የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ፈር ቀዳጇ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚታወሱ ታሪኮቿ።

181

ባሕር ዳር: የካቲት 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የካቲት ወር የነጻነት ምዕራፍ ከፋች፤ የአልደፈር ባይነት አርማ፣ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚታወሱ ታሪካዊ ሁነቶች ያስተናገደችበት ነው፡፡ እነዚህ ሁነቶች አፍሪካውያን ችግራቸውን የመፍታት አቅም የላቸውም ለሚሉ ምላሽ የተሰጠባቸው፣ ዕጣ ፈንታቸውን መወሰን የሚያስችል በቂ ፖለቲካዊ እውቀትና ክህሎት እንዳላቸው ያሳዩባቸው እና ስር የሰደዱ የቅኝ ገዥዎች የፌዝ ትርክቶች ለመጨረሻ ጊዜ የተሰበሩባቸው ናቸው፡፡
በዚህም የካቲት የመላው ጥቁር ሕዝቦች ወር ተብሎ ይጠራል፡፡ በወሩ ከተከናወኑት ውስጥ ደግሞ ሦስት ዓበይት ክስተቶች ጎልተው ይታወሳሉ፡፡ የመጀመሪያው እና ትልቁ ሁነት የመላው የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ሁሉ ድል ተደርጎ የሚወሰደውና የሁሉ ነገር በር ከፋች የሆነው የዓድዋ ድል ነው፡፡ ይህ ድል ኢትዮጵያ የሰውነትን ክብር ለዘነጋው ዓለም ‹የሰውን ልጅ ክቡርነት› የገለጠችበት፣ በዓለም ያሉ ጥቁር ሕዝቦች ይደርስባቸው ከነበረው ግፍና የበታችነት ተጽኖ እንዲወጡ መሠረት የጣለችበት ነው፡፡ ጥቁሮች ነጮችን ለማገልገል እንደተፈጠሩ ይቆጠር የነበረበትን ታሪክ የቀየረና ዓለም አቀፍ ፋይዳ ያለው የማይነጥፍ ድል ነው-አድዋ፡፡
በዚህ ድል አፍሪካውያን ሀገራት ለኢትዮጵያ ክብር ሰጥተው በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሕብረ ቀለማት ያሸበረቀ ሰንደቅ ዓላማን የሀገራቸው ብሔራዊ አርማ አድርገው አውለብልበዋል፡፡ ጃማይካውያንም ለዚህ ድል ተገቢውን ክብር በመስጠት አርማቸው ብቻ ሳይሆን ማኅተባቸው አድርገው እስከማምለክ ደርሰዋል፡፡
ዓድዋ ለአፍሪካውያን የነጻነት ተጋድሎ ትልቅ መሠረት የተጣለበትና መንፈሳዊ አቅም የፈጠረ ድል ነው፡፡ የዓድዋን ጦርነት ተከትሎ አፍሪካን አንድ የማድረግ እና በመላው ዓለም የሚኖሩ አፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦችን የማስተሳሰር ራዕይ የሰነቀው የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ተጸንሷል፡፡ በካረቢያን ደሴት በነጮች የዘረኝነት ቀንበር ውስጥ ወድቀው ከፍተኛ ቀውስ ይደርስባቸው የነበሩ ጥቁሮችን ጨምሮ በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበሩ ሀገራት የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን እንዲያቀጣጥሉ ትልቅ ሥነልቦናዊ መነቃቃት ፈጥሮላቸዋል፡፡
የአድዋ ድልን ተከትሎ የተጀመረው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የምዕራብ አፍሪካውቷ ሀገር ጋና ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ አህጉራዊ ይዘት ተላብሶ ነጥሮ መውጣት ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ከወጡ በኋላም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ወታደራዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸው ስለነበር ከቅኝ ገዢዎቻቸው ጋር የፈጠሩት ጥብቅ ግንኙነት የፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ እንዲቀጭጭ አድርጎታል፡፡
በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴም ሆነ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታው ኢትዮጵያ የመሪነቱ ሚና ነበራት፡፡ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዝምባብዌ እና ሌሎችም ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ የነበራት ሚናም ከፍተኛ ነበር፡፡ መሪወቿም ምዕራባዊያን አፍሪካን ለመከፋፈል የፈጠሩትን አሻጥር በማፍረስ የማይፋቅ ታሪክ ጽፈዋል፡፡
ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ የአፍሪካ አባት የተባሉበት እና በአህጉሪቱ ጉዳይ ያሳዩት የዲፕሎማሲ ስኬት እንዲሁም ኀያልነታቸው የተመሰከረበት የታሪክ ምዕራፍ ከዚህ ሁነት ጋር ተያያዥነት አለው፡፡
በተያዘው ወር ታሪክ በትልቁ የሚዘክረው ሌላኛው ታሪካዊ ክስተት ኢትዮጵያውያን እንደሻማ ቀልጠው ሀገራቸው የነጻነት ቀንዲልነቷን እንድታስቀጥል ያደረጉበት ነው፡፡ የካቲት 12 ፋሽስት ኢጣሊያ ከአድዋው የተሸናፊነት ሥነ ልቦና መንቃት ተስኖት በእብሪት እና በጦር ትምክህት ተነሳስቶ በንጹኃን ላይ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ፈጽሟል፡፡ በአምስት ዓመቱ የዳግም ወረራ ሙከራ ጊዜ ለሦስት ቀናት በዘለቀው የበቀል ጥቃት ከ30 ሺህ የሚበልጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መስዋእት መሆናቸው በታሪክ ይታወሳል፡፡ እንደዚህ ያለው አረመኔያዊና የጭካኔ ጭፍጨፋ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አውራጃዎች መፈጸሙም የሚታወቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በደማቸው የጻፉት ታሪክ ወርሃ የካቲትን የጥቁሮች ያደረገ ያለመሸነፍ ታሪክ ነው፡፡
ሦስተኛው የዚህ ወር ጉልህ ታሪክ በአምስት ዓመታቱ የወረራ ሙከራ ጊዜ ወደ ውጪ አቅንተው የነበሩት ጃንሆይ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማ የተከሉበት ዕለት ነው፡፡ የካቲት 1/1933 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሱዳን በኩል ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ኦሜድላ በሚባል አዋሳኝ አካባቢ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል ብለዋል በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዓለማየሁ እርቅይሁን፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የረጅም ጊዜ የሀገረ መንግሥታት ታሪካ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ ምንም እንኳን በየአዝማናቱ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫና ቢበረታባትም በአፍሪካ ጉዳይ ትናንት የነበራት የታሪክ አሻራ ዛሬም አልነጠበፈም፡፡ ኢትዮጵያን የሚከተሉ የአፍሪካ ሀገራትም ቀላል የሚባሉ አይደለም፡፡ የበቃ (ኖ ሞር) ዘመቻን መቀላቀላቸው ደግሞ መንፈሱ እየጎመራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ይላሉ ዶክትር ዓለማየሁ እርቅይሁን፡፡ እሳቤው ነገም ነጥሮ እንዲወጣ የማድረግ አንድምታው ግልጽ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን የመሪነት ሚና ይዞ መቀጠል የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ቅድሚያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ስርዓት ሊኖረው ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ደካማ ሆኖ ማንም የሚዘውረው ከመሆን አያልፍም፡፡ በአፍሪካ ፖለቲካ ላይ ያላት ተሰሚነት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና ሚናም ታክ ሆኖ ይቀራል፡፡ ስለዚህ የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ሥርዓት በአግባቡ ሊያዝ እና ትክክለኛ መስመር ሊኖረው ይገባል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበአሜሪካ ኦሪገን የአማራ ማሕበር በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ760 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረገ፡፡
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኢፌዴሪ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ምስጋና አቀረቡ።