸው ምክንያት ሳይሳኩ እንደቀሩ ጠቁመዋል።

የህዳሴ ግድብ ከጭቅጭቅ ይልቅ የቀጣናዊ ሕብረትና አንድነት ማሳያ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት የጎላ ጉዳት ሳታደረስ የራሷን ሀብት መጠቀም ትችላለች ነው ያሉት።

የሱዳንን አኹናዊ የፖለቲካ ሁኔታ በሚመለከት ኹሉም ወገኖች ከምንም በላይ ሀገራቸውን ማስቀደምና የሱዳናዊያንን ጥቅም ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። ኹሉም ፓርቲዎች የሀገሪቱን ዜጎች ጥቅም ከኹሉ ነገር በላይ በማስቀደም ነገሮችን በእርጋታና ምክንያታዊነት የሚያስኬዱ ከኾነ ልዩነቶቻቸውን ማስታረቅ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል የታየ ተነሳሽነት ካለ በሚል ከጋዜጠኛዋ ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ሬድዋን የሱዳን ሕዝብ ችግሮቹን ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የመፍታት ጥበብ እንዳለው አስረድተዋል።

ለኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን ለመቋጨት ወታደራዊ ኃይል በምንም መልኩ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም ያሉት አምባሳደሩ አስፈላጊው ነገር ኢትዮጵያ እንዳደረገችው የተሻለ የመፍትሔ ሐሳብ ወደ ጠረጴዛ ይዞ መቅረብ ነው ብለዋል።

ወደ ትግራይ ክልል የሚቀርብ የእርዳታ ድጋፍን በሚመለከትም ምንም እንኳን ታጣቂ ቡድኑ የሰብዓዊ ድጋፍ በተገቢ መልኩ እንዳይቀርብ እንቅፋት ቢኾንም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያልተገደበ ድጋፍ በክልሉ እንዲደረግ የሚችለውን ኹሉ እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሚመለከትም በርካቶች ኢትዮጵያን የማዳከም ፍላጎት እንዳላቸው መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል። አብዛኞቹ ጣልቃ ገብነቶችም መንግሥት ያከናወናቸውን መልካም ሥራዎች ላለማበረታታትና ዝቅ ለማድረግ መኾኑን አምባሳደር ሬድዋን ከአል- አራቢያ ጣቢያ የአረቢኛ ክፍል ባልደረባ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከደቡብ ሱዳን አጎራባች አካባቢ ሰርገው የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አምስት ህጻናትን አግተው መውሰዳቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
Next article❝የተፈናቀሉ ወገኖችን ጊዜያዊ ችግር ለማቃለል በክልሉና በአጋር አካላት ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው❞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም