ጣይቱ ብጡል (ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ)

757

የካቲት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሴት ባለመላ፣ የዓድዋ ጦርነት ድል ቀንዲል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቆርቋሪ እና መሥራች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ሊቅ እና ጥንቁቅ፣ የአጤ ምኒልክ አማካሪ እና የትዳር አጋር፡፡ ኢትዮጵያውያን “ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ” ሲሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ከዓድዋ ድል ምስጢራት አንዷ እቴጌይቱ ተጠቃሽ ናቸው የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡
እንደ ሴት ብልህ፣ እንደ እናት ሩህሩህ፣ እንደ ሚስት መካሪ እንደ ተዋጊ አባራሪ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፤ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፡፡ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ነሐሴ 12/1832 ዓ.ም በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር ከተማ እንደተወለዱ ይነገራል። በልጅነት ዘመናቸው ዳዊት ደግመዋል፤ በታላላቅ የሃይማኖት ተቋማት የተለያዩ ሃማኖታዊ ትምሕርቶችን እንደተከታተሉም ይነገርላቸዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ሚያዝያ 25/1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ከአጤ ምኒልክ ጋር ጋብቻ ፈጸሙ። አፈወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ «ዳግማዊ አጤ ምኒልክ» በሚለው መጽሐፋቸው «አጤ ምኒልክ ከልጅነት ጀምረው ሲመኟት እና ሲያልሟት ትኖር የነበረችው ጣይቱ ብጡል በ1875 ዓ.ም ደብረ ብርሃን ገባች። ንግሥተ ሸዋ ኾነች፤ ወዲያው የፋሲካ ዕለት አንኮበር መድኃኔዓለም ቆርበው ተጋቡ። … ፀሐይቱ ለማለት ጣይቱ ተባለች ነገር ግን ከጣይቱ እጣይቱ ለመባል ይገባታል» ይላሉ። ከውጫሌ ውል ውዝግብ ጋር በተያያዘ እቴጌ ጣይቱ «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ነገር ግን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» በሚለው በሳል እና የጀግና ንግግራቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም ያውቃቸዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የቻሉትን ሁሉ አበርክተዋል፡፡ ከሀገር ግንባታ እስከ አዲስ አበባ ከተማ ምስረታ እቴጌዋ ሳይታክቱ ሠርተዋል፤ ባለቤታቸውንም አግዘዋል፡፡ ከባለቤታቸው እረፍት በኋላ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፊቱን ያዞረባቸው እቴጌይቱ ለዘመናት ከመከሩበት፣ ከዘከሩበት እና ከኖሩበት ቤተ መንግሥት ወጥተው በእንጦጦ ቀሪ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉም ተገድደው ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ታዲያ፡- «ተወዶ ከመኖር ተጠልቶ መውለድ ማን ያይብኝ ነበር ይህንን ሁሉ ጉድ» ሲሉ አንጎራጎሩ የሚባልላቸው፡፡ ከላይም ከታችም የሕይዎትን ጥግ ያዩት፣ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ የተሰኙት፣ በዓድዋ ተራሮች ድል ምን እንደሚመስል ያጣጣሙት እና ሀገራቸውን በቅንነት ያገለገሉት እቴጌዋ የዚህ ዓለም ድካም እረፍታቸው የካቲት 4/1910 ዓ.ም እንደነበር ታሪክ ይዘክረዋል፡፡ መልካም እረፍት!
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“በባሕር ዳር ከተማ የትራንስፖርት ፍሰቱ የተሳለጠ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ እንዲሆን እየተሠራ ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት
Next article“አማራ የሚገጥመውን የኅልውና ስጋት ለመሻገር አንድ ሆኖ መደራጀት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው” ዓለምአቀፍ የሕግ ምሁሩ ዶክተር ዘላለም ሞገስ