
ባሕር ዳር: ጥር 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በረዘሙ ዘመናት ያለ መሸነፍ ታሪካችን እንዴት መጣ? የማሸነፋችን ሚስጢር ምኑ ላይ ነው? ብለሕ ጠይቅ፡፡ ያን ጊዜ እንዴት እንዳልተሸነፍክ፣ የሚያኮራ ታሪክ እንዳለህ፣ ጠላቶች እንደሚፈሩህ፣ ወዳጆች እንደሚያከብሩህ፣ ክፉዎች እንደማይደፍሩህ፣ መልካም ታሪኮች ብቻ እንደሚከተሉህ፣ የወርቅ ቀላማት በማያረጅ ብዕር ላይ እንደመዘገቡህ፤ ድርሳናት ሁሉ ከፍ ከፍ እንዳደረጉህ፣ ሁሉም እንደሚቀኑብህ ይገባሃል፡፡ የሰው ዘር በተገኘበት፣ ስልጣኔ በተጀመረበት፣ ጨለማውን የሚገፍፍ ብርሃን በታየበት፣ ጠላት በሚመታበት፣ አሸናፊነት በነገሰበት፣ ጥበብ በመላበት፣ ዓይኖች በሚበረክቱበት፣ ምስጢራት በመሉበት ምድር ጀግኖች፣ ጠቢቦች፣ ብልሆች፣ መልከ መልካሞች፣ ጦረኞች፣ አሸናፊዎች፣ ፈጣሪ የሚወድዳቸው፣ የሰማይ በረከትን ሁሉ የሰጣቸው፣ አብዝቶ የሚጠብቃቸው፣ ለምስክርነት ያስቀመጣች ተናፋቂ ሰዎች አሉ፡፡
እልፍ ጊዜ በጠላት ተሞክረዋል፣ እልፍ ጊዜ ጣላት ጦር ሰብቆ፣ ሠራዊት አዝምቶባቸዋል፣ እልፍ ጊዜ ጠላቶች ዶልተውባቸዋል፣ ታዲያ ሁሉንም አሸንፈው በድል ተወጥተዋል፣ የተፈጠሩት ለአሸናፊነት ለድል ብቻ ነውና፡፡ ትዕዛዛትን ይጠብቃሉ፣ ሕግጋትን ያከብራሉ፣ ሀገራቸውን ከምንም አስበልጠው ይወዳሉ፣ ለሠንደቃቸው እስከ ሞት ድረስ ይታመናሉ፡፡ በደማቸው ፍሳሽ፣ በአጥንታቸው ክስካሽ የጸናች ሀገር ያቆማሉ፡፡ በብርሃኑና በጨለማው መካከል የምትቆም ለምልክት የተሰጠችውን ሠንደቃቸውን አስቀድመው ለድል ይገሰግሳሉ፡፡ ሠንደቋ ቃል ኪዳን ያረፈባት፣ ተስፋና አሸናፊነት ያለባት፣ ጠላት የማይደፍራት ናት፡፡ እርሷ በጨለማውና በብርሃኑ መካከል ትቆማለች፡፡ ጨለማዋን አሳልፋ ብርሃን ታመጣለች፡፡ እርሷን አስቀድሞ የዘመተ ሁሉ በድል ይመለሳል፡፡ እርሷን አስቀድሞ ጦር ሜዳ የተገኘ ሁኩ ምሽግ ያፈርሳል፣ ጠላትን ይደመስሳል፡፡ ከምንም በላይ የገዘፈውን፣ በወርቅ ቀለም የተጻፈውን፣ በማያረጅ ብራና ያረፈውን ታሪኳን ሊያጠፉ፣ ሀብቷን ሊዘርፉ ጠላቶች ብዙ ጊዜ ጥረዋል፣ አቀበት ወጥተዋል፣ ቆልቁለት ወርደዋል፡፡
ዳሩ የጠነከሩ፣ የሚፈሩና የሚተባባሩ ልጆች አሏትና አንዳቸውም አልተሳካለቸውም፡፡ ሌሎች በአንቀላፉበት ዘመን ቀድማ የነቃች፣ ሌሎች ባልሰለጠኑበት ዘመን አስቀድማ የሰለጠነች፣ ሌሎች በተደፈሩበት ዘመን ዳር ድንቧን ያስከበረች፣ የተከበረች፣ የታፈረች፣ ክንዷ የበረታ፣ ኃይሏ የማይረታ፣ ለተቸገሩት የደረሰች፣ ክፉዎችን አደብ ያስያዘች፣ በጨለማው ዘመን ጎዳናውን የሚያሳይ ብርሃን የፈነጠቀች፣ የክፉዎችን ግንብ ያፈራረሰች፣ የጀግኖች እናት ናት ኢትዮጵያ፡፡
ለዚች ድንቅ ምድር ዋጋ ተከፍሎላታል፤ ነገሥታቱ ተዋድቀውላታል፣ የጦር አበጋዞች፣ ጀግና ጦረኞች ተሰውተውላታል፡፡ ለእርሷ መሞት ክብር መሆኑን የሚያምኑት ልጆቿ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ከፊት አስቀድመው ወደ ፊት ብቻ ይገሰግሳሉ፡፡ ጠላቶቻቸውንም ድል አድርገው በድል ይመለሳሉ፡፡ በድል ጎዳና ይመላለሳሉ፡፡
ኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት ኩራት፣ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት፣ ኢትዮጵያዊነት የድል ባለቤት ነውና በኢትዮጵያዊነት ገመድ እየተሳሰሩ፣ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ተቀምጠው እየተመካከሩ አያሌ ጀብዱዎች ሠርተዋል፡፡ እራሳቸው ኮርተው ሀገርና ወገናቸውን አኩርተዋል፡፡
እነሆ ጀግኖች ሲያልፉ ጀግኖች እየተተኩ ያስቀጠሏት፣ የጠበቋትና ያስከበሯት ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ ሺሕ ጠላቶች ሲወለዱባት፣ ሺሕ ጀግኖች እየተወለዱላት፣ ጀግኖቿ ጠላቶቿን እየቀጩላት ነው እዚህ የደረሰችው፡፡ ዛሬም ሺህ ጠላቶች ተነስተውባታል፡፡ ሺሕ ጀግኖችም ያስፈልጓታል፡፡ አባቶቻቸው ሞክረው ያልተሳካላቸውን ድል ልጆቹ ለመሞከር በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ የከፈቱት ብዙዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ያሸነፈ፣ የኢትዮጵያንም ደንበርና ክብር በጉልበት ያለፈ እንደሌለ እያወቁ ዛሬም ጥፋታቸውን አይተውም፡፡ ዳሩ የዛሬዎቹም ይሸነፋሉ፡፡ እንደ ቀደሙት ጠላቶች ሁሉ ይጠፋሉ፡፡
የቀደሙት ኢትዮጵያን ተከብረውና ተፈርተው የኖሩት እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ አንድነት ስለፈጠሩ ነበር፡፡
በሀገራቸው ጉዳይ ልዩነት የላቸውም፡፡ በሠንደቃቸው ክብር መለያዬት አይፈጥሩም፡፡ ሠንደቋ ተደፈረች፣ ሀገር ተነካች በተባለች ቁጥር በአራቱም ንፍቅ እየዘመቱና ጠላትን እያነከቱ፣ በጋራ ደማቸው የጋራ ሀገር አጽንተዋል፡፡ ዛሬ ታሪክ አስቀድሞ የሚጠራት፣ ከፍ አድርጎ ያከበራት፣ የአጥኚዎች ዓይን የበዛባት፣ በረከት የመላባት ሀገር ኢትዮጵያ ልጆቿ ኮርተው የሚናገሩላት፣ ጥቁሮች ተስፋችን ናት የሚሏት ጀግና ልጆች ስለነበሯት፣ በደምና አጥንታቸው ስላስከበሯት ነው፡፡
ታዲያ ትውልድ ሁሉ እንደኮራባት፣ ጠላት ሁሉ እንደፈራት፣ ወዳጅ ሁሉ እንዳከበራት እንድትኖር ዛሬም በኢትዮጵያ ምድር የተፈጠርክ፣ ኢትዮጵያን ለማስከበር አደራ የተሰጠህ ሳትሰለች፣ ሳትደክም በርትተህ ተነስ፡፡ እየከፋፈሉ ለሚያባሉህ፣ ከከፈታው ለሚያወርዱህ፣ ከወንድሞችህ ጋር ለሚያጋጩህ፣ ቀዳሚነትክን ለሚያስረሱህ ቦታ አትስጣቸው፡፡ ይልቁንስ የሚያጋጩህን፣ ሀገርህን የሚነኳትን እየተከታተልክ መኖሪያ ንሳቸው፡፡ ድል ያለው ከተጣመሩ ክንዶች ጋር ነውና፡፡ አንድነት ፍጠር፣ ከወገኖችህ ጋር ተጣመር፣ ጠላቶችህንም መክት፡፡
አባቶችህ ጠላቶቻቸውን ያሸነፉት በአንድነት ስላበሩ እንጂ በመንደር ስለተከፋፈሉ አይደለም፡፡ ለቃል ኪዳኗ ሠንደቅ ታማኝ ሁን፡፡ ሀገርንህን በፍጹም ፍቅር አገልግል፡፡ ከሚነኳት ጠላቶች ጋር በፍጹም ጀግንነት ታገል፡፡ እርሷን ለሚነኳት የተቆጣ ነብር ሁን፡፡ ኩሩ ታሪክ ላለው ልኩ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ሚዛን ሳትጎድል በፍጹም ጀግንነት ታገል፡፡
ከኢትዮጵያዊነት ሚዛን ከጎደልክ እኒያ መንደርና ሠፈር ሳይመርጡ በየጠረፉ ሄደው የወደቁ ጀግኖች አባቶችህ አጽም ይወቅስሃል፡፡ የእነርሱ የጀግንነት መንፈስ ሰላምህን ይነሳሃል፡፡ አንተ ልክህ ኢትዮጵያዊነት፣ አንተ ልክህ አንድነት፣ አንተ ልክህ አሸናፊነት፣ አንተ ልክህ ከፍ ማለት፣ አንተ ልክህ አትንኩኝ ማለት ነው፡፡ በአንድነት ተጣምረህ ሀገርህን ጠብቃት፣ ሠንደቋን ከፍ አድርገህ ስቀልላት፡፡ ያን ጊዜ በመንደር የሚከፋፈሉት፣ የኢትዮጵያዊነትን ማማ የረሱት፣ ስሟን ያረከሱት ያፍራሉ፣ ይሸማቀቃሉ፡፡ አንተ ደግሞ አባቶችህ ስም እየማልክ፣ በሠራኸው ጀብዱ እየኮራህ በክብርና በደስታ ትኖራለህ፡፡ ስምህንም ከፍ አድርገህ በብራና ላይ ታሳርፋለህ፡፡
ኢትዮጵያ ማለት ረቂቅ ናት፣ ሠንደቋም ምስጢር ነው፣ ረቂቋን አክብራት፣ ሚስጢሯን ጠብቃት፡፡ መከራዎች ሁሉ ሊበዙብህ፣ በደሎች ሁሉ ሊበረክቱብህ ይችላሉ ነገር ግን ከከፍታህ ማማ እንዳትወርድላቸው፡፡ በጽናት ታገለህ አሳፍራቸው እንጂ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/