ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብና የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን በመደገፍ የድርሻውን እንዲወጣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

161

የካቲት 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ዋና ጸሐፊዋ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ጫናዎችን ውስጥ እያለፈ እንኳ ኹኔታዎችን በሰከነ ኹኔታ በመመልከት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ያለውን ግንኙነት ገንቢ በኾነ መልኩ ለማስቀጠል ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

በአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ለመታደም መምጣታቸውን በሀገሪቱ የአማራ፣ ሶማሌና ትግራይ ክልሎች ጉብኝት በማድረግ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ ለመገንዘብ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል። በጉብኝታቸው የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በኅብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን የጉዳት ደረጃ ለመገንዘብ መቻላቸውንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመሩ ጥረቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዋና ጸሐፊዋ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠል ዋና ጸሐፊው እና ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላሳዩት ተነሳሽነት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ጫናን ለማድረግ ያለሙ ተከታታይ ስብሰባዎችን ማካሄዱ አግባብነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰላምን የማደፍረስ ተግባራትን እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደርግበትን ጫና በማቋቋም አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ኹኔታ እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉን ለምክትል ዋና ጸሐፊዋ አስረድተዋቸዋል።

ሰሞኑን የተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባን በተሳካ ኹኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁም በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ ማሳለፉን፣ ኹሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መከናወኑን፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ኹኔታዎችን መፍጠሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሀገሪቱ አጠቃላይ የሰላም መደፍረስ እንዲኖር አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ገልጸው አኹንም በሚያደርገው ትንኮሳ የእርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዳይሆን ኾን ብሎ የማወክ ድርጊቱን እንደቀጠለበት ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ እንዲሁም በጦርነት ምክንያት በርካታ ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታን የሚሻ መሆኑን ጠቅሰዋል። መንግሥት በየብስም ኾነ በአየር በረራ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጠዋል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ እና የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን በመደገፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥት ተጨባጩን የኢትዮጵያ እውነታ የማስረዳት ተግባሩን አጠናክሮ የሚስቀጠል መሆኑን ለዋና ጸሐፊዋ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየተደራጀ ቡድን ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ የሕግ ታራሚዎች ማስመለጡን እና ዝርፊያ መፈጸሙ ተገለጸ።
Next articleʺየጠላት ግልገል ቁሞ ሲያንቀራጭ፣ በአፉ አስገባበት እንደ አንቃር ቆራጭ “