
የካቲት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ባስተላለፈው መልዕክት ❝በሴራ ልክፍት እየናወዙ የለውጡ አካል ሆኖ መቀጠል አይቻልም!❞ ብሏል።
ፓርቲው ያስተላለፈው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ ለውጡ በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም ከጅምሩ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዝገብ የጀመሩበት ኢትዮጵያውን በአጠቃላይ፤ በተለይም የአማራ ሕዝብ ለውጡን ደግፈው የቆሙበት ሁኔታ የሚታወስ ነው፡፡
ለለውጡ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑ ሕዝባዊ ጥያቄዎች በተለይም የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት፣ የኢኮኖሚ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ እርምጃዎችና የተካሄዱ ሪፎርሞች፣ የማኅበራዊ ልማት ማሻሻያዎች፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮችን የመለየትና የማረም፣ የፀጥታ የፍትሕና የደኅንነት ተቋማት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሕግ ሪፎርሞች፣ የትላልቅ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ችግር ተፈቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለውጥ… ወዘተ የለውጡ ዓበይት ትሩፋቶች የታዩባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡
በእነዚህ ትልልቅ ሀገራዊ ለውጦች ሂደት ውስጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ዘርፈ ብዙ ጦር ሰብቀዋል፤ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ወግተውናል፡፡ በሕዝብና በሀገር ላይ የተወረወሩ ጦሮች በዓይነትም ሆነ በይዘት የተለያዩ ነበሩ፡፡ ከአሸባሪው ትህነግና በአምሳሉ እስከፈጠራቸው የተደራጁ ሽፍቶች ድረስ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወግተዋል፡፡
በዚያው ልክ ደግሞ ቁሞ ቀሮች በግለሰብና በጠባብ ቡድንተኝነት ኔትወርክ ፈጥረው ብልጽግና ፓርቲን ለመናድ በሐሳብ ከመታገል ይልቅ ስም ማጥፋትን እንደ ትግል መሳሪያ ተጠቅመው ፓርቲውን ከውስጥ ለማፍረስ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቅዠታቸው እውን ሊሆን አልቻለም፡፡
ሕዝብ የሚበጀውን ያውቃልና ነፃና ገለልተኝነቱ በተመሰከረለት ምርጫ አመኔታና ይሁንታውን ለብልጽግና ሰጥቷል፡፡ ፓርቲያችን ለአምስት ዓመት ከሕዝብ የተሰጠውን ይሁንታ ተቀብሎ ብልጽግናን እንደ ራዕይ በማንገብ በሀገር በቀል እሳቤ እየተመራ፣ ወንድማማችነትን (ሕብረ-ብሔራዊነትን) መለያ ባህሪው በማድረግ፣ ከዋልታ ረገጥ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ይልቅ የመሐል ፖለቲካን (centrism) በማራማድ ለውጡን ብቻ ሳይሆን የተሳካ የትውልድ ሽግግርን እውን ለማድረግ የማያቋርጥ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብልጽግና ፓርቲ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በዚህ ጉባዔ አመራርና አባሉን በሚገባ ፈትሾ በአስተሳሰብ ውግንናው ለሕዝብና ለሀገር አንድነት አቅም የሆነ የጠራ አመራርና አባል ይዞ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ እንዲሳካም በቅድመ ጉባዔ መድረኮች ከላይ እስከ ታች ያለውን አመራርና አባሉን በግምገማዊ የስልጠና መድረኮች እያበቃና እያጠራ ይገኛል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ልክ እንደ ብአዴኑ ዘመን ጉባዔ በተቃረበ ቁጥር አንድም በውስጣችን ያሉ ቁሞ- ቀሮች ለሥልጣናቸው በመስጋት በሌላ መልኩ ደግሞ በኅልውና ዘመቻው የተሸነፉና ተስፋ የቆረጡ ትሕነግና የትሕነግ ወኪሎች ፓርቲውንና የፓርቲውን አመራሮች ከሕዝብ ለመነጠልና የተለመደውን ሀገርን የማፍረስ ፕሮጀክታቸውን የጉባዔውን ወቅት ተጠቅመው ሰፊ የሞት ሽረት ትግል እያካሄዱ ነው። ለዘመቻቸው የሚያቀርቡት ምክንያት የተለያየ ይሁን እንጂ ግባቸው በሕዝብ አመኔታ ያገኘውን ብልጽግና ፓርቲን ከውስጥና ከውጭ መናድ፤ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፡፡
ከእነዚህም መካከል በቅርቡ በወለጋ በወገኖቻችን ላይ በከፈቱት ጥቃት የደረሰው የሞት አደጋ በሌላ መልኩ ደግሞ የአማራ ክልልን በማያቋርጥ የጥፋት አጀንዳ ሕዝባችንን ማኅበራዊ ዕረፍት ለመንሳት እያደረጉ ያሉት ጥረት ለማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በእነዚህ ሁሉ አልሳካ ሲል ደግሞ ጉባዔውን መሰረት ያደረጉ ውዥንብሮች እና የሐሰት ክሶችን መሰንዘር ቀጥለዋል። እነዚህኞቹ ኃይሎች በአመለካከት ደረጃ ከሕዝብና ሕዝብ አመኔታ ከጣለበት ገዥው ፓርቲ ጋር ሳይሆን ለጠላት የሚቀርቡ ናቸው፡፡
በመሰረቱ በፓርቲው የአሠራርና ሕገ-ደንብ መሰረት ማንም አመራርና አባል በፓርቲው አሠራር ላይ ‘ግልፀኝነት ይጎድለኛል’ ካለ ማብራሪያ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ምላሽ እንዲሰጠው ለተገቢው ሕጋዊ የፓርቲው የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ጥያቄውን ማቅረብም ይችላል፡፡
ነገር ግን ሕጋዊውን አሠራር ተከትሎ ገና ምላሽ ባልተሰጠበት ሁኔታ የፓርቲውን ስምና አመራር በሐሰት መረጃወች ለመወንጀል መሞከር ሕገ-ወጥነት ብቻ ሳይሆን በፓርቲ ጉባዔ ሰሞን ጀግና መስሎ ለመታየት የመሞከር የከሰረ ብአዴናዊ መንገድ ነው።
በሌላ በኩል ከገንዘብ ጋር በተያያዘ በአመራሩ “ተዘረፈ” ተብሎ የተጠቀሰው ገንዘብ ፍፁም ሐሰትና እና በፓርቲው ወጪ የተደረገ ምንም አይነት ገንዘብ የሌለ ሲሆን፤ ይህንንም በፓርቲው በውስጥና በውጭ ኦዲተር ኦዲት የተደረገበትን ማስረጃ ማንኛውም አካል ቀርቦ መጠየቅና ማረጋገጥ የሚችለው እውነታ ነው።
እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ፓርቲያችን በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ለሚሠሩ አመራሮች እና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች በሌሎች ተቋማት እንዳለው ሕጋዊ አሠራር በረዥም ጊዜ የሚመለስ የብድር አገልግሎት ለጠየቁ አመራሮችና ሠራተኞች በአበዳሪ ተቋማት ሕግና አሠራር መሰረት የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና መልስ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ ያደርጋል፡፡
በዚህ አሠራር መሰረት የብድር ማስያዥያ (Collateral) አስይዘው በፓርቲያችን አቅራቢነት ከአበዳሪ ተቋማት ብድር የወሰዱ አመራር እና ሠራተኞች አሉ፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ የሚገርመው አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች ጭራሽ በብድሩ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ስማቸው በሐሰት የተጠቀሱ እንዳሉ ሆኖ ብድር የወሰዱ አመራርና ሠራተኞችም ቢሆኑ የወሰዱት የብድር መጠን በከሳሾቹ በቀረበው የሐሰት መረጃ መሰረት ሳይሆን አበዳሪ ተቋማቱ በአሠራራቸው መሰረት የሚፈቅደትን የብድር መጠን ነው፡፡
ይህ አሠራር በፓርቲ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥረው የሚሠሩ ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞችንም የሚጨምር ሲሆን፤ ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ በቋሚነት ያገለገሉ ሠራተኞች የብድር አገልግሎት ይመቻችላቸዋል፡፡ መሰል አሠራሮች በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለ ሲሆን፤ ፓርቲው በሕጋዊ የአሠራር መንገድ ሠራተኞቹን መደገፉን ይቀጥላል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የብልጽግና ጉባዔ አደናቃፊዎች፣ ጉባዔውን መሰረት ያደረጉ ውዥንብሮች እና የሐሰት ክሶችን መሰንዘር መርጠዋል፡፡ ይህም ሆኖ ፓርቲያችን ውስጡን ከማጥራትና በሕዝብ የተጣለበትን አመኔታ ከመወጣት ለአፍታም ቢሆን ወደኋላ አይልም፡፡
አመራራችን የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፤ ክልላችን እንደ ክልል፤ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር የተጋረጠባትን ፈተና በውል ይገዘነባል፡፡ ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር ለማረጋገጥ ርብርብ በማድረግ ላይም ይገኛል፡፡ በየደረጃው ያለው የክልላችን አመራር ሙሉ ትኩረቱ በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም፣ ዳግም ወረራ እንዳይከፈት ለመመከት፣ ነፃ ያልወጡ ቀሪ የተወሰኑ አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት ብሎም ጠላትን ለመቅበር በሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት ላይ አድርጓል፡፡
የተቀናጀ፣ የዕዝ ሰንሰለቱን የጠበቀ፣ ተጠያቂነት ያለበት አመራር በማረጋገጥ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ በሂደቱ የሚያጋጥመንን የትኛውንም አይነት የሴራ ድር በጣጥሰን የምናልፈው ሕዝብን ማዕከላችን አድርገን ነው፡፡
በዚህ ሂደት በሕዝብ ጫንቃ ላይ የወደቁ፣ በትላንት ያረጀና ያፈጀ የሴራ ፖለቲካ መንገድ እየተጓዙ የሕዝብ ልጅ ከመሆን ይልቅ ሸክም የሆኑ አመራሮች ከሕዝብ ትክሻ ላይ ተራግፈው የአመለካከት ጥራት ያለው፣ የወቅቱን የትግል መድረክ በድል የሚወጣ ብቁ አመራር እንዲፈጠር ያለምህረት እንታገላለን፡፡
በብዙ መልኩ ተስፋ የተጣለበት የሀገራዊ ምክከር መድረኩ፡- ፅንፈኛ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት ትጥቅ የሚፈታበት፤ ከትርክት ጦርነት ወጥተን የወንድማማችነትን እሴት ያዳበረ ትውልድ ግንባታ መሰረቱ የሚጣልበት፤ ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት ግንባታ እውን እንዲሆን የጋራ ሁለንተናዊ ስምምነት የሚደረስበት፤ … እንደመሆኑ መጠን መላ ኢትዮጵያዊያን በጉጉት ለሚጠብቁት ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር መድረክ የበኩላችንን አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
በሴራ ልክፍት እየናወዙ የለውጡ አካል ሆኖ መቀጠል አይቻልም!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
የካቲት 03/2014 ዓ.ም
ባሕር ዳር – ኢትዮጵያ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/