“በባሕር ዳር ከተማ የትራንስፖርት ፍሰቱ የተሳለጠ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ እንዲሆን እየተሠራ ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት

188

ባሕር ዳር: የካቲት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከጥር 25/2014 ዓ.ም ጀምሮ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ የትራንስፖርት ፍሰቱ ጽዱና የተስተካከለ እንዲሆን የሕግ ማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል። በባሕር ዳር ከተማ የትራንስፖርት ፍሰቱ የተስተካከለ ለማድረግ እየተሠራ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር አደጋን ከመቀነስ አንጻር፣ እንዲሁም ከከተማዋ ውበትና ደረጃ አንጻር የሚበረታታና የሚደገፍ መሆኑን አሚኮ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዓለማየሁ መንግሥቴ የትራንስፖርት ፍሰቱ የተስተካከለ እንዲሆን ዘላቂ የሆነ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡ በተለይ ታክሲዎች ትርፍ አለመጫናቸው በታክሲ ውስጥ ሊመጣ የሚችለዉን ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ ጅምሩ ጥሩና ለከተማዋ ውበት ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው ያነሱት አቶ ዓለማየሁ ኅብረተሰቡ እንዳይጉላላ ከተማ አሥተዳደሩ በቂ ተሽከርካሪዎችን መመደብ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስንታየሁ ዘለቀ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ የተስተካከለና የተሳለጠ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከንቲባ ግብረ ኀይል ውሳኔ መሰረት ባጃጆች፣ የጋሪ ፈረሶችን ጨምሮ ማንኛውም ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ከዋናው የአስፋልት መስመር ውጭ እንዲሠሩ መደረጉን ጠቁመዋል። ባጃጆች ከጠዋቱ 12:00 እስከ ምሽቱ 1:30 ከዋናው የአስፋልት መስመር ውጭ እንዲሠሩ አሠራር መቀመጡን ነው ኀላፊው የተናገሩት።

አቶ ስንታየሁ የአሠራሩን ተፈጻሚነት የሚከታተልና የሚቆጣጠር የቴክኒክ ቡድን ተመድቧል ብለዋል፡፡ ከሕግ ማስከበር ጋር ተያይዞ በተለይ ጠዋትና ማታ የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት በመኖሩ ኅብረተሰቡ እየተጉላላ መሆኑን የተናገሩት አቶ ስንታየሁ ችግሩን ለመቅረፍ የከተማ አሥተዳደሩ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ተቀብሎ ለማስተናገድ ከተማ አሥተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ “በከተማዋ የሚገኙ ታክሲዎች ከኮንትራ ሥራ ወጥተው ሙሉ በሙሉ በኀላፊነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉም እየሠራን ነው፤ በቅርቡም ማሻሻዎች ይደረጋሉ፤ የፍላጎትና አቅርቦት ጥያቄ እስኪስተካል ድረስ ከተማ አሥተዳሩ የመናኽሪያ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ሕጋዊ መብት አለው” ብለዋል፡፡

ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ በባሕር ዳር ከተማ በዋና አስፋልት ግራና ቀኝ የሚቆሙ ተሸከርካሪዎች ተጨማሪ ችግር መሆናቸውን አቶ ስንታየሁ አንስተዋል፡፡ የሕግ ማስከበር ሂደቱ ይህንንም ችግር እየቀረፈ መሆኑን የጠቆሙት ኀላፊው ኅብረተሰቡ ለሕጉ ተፈጻሚነት ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ ታክሲዎች ትርፍ እንዳይጭኑ፣ አሽከርካሪዎች የደኅንነት ቀበቶ እንዲጠቀሙ፣ ባለ ሞተር ሳይክሎች ሄልሜት እንዲለብሱ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ስንታየሁ አሠራሩ ተለምዶ ወደ ቋሚና ተቋማዊ አሠራር ሙሉ በሙሉ እስኪሆን ድረስ የሕግ ማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

የሕግ ማስከበር ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ በየሦስት ወራት ግምገማ እንደሚደረግ አቶ ስንታየሁ ጠቁመዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ 1 ሺህ 450 ታክሲዎች፣ በማኅበር ደረጃ የታቀፉ 6 ሺህ ባጃጆች፣ 59 የኤርፖርት ታክሲዎችና 12 የሕዝብ ተሽከርካራች እንደሚገኙ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article❝በሴራ ልክፍት እየናወዙ የለውጡ አካል ሆኖ መቀጠል አይቻልም!❞ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ
Next articleጣይቱ ብጡል (ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ)