❝ ጉባኤውን ያለ ምንም እክል ማስተናገድ መቻሉ ለኢትዮጵያና ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው❞ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

75

ጥር 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-

35ተኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ በጉባኤው የተሳተፉ መሪዎችም በሰላም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው ስለ አፍሪካ የመከሩት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች ሕብረቱ ዘንድሮ ካስቀመጠው መሪ አጀንዳ አንጻር የተቃኙ ውሳኔዎችንም አሳልፈዋል።

በተለይም አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ቦታ እንድታገኝ ለማድረግ ኹሉም ሀገራት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኩል ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር የተካሄዱት የኹለትዮሽ ምክክሮች ኢትዮጵያ ከየሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት በልዩ ልዩ መስኮች ለማሳደግ የሚያስችሉ ናቸው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ 35ተኛውን የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤን በተሳካና በደመቀ ሁኔታ አዘጋጅታ እንግዶቿን በሰላም ወደ ሀገራቸው ሸኝታለች።

አሁንም ከፍተኛ የጤና ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የገባችውንም ቃል አክብራ ጉባኤው ከመጀመሩ አስቀድሞ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዘርፈ ብዙ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ወስዳለች።

ይህ ጉባኤ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ የነበሩ ጫናዎችን ኹሉ በመቋቋም ከእስከዛሬው በተለየ ድምቀት ጉባኤውን ያለ ምንም እክል ማስተናገድ መቻሏ ለኢትዮጵያና ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው።

35ተኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ የኢትዮጵያን በጎ የማይመኙ አካላት ሲሉት እንደነበረው ሳይሆን ሀገራችን በሰላማዊ መንገድ ፍዑም ኢትዮጵያዊነት በተሞላበት የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት ማንኛውንም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ኹነት በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ እንደምትችልም ዳግም ያስመሰከረችበት ነው።

ለዚህ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ የጸጥታ አካላት፣ መገናኛ ብዙኀን፣ አገልግሎት ሰጪዎች በአጠቃላይ እንግዶች ወደ ሁለተኛ ቤታቸው የመጡ ያህል እንዲሰማቸው ያደረጋችሁ ኹሉ በተለይም መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ፤ በጉባኤው ምክንያት የተፈጠሩ የመንገድ መጨናነቅና አንዳንድ ክለከላዎች ሳያማርሯችሁ በታላቅ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ በትዕግስትና በሞቀ የእንግዳ አቀባበል ስሜት ከጉባኤው መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ መንግስት ላቅ ያለ ምሥጋናውን ያቀርባል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየገቢዎች ሚኒስቴር በመንፈቅ ዓመቱ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
Next articleየአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ኮምቦልቻ ገቡ።